ዘዳግም 33 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ሙሴ የእስራኤልን ነገድ ሁሉ እንደ ባረከ 1 የጌታ ሰው ሙሴ ከመሞቱ በፊት የእስራኤልን ሕዝብ የባረከበት ቃለ ቡራኬ ይህ ነው። 2 እንዲህም አለ፦ “ጌታ ከሲና ተራራ መጣ፥ በሴይርም እንደ ንጋት ተገለጠ፥ ከፋራን ተራራ አበራላቸው፥ በስተቀኙም ከእሳት ነበልባል ጋር፥ ከአእላፋት ቅዱሳኑም ጋር መጣ። 3 በእርግጥ ሕዝቡን ይወዳል፤ ቅዱሳኑ ሁሉ በእጁ ናቸው፤ እነርሱም በእግሮችህ ሥር ይሰግዳሉ፤ መመሪያህንም ከአንተ ይቀበላሉ። 4 ይህ ሙሴ የሰጠን ሕግ፥ የያዕቆብ ጉባኤ ርስት ነው። 5 የሕዝቡ አለቆች ከእስራኤል ነገዶች ጋር ሆነው፥ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ፥ እርሱ በይሹሩን ላይ ንጉሥ ነበር።” 6 “ሮቤል በሕይወት ይኑር፥ አይሙት፥ ሰዎቹም በቍጥር አይነሱ።” 7 ስለ ይሁዳም እንዲህም አለ፦ “ጌታ ሆይ፥ የይሁዳን ድምፅ ስማ፥ ወደ ወገኖቹም አምጣው። እጆቹንም አጠንክርለት፤ ከጠላቶቹ ጋር ሲዋጋም ረዳት ሁነው።” 8 ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፦ “ማሳህ በተባለው ቦታ ለፈተንኸው፥ በመሪባ ውኃም ለተከራከርኸው፥ ቱሚምህን ለሌዊ ስጠው፥ ኡሪምህም ለዚህ ቅዱስ ሰው ነው፤ 9 ለአንት ሲል እናቱንና አባቱን፥ ‘አላየሁም’ ላለ፥ ወንድሞቹንም ላላስተዋለ፥ ልጆቹንም ላላወቀ፥ ቃልህን ላከበረ፥ ቃል ኪዳንህንም ለጠበቀ። 10 ሥርዓትህን ለያዕቆብ፥ ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፥ በፊትህ ዕጣንን፥ በመሠዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባሉ። 11 ጌታ ሆይ፥ ሀብቱን ባርክ፥ የእጁንም ሥራ ተቀበል፤ የጠላቱን አከርካሪ ስበር፤ የሚጠሉትም ዳግመኛ አይነሡ።” 12 ስለ ብንያምም እንዲህ አለ፦ “በጌታ የተወደደ በእርሱ ዘንድ ተማምኖ ይኖራል፤ ቀኑን ሁሉ ይጠብቀዋል፤ በትከሻዎቹም መካከል ያርፋል።” 13 ስለ ዮሴፍም እንዲህ አለ፥ “ምድሩ ከጌታ ዘንድ የተባረከ ይሁን፤ ከሰማያት በሚዘንበው የላቀ ስጦታ፥ ከታችም ከጥልቀት ከሚገኘው ውሃ፥ 14 ከፀሐዩ ሙቀት ከሚገኘው ምርጥ ፍሬ፥ ከወራት መፈራረቅ ከሚገኘው ምርት፥ 15 ከቀደሙትም ከጥንት ተራሮች ከፍተኛነት፥ በዘለዓለሙም ኮረብቶች ገናንነት፥ 16 በምድሪቱም ገናንነትና ሞላዋ፥ በቁጥቋጦው ውስጥ ከነበረው በረከት በዮሴፍ ራስ ላይ፥ ከወንድሞቹም በተለየው ራስ አናት ላይ ይውረድ። 17 ለላሞች በኩር ግርማ ይሆናል፥ ቀንዶቹ አንድ ቀንድ እንዳለው ናቸው፥ በእነርሱ እስከ ምድር ዳርቻ ያሉትን አሕዛብ ሁሉ ይወጋል፥ የኤፍሬም እልፍ አእላፋት፥ የምናሴም አእላፋት እነርሱ ናቸው።” 18 ስለ ዛብሎን ስለ ይሳኮር ነገዶችም እንዲህ አለ፦ “ዛብሎን በመርከብ ስትጓዝ ደስ ይበልህ፤ ይሳኮርም በቤትህ ሆነህ ደስ ይበልህ። 19 የተሰወረውን የአሸዋውን መዝገብ፥ የባሕሩንም ባለጠግነት ይጠባሉና አሕዛብን ወደ ተራራው ይጠራሉ፥ በዚያ የጽድቅ መሥዋዕት ይሠዋሉ።” 20 ስለ ጋድም እንዲህ አለ፥ “ጋድን ሰፊ ያደረገ ቡሩክ ይሁን፥ እንደ አንበሳይቱ ዐርፎአል፥ ክንድንና ራስን ይቀጠቅጣል። 21 በዚያ የአለቃ እድል ፈንታ ቀርቶአልና የመጀመሪያውን ክፍል ለራሱ መረጠ፥ ወደ ሕዝብ አለቆችም መጣ፥ የጌታንም ጽድቅ፥ ፍርዱንም ከእስራኤል ጋር አደረገ።” 22 ስለ ዳንም እንዲህ አለ፥ “ዳን የአንበሳ ደቦል ነው፥ ከባሳን ዘልሎ ይወጣል።” 23 ስለ ንፍታሌምም እንዲህ አለ፦ “ንፍታሌም በሞገስ ጠግቧል፥ የጌታንም በረከት ተሞልቶአል፥ ባሕሩንና ደቡቡን ይወርሳል።” 24 ስለ አሴርም እንዲህ አለ፦ “አሴር በልጆች የተባረከ ይሁን፥ በወንድሞቹ የተወደደ ይሁን፥ እግሩንም በዘይት ውስጥ ያጥልቅ። 25 ጫማህ ብረትና ናስ ይሆናል፥ እንደ ዕድሜህ እንዲሁ ኃይልህ ይሆናል። 26 “ይሹሩን ሆይ፥ በሰማያት ላይ ለረድኤትህ፥ በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ እንደ ጌታ ያለ ማንም የለም። 27 መኖሪያህ የዘለዓለም አምላክ ነው፥ የዘለዓለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፥ ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ፦ አጥፋው ይላል። 28 እስራኤልም ተማምኖ፥ የያዕቆብም ምንጭ ብቻውን፥ እህልና የወይን ጠጅ ባለባት ምድር ይኖራል፥ ሰማያትም ጠልን ያንጠባጥባሉ። 29 እስራኤል ሆይ፥ ምስጉን ነህ፥ በጌታ የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማን ነው? እርሱ የረድኤትህ ጋሻ፥ የከፍተኛነትህም ሰይፍ ነው። ጠላቶችህም ይገዙልሃል፥ አንተም ከፍታቸውን ትረግጣለህ።” |