Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ባሮክ 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 የእስራኤል አምላክ ሁሉን ቻይ ጌታ ሆይ! በጭንቅ የተያዘች ነፍስና በድካም የተጨነቀ መንፈስ ወዳንተ ይጣራሉ፤

2 ጌታ ሆይ ስማ፥ ይቅርም በለን፥ በአንተ ፊት በድለናልና፤

3 አንተ ለዘለዓለም የምትነግሥ ነህ፤ እኛም ለዘለዓለሙ የምንጠፋ ነን።

4 የእስራኤል አምላክ ሁሉን ቻይ ጌታ ሆይ! የእስራኤልን ሙታን፥ በፊትህ የበደሉ ሰዎች የልጆቻቸውን ጸሎታቸውን ስማ፤ የአምላካቸውን የጌታን ቃል አልሰሙም፥ ስለዚህ መቅሰፍቶች ተጣበቁብን።

5 የአባቶቻችን ክፋት አታስታውስ፤ ነገር ግን በዚህ ጊዜ ኃይልህንና ስምህን አስታውስ።

6 አንተ ጌታ አምላካችን ነህና፥ ጌታ ሆይ የምናመሰግነውም አንተን ነው።

7 ስለዚህም ነው ስምህን እንድንጠራ አንተን መፍራት በልባችን ውስጥ ያሳደርኸው፤ በስደት ላይ ሆነን እናመስግንሃለን፥ በአንተ ላይ የበደሉትን የአባቶቻችንን ክፋት ሁሉ ከልባችን አርቀናልና።

8 ጌታ አምላካችን በተውት በአባቶቻችን ክፋት ምክንያት ስድብ፥ እርግማንና ቅጣት ሆነን እነሆ እኛ ዛሬ አንተ በበተንኸን በምርኮ ላይ ነን።


ጥበብ፥ የእስራኤል ሥልጣን

9 እስራኤል ሆይ የሕይወትን ትእዛዝ ስማ፤ ጆሮን ስጥ፥ ጥበብንም ተማር።

10 ለምን እስራኤል ሆይ፥ በጠላት ምድር የተገኘኸው፥ በሰው አገር ያረጀኸው፥ ከሞቱት ጋር የረከስኸው፥

11 በሲኦል ካሉት ጋር የተቆጠርኸው ለምንድን ነው?

12 የጥበብን ምንጭ ተውህ።

13 በእግዚአብሔር መንገድ ሄደህ ቢሆን ኖሮ ለዘለዓለም በሰላም በኖርህ ነበር።

14 ጥበብ የት እንዳለ፥ ኃይል የት እንዳለ፥ ማስተዋል የት እንዳለ ተማር፤ እንዲሁም የዘመን ርዝመት፥ ሕይወት፥ የዐይን ብርሃንና ሰላም የት እንዳለ እንድታውቅ ተማር።

15 ቦታዋን ማን አገኘ? ወደ መዛግብትዋስ ማን ገባ?

16 የአሕዛብ ገዢዎች የት አሉ? የምድር አውሬዎች ጌቶችስ የት ናቸው?

17 በሰማይ ወፎች የሚቀልዱ ሰዎች የት ናቸው? ሰዎች እምነታቸውን የጣሉባቸው ብርና ወርቅ ያከማቹ፥ ሀብቶቻቸው መጠን ያልነበረው እነዚያ ሰዎች የት አሉ?

18 ብር የሚያቀልጡና ሐሳቦቻቸው ሁሉ በብር ላይ የነበረ እነዚያ ሰዎች የት ናቸው? ሥራቸው ከሰው ሐሳብ በላይ የነበረ፥ እነዚያ ሰዎች የት ናቸው?

19 ሁሉም ጠፍተዋል፥ ወደ ሲኦልም ወርደዋል፥ በእነሱ ፈንታ ሌሎች ተነስተዋል።

20 ወጣቶች ብርሃን አይተው በምድር ላይ ኖረዋል፤ የዕውቀትን መንገድ ግን አላወቁም።

21 መንገድዋንም አላስተዋሉም፥ አልያዙአትምም፤ ልጆቻቸውም ከመንገድዋ ርቀዋል።

22 በከነዓንም አልተሰማችም፤ በቴማንም አልታየችም።

23 በምድር ላይ ማስተዋልን የሚፈልጉ የአጋር ልጆች፥ የሜራንና የቴማን ነጋዴዎች፥ የተረት የሚነግሩና ማስተዋልን የሚፈልጉ የጥበብን መንገድ አላወቁም፤ መንገዶቿን አላስታወሱም።

24 እስራኤል ሆይ እግዚአብሔር ቤት እንዴት ታላቅ ነው! የግዛቱ መጠን እንዴት ሰፊ ነው፤

25 ትልቅ ነው መጨረሻም የለው፤ ከፍ ያለና የማይለካ ነው።

26 ከጥንት ጀምሮ የታወቁ፥ ቁመታቸው ረጅም የሆነ፥ ጦርነትንም የሚያውቁ፥ ግዙፎቹ የተወለዱት እዚያ ነው።

27 እግዚአብሔር እነርሱን አልመረጣቸውም፤ የዕውቀትንም መንገድ አልሰጣቸውም።

28 ማስተዋል አልነበራቸውምና ጠፉ፤ በሞኝነታቸው ጠፉ።

29 ወደ ሰማይ ሄዶ የወሰዳት፥ ከደመናዎቹም ያወረዳት ማነው?

30 ባሕሩን አቋርጦ ሄዶ ያገኛት፥ በተመረጠ ወርቅስ ያመጣት ማነው?

31 ወደ እርሷ የሚወስደውን መንገድ ማንም አያውቀውም፥ ወደ እርሷ ስለሚወስደው መንገድም መገንዘብ የሚችል ማንም የለም።

32 ነገር ግን ሁሉን ነገር የሚያውቅ ሰው ያውቃታል፥ በማስተዋሉም አገኛት። ምድርን ለዘለዓለም ያዘጋጀ በአራት እግር አራዊት ሞልቷታል፤

33 ብርሃንን ይልካል፥ እርሱም ይሄዳል፤ ይጠራዋል፥ በመንቀጥቀጥም ይታዘዘዋል።

34 ከዋክብትም በመጠበቂያቸው ሆነው ያበራሉ፥ ሐሴትም ያደርጋሉ።

35 ሲጠራቸው “እዚህ አለን” አሉ፤ ለፈጠራቸውም በደስታ አበሩ።

36 አምላካችን ይህ ነው፤ ከእሱ ጋር መወዳደር የሚችል ከቶ የለም።

37 የዕውቀትን መንገድ ሁሉ አገኛት። እርሷንም ለአገልጋዩ ለያዕቆብ፥ ለሚወደውም ለእስራኤል ሰጠው።

38 ከዚህ በኋላ በምድር ላይ ታየች፤ በሰዎች መካከልም ኖረች።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች