ዘዳግም 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የእስራኤል ሕዝብ ታዛዦች እንዲሆኑ ሙሴ መምከሩ 1 “አሁንም፥ እስራኤል ሆይ፥ እንድታደርጉአቸው በሕይወትም እንድትኖሩ፥ የአባቶቻችሁም አምላክ ጌታ ወደሚሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱ፥ የማስተምራችሁን ሥርዓትና ሕግጋት ስሙ። 2 እኔ ያዘዝኋችሁን የጌታ አምላካችሁን ትእዛዝ ትጠብቃላችሁ እንጂ ባዘዝኋችሁ ቃል ላይ አትጨምሩም፥ ከእርሱም አታጎድሉም። 3 የፌዖሩን ባዓልን የተከተሉትን ሰዎች ሁሉ ጌታ አምላካችሁ ከመካከላችሁ እንዳጠፋ፥ እግዚአብሔር በባዓል ፌዖር ያደረገውን ዐይኖቻችሁ አይተዋል። 4 እናንተ ግን ጌታ አምላካችሁን የተከተላችሁ ሁላችሁ እስከ ዛሬ ድረስ በሕይወት ትኖራላችሁ። 5 “እነሆ፥ እናንተ ገብታችሁ በምትወርሱአት ምድር ውስጥ እንዲህ እንድታደርጉ ጌታዬ አምላኬ እንዳዘዘኝ ሥርዓትንና ሕግጋትን አስተማርኋችሁ። 6 ጠብቁአት አድርጉአትም፥ ይህችን ሥርዓት ሁሉ ሰምተው፦ ‘በእውነት ይህ ታላቅ ሕዝብ ጠቢብና አስተዋይ ሕዝብ ነው’ በሚሉ በአሕዛብ ፊት ጥበባችሁና ማስተዋላችሁ ይህ ነውና። 7 “እኛ በምንለምነው ጊዜ ሁሉ ጌታ አምላካችን ለእኛ ቅርብ እንደ ሆነው፥ የየትኛው ሌላ ታላቅ ሕዝብ ነው አምላኩ ለእርሱ ቅርብ የሆነለት? 8 በዓይናችሁ ፊት ዛሬ እንዳኖርኩት እንደዚህ ሕግ ሁሉ ጽድቅ የሆነች ሥርዓትና ሕግጋት ያለው ታላቅ ሕዝብስ የት ይገኛል? 9 “ብቻ አስተውል፥ ነፍስህንም በትጋት ጠብቅ፤ ዐይኖችህ ያዩትን ነገር እንዳትረሳ፥ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ ከልብህ እንዳይለይ፥ ለልጆችህም ለልጅ ልጆችህም አሳውቃቸው። 10 በጌታ በአምላካችሁ ፊት በኮሬብ በቆማችሁበት ቀን፥ ጌታ፦ ‘ሕዝቡን ወደ እኔ ሰብስብ፥ በምድርም በሕይወት በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ እኔን መፍራት እንዲማሩ፥ ልጆቻቸውንም እንዲያስተምሩ፥ ቃሌን አሰማቸዋለሁ’ ብሎ በተናገረኝ ጊዜ፥ 11 እናንተም ቀርባችሁ ከተራራው በታች ቆማችሁ ነበር፥ እስከ ሰማይም ድረስ እሳት በተራራው ላይ ይነድድ ነበር፥ ጨለማም ደመናና ድቅድቅ ጨለማ ነበረ። 12 ጌታም በእሳት ውስጥ ሆኖ ተናገራችሁ፤ የቃሉን ድምፅ ሰማችሁ፥ ድምፅን ብቻ ነበር እንጂ መልክ አላያችሁም። 13 እንድታደርጉትም ያዘዛችሁን ቃል ኪዳኑን፥ ዓሥሩን ትእዛዝ፥ ገለጸላችሁ፤ በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይም ጻፋቸው። 14 ትወርሱአት ዘንድ ተሻግራችሁ በምትገቡባት ምድር የምታደርጉትን ሥርዓትና ሕግጋት እንዳስተምራችሁ ጌታ በዚያን ጊዜ አዘዘኝ። ከጣዖት አምልኮ ስለ መራቅ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ 15 “ጌታ በኮሬብ በእሳት ውስጥ ሆኖ በተናገራችሁ ጊዜ ምንም መልክ አላያችሁምና፥ ለነፍሳችሁ እጅግ ተጠንቀቁ፤ 16 የማናቸውንም መልክ በየትኛውም ምስል፥ በወንድ ይሁን በሴት መልክ፥ የተቀረጸውን ምስል ለራሳችሁ በማድረግ እንዳትረክሱ፥ 17 በምድር ላይ ያለውን የማንኛውንም እንስሳ ምስል በክንፉ የሚበርና የማንኛውንም ወፍ ምስል፥ 18 በምድርም ላይ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱትን፥ ከምድር በታች በውሃ ውስጥ የሚኖሩትን የዓሣ ሁሉ ምስል አታድርጉ። 19 ዐይኖችህን ወደ ሰማይ አንሥተህ፥ ጌታ አምላካችሁ ከሰማይ በታች ላሉት ሕዝቦች ሁሉ የሰጣቸውን፥ ፀሐይንና ጨረቃን ከዋክብትንም፥ የሰማይን ሠራዊት ሁሉ ባያችሁ ጊዜ፥ በመሳት እንዳትሰግዱላቸውና እንዳታመልኳቸው ተጠንቀቁ። 20 እናንተን ግን ጌታ ወስዶ፥ እንደ ዛሬው ሁሉ የርስቱ ሕዝብ እንድትሆኑለት፥ ከብረት እቶን ከግብጽ አውጥቷችኋል። 21 በእናንተ ቃላት ምክንያት ጌታ እኔን ተቆጣኝ፤ ዮርዳኖስንም እንዳልሻገር ጌታ አምላካችሁ ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ወደ መልካሚቱ ምድር እንዳልገባ ማለ። 22 እኔ በዚህች ምድር እሞታለሁና፥ ዮርዳኖስን አልሻገርም፥ እናንተ ግን ትሻገራላችሁ፥ ያችንም መልካሚቱን ምድር ትወርሳላችሁ። 23 ጌታ አምላካችሁ ከእናንተ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እንዳትረሱ፥ ጌታ አምላካችሁም የከለከለውን በማናቸውም መልክ የተቀረጸውን ምስል እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ። 24 ጌታ እግዚአብሔር የሚበላ እሳት፥ ቀናተኛ አምላክ ነውና። 25 “ልጆችን የልጅ ልጆችንም በወለዳችሁ ጊዜ፥ በምድሪቱም ብዙ ዘመን በተቀመጣችሁ ጊዜ፥ ማናቸውም ቅርጽ የተቀረጸውን ምስል አድርጋችሁ ከረከሳችሁ፥ ታስቆጡትም ዘንድ በጌታ በአምላካችሁ ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ከሠራችሁ፥ 26 ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ከምትገቡባት ምድር ፈጥናችሁ እንደምትጠፉ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በእናንተ ላይ ለምስክርነት እጠራለሁ፥ ፈጽሞም ትጠፋላችሁ እንጂ ረጅም ዘመን አትኖሩባትም። 27 ጌታም በአሕዛብ መካከል ይበትናችኋል፥ ጌታ በውስጣቸው በሚያኖራችሁ በአሕዛብ መካከልም ጥቂቶች ሆናችሁ ትቀራላችሁ። 28 በዚያም ማየትም ሆነ መስማት፥ መብላት ሆነ ማሽተት የማይችሉትን፥ በሰው እጅ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት ታመልካላችሁ። 29 ነገር ግን ከዚያ ጌታ አምላካችሁን ትሻላችሁ፥ በሙሉ ልባችሁ በሙሉ ነፍሳችሁም የፈለጋችሁት እንደሆን ታገኙታላችሁ፤ 30 ይህም ሁሉ በደረሰባችሁ ጊዜ፥ ስትጨነቁ፥ በዘመኑ ፍጻሜ ወደ አምላካችሁ ወደ ጌታ ትመለሳላችሁ፥ ቃሉንም ትሰማላችሁ። 31 ጌታ እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ነውና አይተዋችሁም፥ አያጠፋችሁምም፤ ለአባቶቻችሁ የገባውን ቃል ኪዳኑን አይረሳም። 32 “እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረው ጊዜ ጀምሮ፥ ከሰማይ ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ከቶ እንዲህ ያለ ታላቅ ነገር ወይም እንደ እርሱ ያለ ተሰምቶ እንደሆነ ከአንተ በፊት የነበረውን የቀደመውን ዘመን ጠይቅ። 33 እናንተን ከእሳት ውስጥ ሆኖ እንደ ተናገረው፥ የእግዚአብሔርን ድምፅ ሰምቶ በሕይወት መኖር የቻለ፥ ሌላ ሕዝብ ከቶ አለን? 34 ወይስ በፈተና፥ በተአምራት፥ በድንቅ፥ በጦርነት፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በሚያስፈራም ኃይል፥ በዐይናችሁ ፊት ጌታ አምላካችሁ እናንተን ከግብጽ ምድር እንዳወጣችሁ፥ አንድን ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ መካከል ወስዶ የራሱ ሕዝብ ለማድረግ የሞከረ ሌላ አምላክ አለን? 35 ጌታም አምላካችሁ እንደሆነ እንድታውቁ ይህ ለእናንተ ተገልጧል፥ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም። 36 ያስተምራችሁ ዘንድ ከሰማይ ድምፁን አሰማችሁ፥ በምድርም ላይ ታላቁን እሳቱን አሳያችሁ፥ ከእሳቱም መካከል የእርሱን ድምፅ ሰማችሁ።። 37 አባቶቻችሁን ወድዶአልና ከእነርሱ በኋላ ዘራቸውን መረጠ፥ ከእናንተ ጋር ሆኖ በታላቅ ኃይሉ ከግብጽ አወጣችሁ። 38 ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ፥ ከእናንተ የበረቱትን ታላላቆችን አሕዛብ በፊታችሁ እንዲያስወጣ፥ እናንተንም እንዲያስገባ፥ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ ይሰጣችሁ ዘንድ ነው። 39 እንግዲህ፥ ጌታ በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ እንደሆነ፥ ሌላም እንደሌለ ዛሬ እወቁ፥ በልባችሁም ያዙት። 40 ለእናንተ፥ ከእናንተም በኋላ ለልጆቻችሁ መልካም ይሆን ዘንድ፥ ጌታ አምላካችሁ ለዘለዓለም በሚሰጣችሁ ምድር ዕድሜአችሁ ይረዝም ዘንድ፥ እኔ ዛሬ የማዝዛችሁን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ጠብቁ።” ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የመማፀኛ ከተሞች 41 ከዚህ በኋላ ሙሴ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ በስተ ምሥራቅ ሦስት ከተሞች በመለየት ከለለ፤ 42 ይህንንም ማድረጉ ትናንት ከትናንት በስቲያም ከዚህ ቀድሞ ጠላትነት ሳይኖረው፥ ባልንጀራውን ሳያውቅ የገደለ፥ ገዳዩ ይሸሽባቸው ዘንድ፥ ከእነዚህም ከተሞች ወደ አንዲቱ ሸሽቶ በሕይወት እንዲኖር ነው። 43 ከተሞቹም ለሮቤል ነገድ በምድረ በዳ በደልዳላ ስፍራ ያለ ቤጼር፥ ለጋድም ነገድ በገለዓድ ያለ ራሞት፥ ለምናሴም ነገድ በባሳን ያለ ጎላን ነበሩ። ስለ ሕጉ የተሰጠ ማብራሪያ 44 ሙሴም በእስራኤል ልጆች ፊት ያኖራት ሕግ ይህች ናት። 45 ከግብጽ በወጡ ጊዜ ሙሴ ለእስራኤል ልጆች የተናገረው ምስክርና ሥርዓት፥ ሕጎችም እነዚህ ናቸው። 46 ሙሴና የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ከወጡ በኋላ ድል በነሱት፥ በሐሴቦን ተቀምጦ በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ምድር፥ በቤተፌዖር አንጻር ባለው ሸለቆ በዮርዳኖስ ማዶ ያወጃቸው። 47 እነርሱም የእርሱን ምድርና እንዲሁም በዮርዳኖስ ምሥራቅ የምትገኘውን ባሳንን ይገዛ የነበረውን የሌላውን አሞራዊ ንጉሥ የዖግን ምድር ወረሱ። 48 በአርኖን ወንዝ ዳር ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ እስከ ሲሪዮን ተራራ፥ ይህም ሔርሞን ድረስ፥ 49 በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ከፒስጋ ተራራ በታች ያለውን ዓረባ ሁሉ እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ ወሰዱ። |