Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ባሮክ 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ባሮክና አይሁዳውያን በባቢሎን

1 የሂልቅያ ልጅ፥ የሃሳዲያ ልጅ፥ ሴዴቅያ ልጅ፥ ማህሴያ ልጅ፥ የኔሪያ ልጅ ባሮክ በባቢሎን የጻፈው የመጽሐፉ ቃል ይህ ነው፤

2 በአምስተኛው ዓመት ከወሩ በሰባተኛው ቀን ከለዳውያን ኢየሩሳሌምን በያዙአትና በእሳት በአቃጠሉአት ጊዜ፤

3 ባሮክ የዚህን መጽሐፍ ቃል ለይሁዳ ንጉሥ ለኢኮንያን ልጅ ለኢዮአቄምና መጽሐፉን ለመስማት ለመጣው ሕዝብ አነበበው፤

4 ባለ ሥልጣኖች፥ ለመሳፍንት፥ ለሽማግሌዎች፥ ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ በባቢሎን በሱድ ወንዝ አጠገብ ለሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ አነበበ።

5 በዚህን ጊዜ አለቀሱ፥ ጾሙ፥ በጌታም ፊት ጸለዩ።

6 እያንዳንዱ መስጠት እንደሚችለው መጠን ገንዘብ ሰበሰቡ፤

7 እርሱንም ወደ ሻሉም ልጅ፥ ወደ ሂልቅያ ልጅ፥ ወደ ሊቃ ካህኑ ኢዮአቄም፥ ወደ ካህናቱ፥ በኢየሩሳሌም ከእርሱ ወደነበሩት ወደ ሕዝቡ ሁሉ ላኩት።

8 በዚያው ጊዜ፥ በሲቫን ወር በዐሥረኛው ቀን፥ ከቤተ መቅደስ ተወስደው የነበሩትን የጌታን ቤት ዕቃዎች ወደ ይሁዳ ምድር ለመመለስ ወሰዳቸው፤ እነዚህ የብር ዕቃዎች የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያ የሠራቸው ነበሩ፤

9 ኢዮአቴም የሠራቸውም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢየንያንን ማርኮ እንዲሁም ሹማምንቱን፥ ምርኮኞቹን፥ ባለሥልጣኖቹንና የአገሩን ሕዝብ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ከወሰደ በኋላ ነው።


ወደ ኢየሩሳሌም የተላከ ደብዳቤ

10 እንዲህም አሉ፦ “እነሆ ገንዘብ ልከንላችኋል፤ ስለዚህ በገንዘቡ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኃጢአት መሥዋዕት፥ ዕጣን ግዙ፥ የእህል መሥዋዕት አዘጋጁ፤ በጌታ በአምላካችን መሠዊያ ላይ አቅርቡት፤

11 የምድር ቀኖቻቸው እንደ ሰማይ ቀኖች ረጅም እንዲሆኑላቸው፥ ስለ ባቢሎን ንጉሥ ስለ ናቡከደነፆር ሕይወትና ስለ ልጁ ሰለ ብልጣሶር ሕይወት ጸልዩ።

12 ጌታ ኃይል ይሰጠናል፥ ብርሃንም ዐይኖቻችን። በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር ጥላ ሥርና በልጁ በብልጣሶር ጥላ ሥር እንኖራለን፥ ብዙ ቀኖችም እናገለግላቸዋለን፥ በፊታቸውም ሞገስን እናገኛለን።

13 እኛ በጌታ በአምላካችን ላይ ኃጢአትን ሰርተናልና፥ እስከዚችም ቀን ድረስ የጌታ መዓቱና ቁጣው ከኛ አልራቀምና ወደ ጌታ ወደ አምላካችን ጸልዩልን።

14 በበዓል ቀኖችና በተመደቡ ቀኖችና ንስሐችሁን በጌታ ቤት ለማድረግ ይህንን የምንልክላችሁን መጽሐፍ አንብቡ።”


የኃጢአት ንስሐ

15 እንዲህም በሉ፤ ጽድቅ የጌታ የአምላካችን ነው፥ ነገር ግን ዛሬ በእኛ ላይ የፊት ኅፍረት ነው፥ እንዲሁም በይሁዳ ሰዎች፥ በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች፥

16 ለንጉሦቻችን፥ ለገዢዎቻችን፥ ለካህኖቻችን፥ ለነብዮቻችን፥ ለአባቶቻችን የፊት ኅፍረት ነው፥

17 ምክንያቱም በጌታ ፊት በድለናልና፤

18 አልታዘዝነውም፥ የጌታ የአምላካችንን ድምጽ አልሰማንም፥ በፊታችን ባስቀመጣቸው በጌታ ትእዛዞች መሠረት አልሄድንምና፤

19 ጌታ አባቶቻችንን ከግብጽ ምድር ከአወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለጌታ አምላካችንን አልታዘዝነውም፥ ድምጹንም ባለመስማት ቸልተኞች ሆነናል።

20 ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ሊሰጠን አባቶቻችንን ከግብጽ ምድር በአወጣበት ቀን ጌታ ለባርያው በሙሴ ያዘዘው ክፉ ነገርና መርገም እስከ ዛሬ ጸንቶብናል።

21 ወደ እኛ በላካቸው በነቢያት ቃል በኩል የጌታ አምላካችንን ቃል አልሰማንም።

22 ነገር ግን ሌሎች አማልክትን በማገልገል፥ በጌታ አምላካችን ፊት ክፉውን ሁሉ በማድረግ፥ እያንዳንዳችን የገዛ ልባችንን ክፉ ሐሳብ ተከተልን።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች