Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ባሮክ 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ስለዚህ ጌታ በእኛ ላይና እስራኤልን ያስተደድሩ በነበሩት ዳኞች ላይ፥ በንጉሦቻችን ላይ፥ በገዢዎቻችን ላይ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ሰዎች ላይ ተናግሮት የነበረውን ፍርድ ፈጸመ።

2 በሙሴ ሕግ ላይ በተጻፈው መሠረት በኢየሩሳሌም እንዳደረገው ከሰማይ በታች በየትም አልተደረገም።

3 አንዳንዱ ሰው የወንድ ልጁን ሥጋ ሌላው ሰው የሴት ልጁን ሥጋ በላ፤

4 ጌታ እነርሱን በበተነበት በዙሪያቸው በሚገኙት ሕዝቦች ሁሉ መካከል ለውርደትና ለመከራ እንዲሆኑ በዙሪያችን ባሉ መንግሥታት ሁሉ እንዲገዙ አሳልፎ ሰጣቸው።

5 ድምጹን ባለመስማት ጌታ አምላካችንን ስለበደለን ዝቅ ተደረጉ፥ ክፍም አላሉም።

6 ጽድቅ የጌታ የአምላካችን ነው፤ በእኛና በአባቶቻችን ግን እንደ ዛሬው ቀን የፊት ኀፍረት ነው።

7 እነዚያ ጌታ በእኛ ላይ እንደሚደርሱ የነገረን መከራዎች ሁሉ ደረሱብን።

8 ሆኖም እያንዳንዳችንን ከመጥፎ ልባችን ሐሳብ ለመመለስ የጌታን ፊት አልለመንንም።

9 ጌታ መከራዎቹን ጠብቆ አቆያቸው፥ ጌታም በእኛ ላይ አመጣቸው፥ እንድናደርገው ባዘዘን ነገር ሁሉ ጌታ እውነተኛ ነውና፤

10 ነገር ግን በፊታችን ባስቀመጣቸው በጌታ ትእዛዞች መሠረት እንድንሄድ የተናገረንን ድምጹን አልሰማንም።

11 አሁንም ሕዝብህን ከግብጽ ምድር በብርቱ እጅ፥ በተአምራትና በድንቅ ነገሮች፥ በታላቅ ኃይልና በተዘረጋ ክንድ ያወጣህ፥ እስከ ዛሬም ድረስ ያለ ስምን ያደረግህ የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ፤

12 ኃጢአትን ሠርተናል፥ ክፉ ሰዎች ሆነናል፥ ስህተት ሰርተናል፥ ጌታ አምላካችን ሆይ ትእዛዞችህን ሁሉ አፍርሰናል።

13 እኛን በበታተንህበት አገሮች መካከል በቍጥር ጥቂት ሆነን ተጥለናልና መዓትህ ከእኛ ወዲያ ይራቅ።

14 ጌታ ሆይ ጸሎታችንንና ልመናችንን ስማ፤ ስለ ራስህ ስትል አድነን፥ በማረኩን ሰዎች ፊት ሞገስን ስጠን፤

15 በዚህ ዓይነት ምድር ሁሉ አንተ ጌታ አምላካችን መሆንህን ትወቅ፤ እስራኤልና ዘሩ በአንተ ስም ተጠርቶአልና።

16 ጌታ ሆይ ከቅዱስ ማደሪያህ ላይ ሆነህ ተመልከት፥ እኛንም አስበን፤ ጌታ ሆይ ጆሮህን አዘንብል፥ ስማ።

17 ጌታ ሆይ ዐይኖችህን ክፈትና እይ፥ በሲኦል የሚገኙ ሙታን፥ መንፈሳቸው ከሥጋቸው የተወሰደባቸው፥ ክብርን ወይም ተገቢውን ነገር ለጌታ አይሰጡም፤

18 ነገር ግን በጣም ያዘነች ነፍስ፥ አጎንብሳ የምትሄድና አቅም ያነሳት፥ የፈዘዙ ዐይኖችና የተራበች ነፍስ፥ ክብርን ወይም ተገቢውን ነገር ለጌታ ይሰጣሉ።

19 ጌታ አምላካችን ሆይ በፊትህ የምሕረት ጸሎት የምናቀርበው በአባቶቻችንና በንጉሦቻችን በሰሩት የጽድቅ ሥራ አይደለም፤

20 በአገልጋዮችህ በነቢያት አማካይነት እንደተናገርህ፥ መዓትህንና ቁጣህን በእኛ ላይ ላክህ፤ እንዲህም አልህ፦

21 ጌታ እንዲህ ይላል፥ ትከሻችሁን ዝቅ አድርጉ፥ የባቢሎንን ንጉሥንም አገልግሉ፤ ለአባቶቻችሁ በሰጠኋት ምድርም ትቀመጣችሁ፤

22 ነገር ግን ለጌታ ድምጽ የማትታዘዙ ከሆነ፥ የባቢሎንንም ንጉሥ የማታገለግሉ ከሆነ፤

23 የሣቅና የደስታ ድምጽ፥ የሙሽራና የሙሽሪት ድምጽ ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም እንዲቋረጥ አደርጋለሁ፥ ምድሪቱ በሙሉ ነዋሪዎች የሌሉበት በረሀ ትሆናለች።

24 ነገር ግን የባቢሎን ንጉሥ ለማገልገል ድምጽህን አልሰማም፤ የንጉሦቻችን ዐፅሞችና የአባቶቻችን ዐፅሞች ከቦታቸው እንደሚወጡ በአገልጋዮችህ በነቢያት እጅ የተናገርኸው ቃል ፈጸምከው።

25 እነሆ በቀን ሐሩርና በሌሊት ውርጭ ላይ ተጥለዋል፤ እነሱም በረሀብ፥ በሰይፍና በቸነፈር ክፉ ሞትን ሞቱ።

26 በእስራኤል ቤትና በይሁዳ ቤት ክፋት ምክንያት ስምህ የተጠራበትን ቤት ዛሬ በሚታይበት ሁኔታ ላይ ጣልኸው።

27 ሆኖም ጌታ አምላካችን ሆይ እንደ ደግነትህ ሁሉና እንደ ታላቁ ርህራሄህ ሁሉ አደረግህልን፥

28 በእስራኤል ልጆች ፊት ሕግህን እንዲጽፍ ባዘዝኸው ቀን፥ በአገልጋይህ በሙሴ እንዲህ ስትል እንደ ተናገርኸው ነው፥

29 “ድምጼን የማትሰሙ ከሆነ፥ ይህ በጣም ብዙ ሕዝብ በምበትናቸው አገሮች መካከል ወደ ጥቂት ቍጥር ይመለሳል።

30 አንገተ ደንዳና ሕዝብ ሰለሆኑ እንደማይሰሙኝ ኣውቃለሁና፤ ነገር ግን በተሰደዱበትም ምድር ወደ ልባቸው ይመለሳሉ፥

31 እኔም ጌታ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ የሚታዘዝ ልብና የሚሰሙ ጆሮዎችን እሰጣቸዋለሁ፤

32 በተሰደዱበት ምድር ያመሰግኑኛል፥ ስሜንም ያስታውሳሉ፤

33 ከእልኸኝነታቸውና ከክፉ ሥራቸው ይመለሳሉ፤ በጌታ ፊት የበደሉ የአባቶቻቸውን መንገድ ያስባሉ።

34 ለአባቶቻቸውም ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ እሰጣችኋለሁ ብዬ ወደ ማልሁላቸው ምድር አመጣቸዋለሁ፥ ይገዙአታልም፤ አበዛቸዋለሁ፤ በቍጥር ም አይቀንሱም።

35 አምላካቸው ለመሆን የዘለዓለም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር እገባለሁ፥ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ፤ ሕዝቤ እስራኤልን ከስጠኋቸው ምድር ዳግም አላወጣቸውም።”

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች