Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘፀአት 20 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ዐሥሩ ትእዛዞች

1 እግዚአብሔርም እነዚህን ቃሎች ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፦

2 “ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ ጌታ አምላክህ እኔ ነኝ።

3 “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ።

4 በላይ በሰማያት ካለው፥ በታች በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም አምሳል፥ የተቀረጸ ምስል ለአንተ አታድርግ።

5 አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውም፤ እኔ ጌታ አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፥

6 ለሚወድዱኝ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ ነኝ።

7 “የጌታ የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ ጌታ ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ሳይቀጣው አያልፍም።

8 “እንድትቀድሰው የሰንበትን ቀን አስታውስ።

9 ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፥ ተግባርህንም ሁሉ ፈጽም፤

10 ሰባተኛው ቀን ግን ለጌታ አምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህ፥ ሴት ልጅህ፥ ወንድ ሠራተኛህ፥ ሴት ሠራተኛህ፥ ከብትህ፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ መጻተኛ ሁሉ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፤

11 ጌታ በስድስት ቀናት ሰማያትንና ምድርን፥ ባሕርን፥ እና በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና፤ ስለዚህ ጌታ የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም።

12 “ጌታ አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም፥ አባትህንና እናትህን አክብር።

13 “አትግደል።

14 “አታመንዝር።

15 “አትስረቅ።

16 “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።

17 “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት፥ ወንድ ሠራተኛውን፥ ሴት ሠራተኛውን፥ በሬውን፥ አህያውን፥ የባልንጀራህ የሆነውን ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ።”

18 ሕዝቡም ሁሉ ነጎድጓዱንና መብረቁን፥ የቀንደ መለከቱን ድምፅ፥ ተራራውንም ሲጤስ አዩ፤ ሕዝቡም ፈሩ ተንቀጠቀጡም፥ ርቀውም ቆሙ።

19 ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “አንተ ተናገረን እኛም እንሰማለን፤ ነገር ግን እንዳንሞት እግዚአብሔር አይናገረን።”

20 ሙሴም ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ ሊፈትናችሁ፥ ኃጢአትንም እንዳትሠሩ እርሱን መፍራት በልባችሁ እንዲሆን እግዚአብሔር መጥቷልና።”

21 ሙሴ እግዚአብሔር ወዳለበት ወደ ጨለማው ሲቀርብ ሕዝቡ ግን ርቀው ቆሙ።


ስለ መሠዊያው የተሰጠ ሕግ

22 ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፥ ‘እኔ ከሰማይ ከእናንተ ጋር እንደተነጋገርሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል።

23 ከእኔ ጋር የብር አማልክትን አትሥሩ፥ የወርቅ አማልክትንም ለእናንተ አትሥሩ።

24 ከአፈርም መሠዊያ ሥራልኝ፥ የሚቃጠለውንና የሰላም መሥዋዕትህን በጎችህንም በሬዎችህንም ሠዋበት፤ ስሜን በማሳስብበት ስፍራ ሁሉ ወደ አንተ መጥቼ እባርክሃለሁ።

25 የድንጋይም መሠዊያ ብታደርግልኝ በተጠረበ ድንጋይ አትሥራው፤ በመሣሪያ ብትነካው ታረክሰዋለህና።

26 ኃፍረተ ሥጋህ በእርሱ ላይ እንዳይገለጥ ወደ መሠዊያዬ በደረጃ አትውጣ።’”

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች