ዘዳግም 21 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ገዳዩ ላልታወቀ ሰው ስለሚቀርብ ማስተስረያ 1 “አምላክህ ጌታ እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር አንድ ሰው ተገድሎ ሜዳ ላይ ቢገኝና ገዳዩም ማን እንደሆነ ባይታወቅ፥ 2 ሽማግሌዎችህና ዳኞችህ ወጥተው ሬሳው ወድቆ ከተገኘበት አንሥቶ በአቅራቢያው እስከሚገኙት ከተሞች ድረስ ያለውን ርቀት ይለኩ። 3 ከዚያም ሬሳው ወድቆ ከተገኘበት ስፍራ በጣም ቅርብ የሆነችው ከተማ ሽማግሌዎች ለሥራ ያልደረሰችና ቀንበር ያልተጫነባትን ጊደር ይውሰዱ፥ 4 ከዚያ በፊት ታርሶ ወይም ተዘርቶበት ወደ የማይታወቅ ወራጅ ውሃ ወዳለበት ሸለቆ ያምጡት። በዚያ ሸለቆም የጊደሪቱን አንገት ይስበሩት፤ 5 እንዲያገለግሉና በጌታ ስም እንዲባርኩ፥ በማንኛውም የክርክርና የጥቃት ጉዳዮች ሁሉ ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ፥ አምላክህ ጌታ መርጦአቸዋልና የሌዊ ልጆች ካህናቱ ወደ ፊት ይቅረቡ። 6 ከዚያም ሬሳው በተገኘበት አቅራቢያ ባለችው ከተማ የሚኖሩ ሽማግሌዎች ሁሉ፥ በሸለቆው ውስጥ፥ አንገቷ በተሰበረው ጊደር ላይ እጃቸውን ይታጠቡ። 7 እንዲህም ብለው ይናገሩ፦ ‘እጆቻችን ደም አላፈሰሱም፤ ድርጊቱ ሲፈጸምም ዐይኖቻችን አላዩም። 8 ጌታ ሆይ፤ ስለ ተቤዥኸው ሕዝብህ ስለ እስራኤል ብለህ ይህን ስርየት ተቀበል፤ ሕዝብህንም በፈሰሰው ንጹሕ ደም በደለኛ አታድርግ።’ ስለ ፈሰሰውም ደም ስርየት ይደረግላቸዋል። 9 አንተም በጌታ ፊት ቀና የሆነውን ስታደርግ፥ የንጹሑን ደም የማፍሰስ በደልን ከመካከልህ ታስወግዳለህ። ስለ የጦር ምርኮኛ ሴቶች 10 “ከጠላቶችህ ጋር ጦርነት ልትገጥም ወጥተህ አምላክህም ጌታ እነርሱን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶህ በማረክህ ጊዜ፥ 11 ከምርኮኞቹ መካከል መልከ መልካም ሴት አይተህ ብትማርክህ፥ ሚስትህ ልታደርጋት ትችላለህ። 12 ወደ ቤትህ ውሰዳት፤ ጠጉሯን ትላጭ፤ ጥፍሯንም ትቆረጥ። 13 ስትማረክ የለበሰችውንም ልብስ ታውልቅ፤ እቤትህ ተቀምጣ ለአባትና ለእናቷ ወር ሙሉ ካለቀሰችላቸው በኋላ፥ ልትደርስባትና ባል ልትሆናት፥ እርሷም ሚስት ልትሆንህ ትችላለች። 14 በእርሷ ደስተኛ ባትሆን፥ ወደምትፈልገው እንድትሄድ ነጻነት ስጣት፤ ውርደት ላይ ጥለሃታልና አትሽጣት ወይም እንደ ባርያ አትቁጠራት። የበኲር ልጅ መብት 15 “አንድ ሰው ሁለት ሚስቶች ቢኖሩት፤ አንደኛዋን የሚወዳት፥ ሌላዋን ግን የሚጠላት ቢሆን፥ ሁለቱም ወንዶች ልጆችን ወልደውለት በኩር ልጁ ግን የተወለደው ከማይወዳት ሚስቱ ቢሆን፥ 16 ንብረቱን ለልጆቹ በሚያወርስበት ጊዜ፥ የብኩርናን መብት ከማይወዳት ሚስቱ ከወለደው በኩር ልጅ ገፎ፥ ከሚወዳት ሚስቱ ለተወለደው ልጁ፥ በአድልዎ መስጠት አይገባውም፤ 17 ይልቁንም ከተጠላችው ሚስቱ ለተወለደው ልጅ ካለው ሀብት ሁሉ ሁለት እጅ ድርሻውን በመስጠት ብኩርናውን ያስታውቅ፤ ያ ልጅ የአባቱ ኃይል መጀመሪያ ነውና፤ የብኩርና መብት የእርሱ ነው። ስለማይታዘዙ ልጆች 18 “አንድ ሰው፥ የአባቱን ወይም የእናቱን ትእዛዝ የማይሰማ፥ ቢቀጡትም የማይታረም እልከኛና ዓመፀኛ ልጅ ቢኖረው፥ 19 አባትና እናቱ ይዘው በሚኖሩበት ከተማ በር ወዳሉት አለቆች ያምጡት፤ 20 ‘ይህ ልጃችን እልከኛና ዓመፀኛ ነው፤ አይታዘዘንም፤ አባካኝና ሰካራም ነው’ ብለው ለአለቆች ይንገሯቸው። 21 ከዚያም በኋላ የከተማዪቱ ሰዎች ሁሉ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩት፤ ክፉውንም ከመካከልህ አስወግድ፤ እስራኤልም ሁሉ ይህን ሰምቶ ይፈራል። ልዩ ልዩ ሕጎች 22 “አንደ ሰው ለሞት የሚያበቃ በደል ፈጽሞ ቢገደልና በድኑ በዕንጨት ላይ ቢሰቀል፤ 23 በድኑን በዕንጨት ላይ እንደ ተሰቀለ አታሳድረው፤ ምክንያቱም በዕንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና፤ አምላክህ ጌታ ርስት አድርጎ የሚሰጥህን ምድር እንዳታረክስ በዚያኑ ዕለት ቅበረው።” |