ዘፀአት 40 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የድንኳኑ መተከልና ዕቃዎቹ ሁሉ በየቦታቸው መቀመጣቸው 1 ጌታም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2 “በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን የመገናኛውን ድንኳን ማደሪያ ትተክላለህ። 3 በእርሱም ውስጥ የምስክሩን ታቦት ታኖራለህ፥ ታቦቱንም በመጋረጃ ትጋርዳለህ። 4 ገበታውን ታስገባለህ፥ በአግባቡ ታሰናዳለህ፤ መቅረዙንም አስገብተህ ቀንዲሎቹን ትለኩሳለህ። 5 ለዕጣን የሚሆነውን የወርቅ መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ፊት ታኖራለህ፥ በማደሪያውም ደጃፍ መጋረጃውን ትጋርዳለህ። 6 የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው መግቢያ ፊት ታኖረዋለህ። 7 የመታጠቢያውን ሳሕን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኑረህ ውኃ ትጨምርበታለህ። 8 በዙሪያውም አደባባዩን ትተክላለህ፥ መጋረጃውንም በአደባባዩ ደጃፍ ትዘረጋለህ። 9 የቅባቱንም ዘይት ወስደህ ማደሪያውን እና በእርሱ ያለውን ሁሉ ትቀባለህ፥ እርሱን፥ ዕቃውንም ሁሉ ትቀድሳለህ፤ ቅዱስም ይሆናል። 10 የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውንና ዕቃዎቹን ሁሉ ትቀባለህ፥ መሠዊያውንም ትቀድሳለህ፤ መሠዊያውም እጅግ የተቀደሰ ይሆናል። 11 የመታጠቢያውን ሳሕንና ማስቀመጫውን ትቀባዋለህ፥ ትቀድሰዋለህም። 12 አሮንንና ልጆቹን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ታቀርባቸዋለህ፥ በውኃም ታጥባቸዋለህ። 13 አሮንን የተቀደሰውን ልብስ ታለብሰዋለህ፥ ካህን እንዲሆነኝ ትቀባዋለህ፥ ትቀድሰውማለህ። 14 ልጆቹንም አቅርበህ ቀሚስ ታለብሳቸዋለህ፤ 15 አባታቸውን እንደ ቀባህ ትቀባቸዋለህ፥ ካህናትም ይሆኑልኛል፤ ቅባታቸውም ለሚመጣው ትውልድ ሁሉ ለዘለዓለም ክህነት ይሆንላቸዋል።” 16 ሙሴም ጌታ እንዳዘዘው ሁሉ አደረገ፥ እንዲሁም አደረገ። 17 እንዲህም ሆነ፤ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ማደሪያው ተተከለ። 18 ሙሴ ማደሪያውን ተከለ፥ እግሮቹን አኖረ፥ ሳንቆቹን አቆመ፥ መወርወሪያዎቹን አደረገባቸው፥ ምሰሶቹንም አቆመ። 19 ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ድንኳኑን በማደሪያው ላይ ዘረጋ፥ የድንኳኑንም መደረቢያ በላዩ አደረገበት። 20 ጽላቱን ወስዶ በታቦቱ ውስጥ አኖረው፥ መሎጊያዎቹንም በታቦቱ አደረገ፥ የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ አኖረው፤ 21 ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ታቦቱን ወደ ማደሪያው አስገባ፥ የሚሸፍነውን መጋረጃ አድርጎ የምስክሩን ታቦት ሸፈነ። 22 ገበታውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ ከመጋረጃው ውጭ፥ በማደሪያው በሰሜን በኩል አኖረው፤ 23 ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ኅብስቱን በላዩ በጌታ ፊት አሰናዳ። 24 መቅረዙን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ በገበታው ፊት ለፊት፥ በማደሪያው በደቡብ በኩል አኖረ፤ 25 ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ቀንዲሎቹን በጌታ ፊት አበራ። 26 የወርቁን መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በመጋረጃው ፊት አኖረ፤ 27 ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው መልካም መዓዛ ያለውን ዕጣን ዐጠነበት። 28 መጋረጃውን በማደሪያው መግቢያ ፊት ሰቀለ። 29 ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው መግቢያ ፊት አኖረ፥ የሚቃጠልና የእህልን መሥዋዕት ሠዋበት። 30 የመታጠቢያውን ሳሕን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አስቀመጠ፥ ለመታጠቢያም ውኃን ጨመረበት። 31 ሙሴ፥ አሮንና ልጆቹ እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በእርሱ ታጠቡ፤ 32 ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ወደ መገናኛው ድንኳን በሚገቡበት ጊዜ፥ ወደ መሠዊያውም በሚቀርቡበት ጊዜ ይታጠቡ ነበር። 33 በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ አደባባዩን ተከለ፤ በአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ ዘረጋ። በዚህ ዓይነት ሙሴ ሥራውን ፈጸመ። ደመናውና ክብሩ 34 ከዚህ በኋላ ደመናው የመገናኛውን ድንኳን ሸፈነ፥ የጌታም ክብር ማደሪያውን ሞላ። 35 ደመናው በላዩ ስለ ነበረና የጌታ ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን መግባት አልቻለም። 36 ደመናው ከማደሪያው በሚነሣበት ጊዜ የእስራኤል ልጆች ወደሚጓዙበት ሁሉ ይሄዱ ነበር። 37 ደመናው ካልተነሣ ግን እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር። 38 በጉዞአቸው ሁሉ በእስራኤል ቤት ሁሉ ፊት የጌታ ደመና በቀን በማደሪያው ላይ፥ በሌሊትም እሳት በዚያ ላይ ነበረ። |