ዘፀአት 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)መግቢያ 1 ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብጽ የገቡት የእስራኤል ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፤ እያንዳንዳቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ገቡ። 2 ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊና ይሁዳ 3 ይሳኮር፥ ዛብሎንና ብንያም 4 ዳንና ንፍታሌም፥ ጋድና አሴር። 5 ከያዕቆብ ጉልበት የወጡት ሰዎች ሁሉ ሰባ ነፍሶች ነበሩ፤ ዮሴፍም አስቀድሞ በግብጽ ነበር። 6 ዮሴፍም ሞተ፥ ወንድሞቹም ሁሉ፥ ያም ትውልድ ሁሉ። 7 ነገር ግን የእስራኤል ትውልዶች ፍሬያማ ነበሩ፥ እጅግም በዙ፥ ተባዙም፥ እጅግም በረቱ፤ ምድሪቱም በእነርሱ ሞላች። በእስራኤላውያን ላይ የደረሰው ግፍ 8 ዮሴፍን የማያውቅ አዲስ ንጉሥ በግብጽ ተነሣ። 9 እርሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ የእስራኤል ሕዝብ ከእኛ ይልቅ በዝተዋል በርትተውማል፤ 10 እንዳይበዙ፥ ጦርነትም በተነሣብን ጊዜ ጠላቶቻችንን አግዘው እንዳይወጉን ከምድሪቱም እንዳይወጡ ኑ በጥበብ እንምከር።” 11 በብርቱ ሥራ እንዲያስጨንቁአቸው ግብር አስገባሪዎችን ሾመባቸው፤ ለፈርዖንም ፊቶምንና ራዓምሴስን የማከማቻ ከተሞች አድርገው ሠሩ። 12 ነገር ግን በጨቆኑአቸው መጠን እንዲሁ በዙ፥ እጅግም ሰፉ፤ ከዚህም የተነሣ እስራኤላውያንን ፈሩአቸው። 13 ግብፃውያንም እስራኤላውያንን በጭካኔ እንዲሠሩ አስገደዱአቸው። 14 በጽኑ ሥራ፥ በጭቃ በጡብም በእርሻም ሥራ ሁሉ፥ በመከራም በሚያሠሩአቸው ሥራ ሁሉ፥ ሕይወታቸውን አስመረሩት። 15 የግብጽም ንጉሥ የዕብራውያንን አዋላጆች አንዲቱ ሺፍራ ሁለተኛይቱም ፑአ የሚባሉትን እንዲህ አላቸው፦ 16 “የዕብራውያንን ሴቶች ስታዋልዱ፥ ለመውለድ እንደ ደረሱ ባያችሁ ጊዜ፥ ወንድ ከሆነ ግደሉት፤ ሴት ከሆነች ግን በሕይወት ትኑር።” 17 አዋላጆቹ ግን እግዚአብሔርን ፈሩ፥ የግብጽ ንጉሥም እንዳዘዛቸው አላደረጉም፥ ወንዶቹን ሕፃናትንም በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ተዋቸው። 18 የግብጽም ንጉስ አዋላጆቹን ጠርቶ፦ “ለምን ይህን አደረጋችሁ? ወንዶቹን ሕፃናትንስ ለምን በሕይወት እንዲኖሩ ፈቀዳችሁላቸው?” አላቸው። 19 አዋላጆቹም ፈርዖንን፦ “የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብጽ ሴቶች አይደሉም፤ እነርሱ ጠንካሮች ናቸውና አዋላጆች ሳይገቡ ስለሚወልዱ ነው” አሉት። 20 እግዚአብሔርም ለአዋላጆቹ መልካም ነገርን አደረገላቸው፤ ሕዝቡም በዛ፥ እጅግም ብርቱ ሆነ። 21 አዋላጆቹ እግዚአብሔርን ስለ ፈሩ ቤተሰብን ሰጣቸው። 22 ፈርዖንም፦ “የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ ወደ ዓባይ ወንዝ ጣሉት፥ ሴትን ልጅ ሁሉ ግን በሕይወት እንድትኖር ተዉአት” ብሎ ሕዝቡን ሁሉ አዘዘ። |