ሕዝቅኤል 36 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)በረከት በእስራኤል ላይ 1 አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ተራሮች ትንቢት ተናገር፥ እንዲህም በላቸው፦ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታን ቃል ስሙ። 2 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠላት በእናንተ ላይ፦ “እሰይ! የጥንት ከፍታዎች ለእኛ ርስት ሆነዋል” ብሏልና፥ 3 ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰላጠፉአችሁ፥ ለቀሩት አሕዛብ ርስት ትሆኑ ዘንድ በዙሪያችሁ ያሉ ባድማ አድርገዋችኋልና፥ ውጠዋችኋልምና፥ እናንተም የተናጋሪዎች ከንፈር መተረቻና የሕዝብ ማላገጫ ሆናችኋልና 4 ስለዚህ፥ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታ እግዚአብሔርን ቃል ስሙ። ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኮረብቶች፥ ለውሃ መውረጃዎችና ለሸለቆዎች፥ ለፈራረሱ ቦታዎችና ባዶ ለሆኑትም በዙሪያ ላሉት ለቀሩት ሕዝቦች ምርኮና መሳቂያ ለሆኑት ከተሞች እንዲህ ይላል፥ 5 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያሳድዱአትና ይበዘብዙአት ዘንድ በልባቸው ሁሉ ደስታና በነፍሳቸው ንቀት ምድሬን ርስት አድርገው ለራሳቸው በሰጡ በቀሩት አሕዛብና በኤዶምያስ ሁሉ ላይ በቅንዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ፤ 6 ስለዚህ ስለ እስራኤል ምድር ትንቢት ተናገር፥ ለተራሮችና ለኮረብቶች፥ ለውሃ መውረጃዎችና ለሸለቆች እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በቅንዓቴና በመዓቴ ተናግሬአለሁ የሕዝቦችን ስድብ ተሸከማችሁአልና፤ 7 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዙሪያችሁ ያሉ ሕዝቦች በእርግጥ ስድባቸውን ይሸከማሉ ብዬ እጄን አንስቻለሁ። 8 እናንተም የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ ቅርንጫፎችን ታቆጠቁጣላችሁ፥ ለሕዝቤ ለእስራኤል ፍሬአቸሁን ትሰጣላችሁ ለመምጣት ቀርበዋልና። 9 እነሆ እኔ ለእናንተ ነኝና፥ ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ትታረሳላችሁ ትዘራላችሁም፤ 10 የእስራኤልን ቤት ሰዎች ሁሉ ሙሉን በእናንተ ላይ አበዛለሁ፥ በከተሞቹም ሰዎች ይኖሩባቸዋል፥ የፈረሱት ስፍራዎችም ይሠራሉ፤ 11 ሰውንና እንስሳም በእናንተ ላይ አበዛለሁ፥ እነርሱም ይበዛሉ ያፈራሉም፤ እንደ ቀድሞም ሰዎችን አኖርባችኋለሁ፥ መጀመሪያ ካደረግሁላችሁ ይልቅ መልካም አደርግላችኋለሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። 12 ሰዎችን፥ ሕዝቤን እስራኤልን፥ በእናንተ ላይ አስሄዳቸዋለሁ፤ እነርሱም ይወርሱሻል ርስትም ትሆኛቸዋለሽ፥ ከእንግዲህም ወዲያ ልጅ አልባ አታደርጊአቸውም። 13 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነርሱ፦ ሰው በሊታ ምድር ነሽ ሕዝብሽንም ልጅ አልባ የምታደርጊ ነሽ ብለዋችኋልና 14 ስለዚህ ዳግመኛ ሰው አትበይም፥ ዳግመኛም ሕዝብሽን ልጅ አልባ አታደርጊም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ 15 ዳግመኛም የአሕዛብን ውርደት አላሰማብሽም፥ ዳግመኛም የአሕዛብን ስድብ አትሸከሚም፥ ዳግመኛም ሕዝብሽን አታሰናክዪም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የእስራኤል መታደስ 16 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 17 የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት በምድራቸው በተቀመጡ ጊዜ በመንገዳቸውና በሥራቸው አረከሱአት፥ መንገዳቸው በፊቴ እንደ አደፍ ነበረ። 18 በምድር ላይ ባፈሰሱት ደምና በጣዖቶቻቸውም አርክሰዋታልና መዓቴን አፈሰስሁባቸው። 19 ወደ መንግሥታት በተንኋቸው ወደ አገሮችም ተዘሩ፤ እንደ መንገዳቸውና እንደ ሥራቸው መጠን ፈረድሁባቸው። 20 ወደ ሄዱባቸውም ወደ ሕዝቦች በመጡ ጊዜ፥ ሰዎች እነርሱን፦ ከምድሩ የወጡ የጌታ ሕዝብ እነዚህ ናቸው ሲሉአቸው ቅዱስ ስሜን አረከሱ። 21 እኔ ግን የእስራኤል ቤት በመጡባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሱት ለቅዱስ ስሜ እራራለሁ። 22 ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ የምሠራው ስለ እናንተ ሳይሆን በሄዳችሁባቸው በመንግሥታት መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ነው። 23 በመንግሥታት መካከል የረከሰውን፥ በመካከላቸው እናንተ ያረከሳችሁትን ታላቁን ስሜን እቀድሰዋለሁ፤ ዓይናቸው እያየ በእናንተ በተቀደስሁ ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ መንግሥታት ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 24 ከመንግሥታት መካከል አወጣችኋለሁ፥ ከየአገሩም ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፥ ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ። 25 በእናንተ ላይ ንጹሕ ውኃ እረጫለሁ እናንተም ትነጻላችሁ፥ ከርኩሰቶቻችሁ ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አነጻችኋለሁ። 26 አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፥ አዲስ መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋያማ ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፥ የሥጋ ልብ እሰጣችኋለሁ። 27 መንፈሴን በውስጣችሁ አኖራለሁ፥ በትእዛዜ እንድትሄዱና ፍርዴን እንድትጠብቁ አደርጋችኋለሁ ትፈጽሟቸዋላችሁም። 28 ለአባቶቻችሁ በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። 29 ከርኩሰታችሁ ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህሉን እጠራዋለሁ አበዛዋለሁም፥ ረኃብም አላመጣባችሁም። 30 የረኃብን ስድብ ዳግም ከመንግሥታት እንዳትቀበሉ የዛፍን ፍሬና የእርሻውን ምርት አበዛለሁ። 31 ክፉዎች መንገዶቻችሁንና መልካም ያልሆኑ ሥራዎቻችሁን ታስባላችሁ፥ ስለ በደሎቻችሁና ስለ ርኩሰቶቻችሁም ራሳችሁን ትጠላላችሁ። 32 ይህንን የሠራሁት ለእናንተ እንዳልሆና በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ መንገዳችሁ እፈሩና ተዋረዱ። 33 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከኃጢአታችሁ ሁሉ በማነጻችሁ ቀን በከተሞች ሰዎችን አኖራለሁ ባድማዎቹም ስፍራዎች ይሠራሉ። 34 በአላፊ አግዳሚው ሁሉ ዐይን ባድማ የነበረች፥ ባድማዋ ምድር ትታረሳለች። 35 “ባድማ የነበረች ይህች ምድር እንደ ዔድን ገነት ሆነች፤ የወደሙት፥ ባድማ የሆኑት፥ የፈረሱት ከተሞች አጥር ተሰርቶላቸዋል፥ መኖሪያም ሆነዋል” ይላሉ። 36 በዙሪያችሁም የቀሩት መንግሥታት፥ የፈረሱትን ስፍራዎች የሠራሁ፥ ባድማ የሆነውንም የተከልሁ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ፥ እኔም አደርገዋለሁ። 37 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አሁንም የእስራኤል ቤት እንድሠራላቸው እንዲፈልጉኝ እፈቅድላቸዋለሁ፥ ሰዎችንም እንደ መንጋ አበዛላቸዋለሁ። 38 እንደ ተቀደሰ መንጋ፥ በበዓላቶችዋ ቀን እንደሚሆኑ እንደ ኢየሩሳሌም መንጋ፥ እንዲሁም የፈረሱት ከተሞች በሰዎች መንጋ ይሞላሉ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። |