ዘፀአት 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የሙሴ መወለድ 1 ከሌዊ ወገን የሆነ አንድ ሰው ሄዶ የሌዊን ልጅ አገባ። 2 ሴቲቱም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅም ወለደች፤ መልካምም እንደሆነ ባየች ጊዜ ሦስት ወር ሸሸገችው። 3 ደግሞም ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ፥ የደንገል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም እዚያ ውስጥ አስገባችው፥ በወንዝም ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው። 4 እኅቱም ምን እንደሚደርስበት ለማየት በሩቅ ቆማ ትከታተለው ነበር። 5 የፈርዖንም ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ ወረደች፤ ደንገጥሮችዋም በወንዝ ዳር ይሄዱ ነበር፤ ሣጥኑንም በቄጠማ ውስጥ አየች፥ ደንገጥሩዋንም ልካ አስመጣችው። 6 በከፈተችውም ጊዜ ሕፃኑን አየች፥ እነሆም ሕፃኑ ያለቅስ ነበር፤ አዘነችለትም፦ “ይህ ከዕብራውያን ልጆች አንዱ ነው” አለች። 7 እኅቱም ለፈርዖን ልጅ፦ “ሕፃኑን እንድታጠባልሽ ሄጄ የምታጠባ ሴት ከዕብራውያን ሴቶች ልጥራልሽን?” አለቻት፤ 8 የፈርዖንም ልጅ፦ “ሂጂ” አለቻት፤ ብላቴናይቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ጠራች። 9 የፈርዖንም ልጅ፦ “ይህን ሕፃን ወስደሽ አጥቢልኝ፥ ዋጋሽንም እከፍልሻለሁ” አለቻት። ሴቲቱም ሕፃኑን ወስዳ አጠባችው። 10 ሕፃኑም አደገ፥ ወደ ፈርዖንም ልጅ አመጣችው፥ ለእርሷም ልጅ ሆነላት። እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና ስትልም ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው። የሙሴ ወደ ምድያም መኮብለል 11 በነዚያም ቀኖች፥ ሙሴ ባደገ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ፥ የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ፤ የግብጽም ሰው ከወንድሞቹ አንድ የሆነውን ዕብራዊ ሰው ሲመታ አየ። 12 ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፥ ማንንም አላየም፥ ግብፃዊውንም ገደለው፥ በአሸዋም ውስጥ ደበቀው። 13 በሁለተኛውም ቀን ወጣ፥ ሁለት ዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፥ በዳዩንም፦ “ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ?” አለው። 14 እሱም፦ “አንተን በእኛ ላይ አለቃና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?” አለው። ሙሴም፦ “በእውነት ይህ ነገር ታውቆአል” ብሎ ፈራ። 15 ፈርዖንም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኮበለለ፥ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፥ በውኃም ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ። 16 የምድያምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም መጥተው ውኃ ቀዱ፥ የአባታቸውንም በጎች ሊያጠጡ የውሀውን ገንዳ ሞሉ። 17 እረኞችም መጥተው ገፉአቸው፤ ሙሴ ግን ተነሥቶ ረዳቸው፥ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው። 18 ወደ አባታቸው ወደ ሩኤልም ሄዱ እርሱም፦ “ለምን ዛሬ ፈጥናችሁ መጣችሁ?” አላቸው። 19 እነርሱም፦ “አንድ ግብፃዊ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፥ ደግሞም ቀዳልን፥ በጎቻችንንም አጠጣ” አሉት። 20 ልጆቹንም፦ “ሰውዬው የት ነው? ለምንስ ይህንን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት ምግብም ይብላ” አላቸው። 21 ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ፈቀደ፤ ልጁንም ጺጶራን ለሙሴ ሰጠው። 22 ወንድ ልጅም ወለደች፦ “በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ” ሲል ስሙን “ጌርሾም” ብሎ ጠራው። 23 ከብዙ ቀኖች በኋላ የግብጽ ንጉሥ ሞተ፤ የእስራኤልም ሕዝቦች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፥ ጮኹም፥ ስለባርነታቸውም የልመና ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። 24 እግዚአብሔርም የለቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፥ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አስታወሰ። 25 እግዚአብሔርም የእስራኤልን ሕዝቦች አየ፥ እግዚአብሔርም የደረሰባቸውን ነገር አወቀ። |