ዘዳግም 10 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ሙሴ ዐሥርቱን ትእዛዛት እንደገና መቀበሉ 1 በዚያን ጊዜ ጌታ እንዲህ አለኝ፥ “እንደ ቀድሞ ዓይነት ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠርበህ ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፥ ለአንተም የእንጨት ታቦት ሥራ። 2 በሰበርሃቸውም በቀድሞዎቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች በእነዚህ ጽላቶች እጽፋለሁ፥ በታቦቱም ውስጥ ታደርጋቸዋለህ።” 3 “እኔም ከግራር እንጨት ታቦትን ሠራሁ፥ እንደ ቀድሞዎቹም ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠረብሁ፥ ሁለቱንም ጽላቶች በእጄ ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ። 4 ዐሥርቱን ቃላት ጌታ በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገራችሁ ተሰብስባችሁበት በነበረበት ቀን፥ ቀድሞ ተጽፈው እንደነበረው በጽላቶቹ ላይ ጻፈ፥ እነርሱንም ጌታ ለእኔ ሰጠኝ። 5 ተመልሼም ከተራራው ወረድሁ፥ ጽላቶችንም በሠራሁት ታቦት ውስጥ አደረግኋቸው፥ ጌታም እንዳዘዘኝ በዚያ ይገኛሉ።” 6 እስራኤላዊያንም ከብኤሮት ብኔያዕቃን ወደ ሞሴራ ተጓዙ፤ አሮንም እዚያ ሞቶ፥ እዚያው ተቀበረ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ አልዓዛር ካህን ሆነ። 7 ከዚያም ወደ ጉድጎዳ ተጓዙ፥ ከጉድጎዳም ወደ ውኃ ፈሳሾች ምድር ወደ ዮጥባታ ተጓዙ። 8 በዚያን ጊዜ የጌታን ቃል ኪዳን ታቦት እንዲሸከም፥ እርሱንም ለማገልገል በጌታ ፊት እንዲቆም፥ በስሙም እንዲባርክ ጌታ እስከ ዛሬ ድረስ የሌዊን ነገድ ለየ። 9 ስለዚህ ለሌዊ ከወንድሞቹ ጋር ክፍልና ርስት የለውም፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ጌታ ርስቱ ነው። 10 “እኔም፥ ከዚህ ቀደም እንዳደረኩት፥ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በተራራው ላይ ተቀመጥሁ፥ በዚህም ጊዜ ጌታ ደግሞ ሰማኝ፤ ጌታ ሊያጠፋህ አልወደደም። 11 ጌታም እንዲህ አለኝ፦ ‘ተነሥ፥ ለአባቶቻቸውም ልሰጣቸው ወደ ማልሁላቸው ምድር እንዲገቡ እንዲወርሱአትም፥ ሕዝቡን ምራ።’” የሕጉ ምንነት 12 “እስራኤል ሆይ፥ አሁንስ ጌታ አምላክህ ከአንተ የሚፈልገው ምንድነው? ነገር ግን ጌታ እግዚአብሔርን እንድትፈራው፥ በመንገዱም ሁሉ እንድትሄድ፥ ጌታ አምላክህንም እንድትወደው፥ በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ እንድታመልከው፥ 13 መልካም እንዲሆንልህ ዛሬ ለአንተ የማዝዘውን የጌታን ትእዛዝና ሥርዓት እንድትጠብቅ ነው። 14 እነሆ፥ ሰማይ ሰማየ ሰማያትም፥ ምድርም በእርሷም ያለው ሁሉ የጌታ የአምላክህ ነው። 15 ብቻ ጌታ ስለ አባቶችህ ደስ ብሎታል፥ እነርሱንም ወድዶአል፥ ከእነርሱም በኋላ እናንተን ዘራቸውን እንደ ዛሬው ሁሉ ከአሕዛብ ሁሉ መካከል መረጠ። 16 እንግዲህ እናንተ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ፥ ከእንግዲህ ወዲህም አንገተ ደንዳና አትሁኑ። 17 ምክንያቱም ጌታ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ፥ የጌቶችም ጌታ፥ ታላቅ አምላክ፥ ኃያልም፥ የሚያስፈራም፥ በፍርድ የማያደላ፥ ጉቦም የማይቀበል ነው። 18 ወላጁን ላጣና ለመበለቲቱ ይፈርዳል፥ ስደተኛውንም ስለሚወድ ምግብና ልብስ ይሰጠዋል። 19 ስለዚህ፥ እናንተ በግብጽ አገር ስደተኞች ነበራችሁና፥ ስደተኛውን ውደዱ። 20 ጌታ እግዚአብሔርን ፍራ፥ እርሱንም አምልክ፥ ከእርሱም አትነጠል፥ በስሙም ማል። 21 ዐይኖችህ ያዩትን እነዚህን ታላላቅና የሚያስፈሩ ነገሮችን ያደረገልህ እርሱ ክብርህ ነው፥ እርሱ አምላክህ ነው። 22 አባቶችህ ሰባ ሰው ሆነው ወደ ግብጽ ወረዱ፤ አሁን ግን ጌታ አምላክህ ብዛትህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አደረገ።” |