ዘፀአት 22 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 “ሌባ ቤት ሲሰብር ቢገኝ፥ ቢመታና ቢሞት፥ በመታው ሰው ላይ ደሙ የለበትም። 2 ፀሐይ ከወጣችበት ግን ደሙ በላዩ ነው፥ ዋጋውን ይክፈል፤ የሚከፍለው ከሌለው ስለ ሰረቀው ነገር ይሸጥ። 3 የሰረቀው በሬ ወይም አህያ ወይም በግ ቢሆንና በሕይወት ሳለ በእጁ ቢገኝ፥ የሰረቀውን ሁለት እጥፍ አድርጎ ይክፈል። 4 አንድ ሰው በእርሻ ወይም በወይን ስፍራ ከብቱን ቢያሰማራ፥ የሌላውንም ሰው እርሻ ቢያስበላ፥ ከተመረጠ እርሻውና መልካም ከሆንው ወይኑ ይካስ። 5 እሳት ቢነሣ፥ እሾኽንም ቢይዝ፥ ክምሩንም ወይም ያልታጨደውን እህል ወይም እርሻውን ቢያቃጥል፥ እሳቱን ያነደደው ይካስ። 6 አንድ ሰው ብር ወይም ሌላ ነገር እንዲጠብቅለት ለባልንጀራው በአደራ ቢሰጥ፥ ከቤቱም ቢሰረቅና ሌባው ቢገኝ እጥፍ ይክፈል። 7 ሌባው ግን ባይገኝ፥ እጁን በባልንጀራው ንብረት ላይ እንዳልዘረጋ እንዲታወቅ ባለቤቱ ወደ እግዚአብሔር ፊት ይቅረብ። 8 ሰዎች ስለ በሬ ወይም ስለ አህያ ወይም ስለ በግ ወይም ስለ ልብስ ወይም ስለ ሌላ ስለ ጠፋ ነገር ቢካሰሱ፥ አንዱም፦ ይህ የእኔ ነው ቢል ክርክራቸው ወደ እግዚአብሔር ይምጣ፤ እግዚአብሔርም የፈረደበት እርሱ ለባልንጀራው እጥፍ አድርጎ ይክፈል። 9 አንድ ሰው ለባልንጀራው አህያ ወይም በሬ ወይም በግ ወይም ሌላ እንስሳ እንዲጠብቅለት በአደራ ቢሰጥ፥ ማንም ሳያይ ቢሞት ወይም ቢጎዳ ወይም ቢማረክ፥ 10 በባልንጀራው ንብረት ላይ እጁን እንዳልዘረጋ የጌታ መሐላ በሁለታቸው መካከል ይሁን፤ የከብቱም ባለቤት መሐላውን ይቀበል፥ እርሱም ምንም አይክፈል። 11 ከእርሱ ከተሰረቀ ግን ለባለቤቱ ይክፈል። 12 በአውሬ ተበልቶ ከሆነ የቀረውን ለምስክርነት ያምጣው፤ በአውሬም ስለተበላ አይክፈል። 13 አንድ ሰው ከባልንጀራው አንዳች ቢዋስ ባለቤቱም ከእርሱ ጋር ሳይኖር ቢጎዳ፥ ወይም ቢሞት፥ ካሳ ይክፈለው። 14 ባለቤቱ ግን ከእርሱ ጋር ቢኖር አይክፈል፤ አከራይቶት ከሆነም ኪራዩን ብቻ ይክፈል። ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ሕጎች 15 “ሰው ያልታጨችውን ድንግል ቢያታልላት፥ ከእርሷም ጋር ቢተኛ፥ የማጫዋን ዋጋ ሰጥቶ ሚስት ያድርጋት። 16 አባትዋ ለእርሱ አልሰጥም ቢል ለደናግል የሚሰጥ ማጫ ብር ይክፈል። 17 መተተኛይቱን በሕይወት እንድትኖር አትፍቀድላት። 18 ከእንስሳ ጋር የሚተኛ ፈጽሞ ይገደል። 19 ከጌታ በቀር ለሌላ አምላክ የሚሠዋ ፈጽሞ ይጥፋ። 20 ስደተኛውን አትበድለው፥ አትጨቁነውም፥ እናንተም በግብጽ ምድር ስደተኞች ነበራችሁና። 21 መበለቲቱንና ድሀ አደጉን አታስጨንቁአቸው። 22 ብታስጨንቁአቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ ግን እኔ ጩኸታቸውን በእርግጥ እሰማለሁ፤ 23 ቁጣዬም ይነዳል፥ በሰይፍም እገድላችኋለሁ፥ ሚስቶቻችሁ መበለት፥ ልጆቻችሁም ድሀ አደጎች ይሆናሉ። 24 ከአንተ ጋር ላለው ለአንዱ ድሃ ወገኔ ገንዘብ ብታበድረው፥ እንደ ባለ አራጣ አትሁንበት፥ ወለድም አታስከፍለው። 25 የባልንጀራህን ልብስ ለመያዣ ብትወስድ ፀሐይ ሳትገባ መልስለት፤ 26 የሚለብሰው ሌላ የለውም፥ ገላውን የሚሸፍንበት እርሱ ብቻ ነውና፤ ወደ እኔም ቢጮኽ መሐሪ ነኝና እሰማዋለሁ። 27 እግዚአብሔርን አትስደብ፥ የሕዝብህንም መሪ አትርገም። 28 ከሙላትህና ከጭማቂህ ለማቅረብ አትዘግይ፤ የልጆችህንም በኩር ትሰጠኛለህ። 29 ከበሬህና ከበግህም እንዲሁ አድግር፤ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቀመጥ፥ በስምንተኛውም ቀን ለእኔ ትሰጠዋለህ። 30 ቅዱስ ወገን ትሆኑልኛላችሁ፤ ስለዚህ በሜዳ አውሬ የገደለውን ሥጋ አትብሉ፤ ለውሻ ጣሉት። |