Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘዳግም 31 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የኢያሱ በሙሴ እግር መተካት

1 ሙሴም ወጥቶ እነዚህን ቃሎች ለእስራኤል ሁሉ ተናገረ፤

2 “እነሆ፤ መቶ ሃያ ዓመት ሆኖኛል፤ ከእንግዲህ ልወጣና ልገባ አልችልም፤ ጌታም ‘ዮርዳኖስን አትሻገርም’ ብሎኛል፤

3 ጌታ አምላክህም ራሱ በፊትህ ቀድሞ ይሄዳል፤ እነዚህንም አሕዛብ ከፊትህ ያጠፋቸዋል፤ አንተም ምድራቸውን ትወርሳለህ፤ ጌታ እንደ ተናገረው ኢያሱም አንተን ቀድሞ ይሻገራል።

4 ጌታ የአሞራውያንን ነገሥታት ሴዎንንና ዐግን ከነምድራቸው እንዳጠፋቸው እነዚህንም ያጠፋቸዋል።

5 ጌታ እነርሱን በፊታችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ያዘዝኳችሁን ሁሉ በእነርሱ ላይ ታደርጋላችሁ።

6 ብርቱና ደፋር ሁኑ፤ አትፍሯቸው ወይም አትደንግጡላቸው። ጌታ አምላክህም ካንተ ጋር ይሄዳልና፤ አይተውህም፤ አይጥልህምም።”

7 ከዚያም ሙሴ ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት እንዲህ አለው፤ “ጌታም ለአባቶቻቸው ሊሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ከዚህ ሕዝብ ጋር አብረህ ስለምትገባ፥ ምድሪቱን ርስታቸው አድርገህ ስለምታከፋፍል በርታ፤ ደፋርም ሁን።

8 ጌታ ራሱ በፊትህ ይሄዳል፤ ከአንተም ጋር ይሆናል፤ ፈጽሞ አይለይህም፤ አይተውህምም፤ አትፍራ፤ ተስፋም አትቁረጥ።”


ሕጉ በየሰባት ዓመት መነበብ እንዳለበት

9 ሙሴም ይህን ሕግ ጽፎ፥ የጌታን የኪዳን ታቦት ለሚሸከሙ ለሌዊ ልጆች፥ ለካህናቱና ለእስራኤል አለቆች ሁሉ ሰጠ።

10 ከዚያም በኋላ ሙሴ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ዕዳ በሚተውበት፥ የዳስ በዓልም በሚከበርበት፥ በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ፥

11 እስራኤል ሁሉ እርሱ በሚመርጠው ስፍራ በጌታህ በእግዚአብሔር ፊት ሲታይ ይህን ሕግ በእነርሱ ፊት በጆሮአቸው ታነበዋለህ።

12 ይሰሙና ጌታ አምላካችሁንም መፍራት ይማሩ ዘንድ፥ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ በጥንቃቄ እንዲከተሉ ሕዝቡን ይኸውም ወንዶችን፥ ሴቶችን፥ ልጆችንና በከተሞችህ የሚኖረውንም መጻተኛ ሰብስብ።

13 ዮርዳኖስን ተሻግረህ በምትወርሷት ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይህን ሕግ የማያውቁት ልጆቻቸውም መስማትና ጌታ አምላካችሁንም መፍራት ሊማሩ ይገባቸዋል።”


እግዚአብሔር ለሙሴና ለኢያሱ የሰጣቸው መመሪያ

14 ጌታ ሙሴን፥ “እነሆ የምትሞትበት ቀን ቀርቧል፤ ትእዛዝ እንድሰጠው ኢያሱን ጥራውና ወደ መገናኛው ድንኳን ቅረቡ።” ሙሴና ኢያሱም ሄዱ፤ ወደ መገናኛው ድንኳንም ቀረቡ።

15 ጌታም በድንኳኑ ላይ በደመና ዐምድ ተገለጠ፤ የደመናውም ዐምድ ከድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆመ።

16 ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ ከአባቶችህ ጋር ልታርፍ ነው፤ ይህም ሕዝብ በሚገባበት ምድር በሚገኙ ባዕዳን አማልክት ወዲያውኑ ያመነዝራል። እኔን ይተወኛል፤ ከእነርሱም ጋር የገባሁትን ኪዳን ያፈርሳሉ።

17 በዚያች ቀን እቀጣቸዋለሁ፤ እተዋቸዋለሁም፤ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይጠፋሉ። ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር ይደርስባቸዋል፤ በዚያችም ቀን፥ ‘ይህ ጥፋት የደረሰብን፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባለመሆኑ አይደለምን?’ ይላሉ።

18 ወደ ባዕዳን አማልክት በመዞር ከፈጸሙት ክፋታቸው የተነሣ፥ በዚያች ቀን ፊቴን ከእነርሱ ፈጽሞ እሰውራለሁ።

19 “እንግዲህ ይህን መዝሙር ለራሳችሁ ጻፉ፤ ለእስራኤል ልጆችም አስተምሩ፤ ስለ እኔ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ እንዲዘምሩ አድርጉ።

20 ወተትና ማር ወደምታፈሰውና ለአባቶቻቸው በመሐላ ቃል ወደ ገባሁላቸው ምድር ባመጣኋቸው ጊዜ ከበሉና ከጠገቡ፥ ከበለጸጉም በኋላ እኔን ንቀው ኪዳኔንም አፍርሰው ወደ ባዕዳን አማልክት ይዞራሉ፤ እነርሱንም ያመልካሉ።

21 ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር በደረሰባቸው ጊዜ ይህ መዝሙር ምስክር ይሆንባቸዋል። በዘራቸው የሚረሳ አይደለምና። ወደ ማልሁላቸው ምድር ሳላስገ ባቸው በፊት ምን ለማድረግ እንደሚያስቡ እንኳን አስቀድሜ ዐውቃለሁ።”

22 ስለዚህም ሙሴ ይህን መዝሙር በዚያች ቀን ጻፈ፤ ለእስራኤላውያንም አስተማራቸው።

23 ጌታም ለነዌ ልጅ ለኢያሱ፥ “በርታ፤ ደፋር ሁን፤ የእስራኤልን ልጆች በመሐላ ቃል ወደ ገባሁላቸው ምድር ታስገ ባቸዋለህና፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ” በማለት ትእዛዝ ሰጠው።

24 ሙሴ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የዚህን ሕግ ቃል በመጽሐፍ ጽፎ እንዳበቃ፥

25 የጌታን የኪዳን ታቦት የሚሸከሙ ሌዋውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤

26 “በእናንተ ላይ ምስክር ሆኖ በዚያ ይኖር ዘንድ በጌታ በእግዚአብሔር የኪዳን ታቦት አጠገብ አስቀምጡት፤ ይህም በእናንተ ላይ ምስክር ሆኖ በዚያ ይኖራል፤

27 እኔ ዓመፃችሁንና የአንገታችሁን ድንዳኔ አውቃለሁና፥ እኔም ዛሬ ከእናንተ ጋር ገና በሕይወት ሳለሁ እናንተ በጌታ ላይ ዐምፃችኋል፥ ይልቁንስ ከሞትሁ በኋላ እንዴት ይሆናል?

28 ይህን ቃል በጆሮአቸው እናገር ዘንድ፥ ሰማይንና ምድርንም አስመሰክርባቸው ዘንድ የነገዶቻችሁን ሽማግሌዎች ሁሉ አለቆቻችሁንም ሰብስቡልኝ፥

29 እኔ ከሞትሁ በኋላ ፈጽማችሁ እንደምትረክሱ፥ ካዘዝኋችሁም መንገድ ዘወር እንደምትሉ ዐውቃለሁና። በጌታ ፊት ክፉ ድርጊት ስለምትፈጽሙ፥ እጆቻችሁ በሠሯቸውም ነገሮች እርሱን ስለምታስቆጡት በሚመጡት ዘመናት ጥፋት ይደርስባችኋል።”


የሙሴ መዝሙር

30 ሙሴም የዚህን መዝሙር ቃል ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ፥ ለተሰበሰበው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በጆሮአቸው እንዲህ ሲል አሰማ፦

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች