Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘፀአት 10 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


8. የአንበጣ መንጋ

1 ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ግባ እኔ ልቡንና የአገልጋዮቹን ልብ ያደነደንኩት በመካከላቸው ምልክቶቼን እንዳሳይ ነው።

2 ይህም በልጅህና በልጅ ልጅህ ጆሮ እንድትነግርና ግብፃውያንን እንዴት እንዳሞኘኋቸው፥ በመካከላቸው ያስቀመጥኩት ምልክቶቼም ጌታ እንደሆንኩ እንድታውቁ ነው።”

3 ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፥ እንዲህም አሉት፦ “የዕብራውያን አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘በፊቴ እራስህን ለማዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ።

4 ሕዝቤን ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን፥ እነሆ እኔ ነገ በአገርህ አንበጣዎችን አመጣለሁ፤

5 የምድሩንም ፊት ይሸፍኑታል፥ ማንም ምድሩን ማየት አይችልም፤ ከበረዶውም ተርፎ የቀረላችሁን ሁሉ ይበሉታል፥ ያደገላችሁንም በሜዳ ያለ ዛፍ ሁሉ ይበሉታል፤

6 ቤቶችህም የአገልጋዮችህም ቤቶች ሁሉ የግብጽንም ቤቶች ሁሉ ይሞሉታል፤ አባቶችህ የአባቶችህም አባቶች በምድር ላይ ከተቀመጡበት ቀን ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ እንደ እርሱ ያለ አላዩም።’” ተመልሶም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ።

7 የፈርዖንም አገልጋዮች፦ “ይህ ሰው እስከ መቼ ወጥመድ ይሆንብናል? ጌታ አምላካቸውን እንዲያገለግሉት ወንዶቹን ልቀቃቸው፥ ግብጽስ እንደ ጠፋች ገና አላወቅህምን?” አሉት።

8 ሙሴንና አሮንን ወደ ፈርዖን አመጡአቸው፦ “ሂዱ፥ ጌታ አምላካችሁን አገልግሉ፥ ነገር ግን የሚሄዱት እነማን ናቸው?” አላቸው።

9 ሙሴም፦ “ወጣቶቻችን፥ ሽማግሌዎቻችን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን፥ በጎቻችንና ከብቶቻችን ከእኛ ጋር ይሄዳሉ የጌታን በዓል እናደርጋለንና” አለ።

10 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ ከእናንተ ጋር ይሁን እናንተንና ልጆቻችሁን እለቅቃለሁ፥ ነገር ግን ክፉ ነገር በፊታችሁ እንደሚሆን ተመልከቱ።

11 እንዲህ አይሆንም፤ እናንተ ወንዶቹ ሂዱና ጌታን አገልግሉ፥ የጠየቃችሁት ይህንን ነውና።” ከፈርዖንም ፊት አባረሩአቸው።

12 ጌታም ሙሴን፦ “አንበጣዎቹ በግብጽ ምድር ላይ እንዲመጡ፥ ከበረዶውም የተረፈውን የምድርን ቡቃያ ሁሉ እንዲበሉ፥ እጅህን በግብጽ ምድር ላይ ዘርጋ” አለው።

13 ሙሴም በግብጽ ምድር ላይ በትሩን ዘረጋ፥ ጌታም የምሥራቅን ነፋስ ያን ቀን ሁሉ ሌሊቱን ሁሉ አመጣ፤ በነጋም ጊዜ የምሥራቁ ነፋስ አንበጣዎቹን አመጣ።

14 አንበጣዎችም በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ወጡ፥ በግብጽም አገር ሁሉ ላይ ተቀመጡ፤ እጅግም ብዙ ነበሩ፥ ይህንም የሚያህል አንበጣ በፊት አልነበረም፥ ወደፊትም ደግሞ እንደ እርሱ ያለ አይሆንም።

15 የምድሩንም ፊት ሸፈኑት ምድሪቱም ጨለመች፤ የአገሪቱን ቡቃያ ሁሉ በረዶውም የተወውን በዛፉ የነበረውን ፍሬ ሁሉ በሉ፤ ለምለም ነገር በዛፉ ላይም በቡቃያው ላይም በግብጽ ምድር ሁሉ አልቀረም።

16 ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በፍጥነት አስጠራና እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ አምላካችሁንና እናንተን በደልሁ፤

17 አሁን እንግዲህ አንድ ጊዜ ብቻ ኃጢአቴን ይቅር በሉኝ፥ ይህንን ሞት ከእኔ እንዲያነሣልኝ ብቻ ጌታ አምላካችሁን ለምኑልኝ።”

18 እርሱም ከፈርዖን ፊት ወጣ፥ ወደ ጌታም ፀለየ።

19 ጌታም ከምዕራብ ዐውሎ ነፋሱን መለሰ፥ አንበጣዎቹንም ወስዶ በኤርትራ ባሕር ውስጥ ጣላቸው፤ አንድ ስንኳ አንበጣ በግብጽ አገር አልቀረም።

20 ጌታም የፈርዖንን ልብ አጸና የእስራኤልንም ልጆች አልለቀቀም።


9. ጨለማ

21 ጌታም ሙሴን፦ “በግብጽ ምድር ላይ ጨለማ እንዲሆን፥ ማንም ሰው የሚያውቀው ጨለማ እንዲሆን እጅህን ወደ ሰማያት ዘርጋ” አለው።

22 ሙሴም እጁን ወደ ሰማያት ዘረጋ፥ በግብጽም ምድር ሁሉ ላይ ሦስት ቀን ፅኑ ጨለማ ሆነ፤

23 ማንም ወንድሙን አላየም፥ ሦስት ቀንም ሙሉ ማንም ከስፍራው አልተነሣም፤ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ግን በተቀመጡበት ስፍራ ብርሃን ነበራቸው።

24 ፈርዖንም ሙሴን ጠርቶ፦ “ሂዱ፥ ጌታን አገልግሉ፤ ነገር ግን በጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ተዉ፤ ልጆቻችሁም ከእናንተ ጋር ይሂዱ” አለው።

25 ሙሴም እንዲህ አለው፦ “አንተ ደግሞ ለጌታ አምላካችን የምንሠዋው መሥዋዕትንና የሚቃጠል መሥዋዕትን በእጃችን ትሰጠናለህ።

26 ከብቶቻችን ከእኛ ጋር ይሄዳሉ አንድ ሰኮናም አይቀርም፥ ጌታ አምላካችንን ለማገልገል ከእነርሱ እንወስዳለንና፤ ጌታን የምናገለግለው በምን እንደሆነ እዚያ እስክንደርስ አናውቅም።”

27 ጌታ ግን የፈርዖንን ልብ አጸና፥ ሊለቅቃቸውም አልወደደም።

28 ፈርዖንም፦ “ከእኔ ዘንድ ሂድ፤ ተጠንቀቅ፤ ፊቴን ባየህበት ቀን ትሞታለህና ፊቴን እንዳታይ” አለው።

29 ሙሴም፦ “እንደ ተናገረህ ይሁን፤ ፊትህን እንደገና አላይም” አለ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች