ሐዋርያት ሥራ 23 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ጳውሎስም ሸንጎውን ትኩር ብሎ ተመልክቶ “ወንድሞች ሆይ! እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኖሬአለሁ፤” አለ። 2 ሊቀ ካህናቱም ሐናንያ አፉን ይመቱት ዘንድ በአጠገቡ ቆመው የነበሩትን አዘዘ። 3 በዚያን ጊዜ ጳውሎስ “አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳ! እግዚአብሔር አንተን ይመታ ዘንድ አለው፤ አንተ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዛለህን?” አለው። 4 በአጠገቡ የቆሙትም “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን?” አሉት። 5 ጳውሎስም “ወንድሞች ሆይ! ሊቀ ካህናት መሆኑን ባላውቅ ነው፤ ‘በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ ቃል አትናገር፤’ ተብሎ ተጽፎአልና፤” አላቸው። 6 ጳውሎስ ግን እኩሌቶቹ ሰዱቃውያን እኩሌቶቹም ፈሪሳውያን መሆናቸውን አይቶ “ወንድሞች ሆይ! እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊም ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣት ይፈርዱብኛል፤” ብሎ በሸንጎው ጮኸ። 7 ይህንም ባለ ጊዜ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጥል ሆነ፤ ሸንጎውም ተለያየ። 8 ሰዱቃውያን “ትንሣኤም መልአክም መንፈስም የለም፤” የሚሉ ናቸውና፤ ፈሪሳውያን ግን ሁለቱን ያምናሉ። 9 ታላቅ ጩኸትም ሆነ፤ ከፈሪሳውያንም ወገን የሆኑት ጻፎች ተነሥተው “በዚህ ሰው ላይ ምንም ክፉ ነገር አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይስ መልአክ ተናግሮት ይሆን?” ብለው ተከራከሩ። 10 ብዙ ጥልም በሆነ ጊዜ የሻለቃው ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈርቶ ጭፍሮቹ ወርደው ከመካከላቸው እንዲነጥቁት ወደ ሰፈሩም እንዲያገቡት አዘዘ። 11 በሁለተኛውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ “ጳውሎስ ሆይ! በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ፤” አለው። ጳውሎስን ለመግደል የተደረገ ሤራ 12 በነጋም ጊዜ አይሁድ ጳውሎስን እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ በመሐላ ተስማሙ። 13 ይህንም ሤራ ያደረጉት ሰዎች ከአርባ ይበዙ ነበር፤ 14 እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎቹ መጥተው “ጳውሎስን እስክንገድል ድረስ ምንም እንዳንቀምስ ተረጋግመን ተማምለናል። 15 እንግዲህ አሁን እናንተ ከሸንጎው ጋር ሆናችሁ ስለ እርሱ አጥብቃችሁ እንደምትመረምሩ መስላችሁ ወደ እናንተ እንዲያወርደው ለሻለቃው አመልክቱት፤ እኛም ሳይቀርብ እንድንገድለው የተዘጋጀን ነን፤” አሉአቸው። 16 የጳውሎስ የእኅቱ ልጅ ግን ደባቸውን በሰማ ጊዜ፥ መጥቶ ወደ ሰፈሩ ገባና ለጳውሎስ ነገረው። 17 ጳውሎስም ከመቶ አለቆች አንዱን ጠርቶ “ይህን ብላቴና ወደ ሻለቃው ውሰድ፤ የሚያወራለት ነገር አለውና፤” አለው። 18 እርሱም ይዞት ወደ ሻለቃው ወሰደውና “ይህ ብላቴና የሚነግርህ ነገር ስላለው እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶ ወደ አንተ እንድወስደው ለመነኝ፤” አለው። 19 የሻለቃውም እጁን ይዞ ፈቀቅ አለና ለብቻው ሆኖ “የምታወራልኝ ነገር ምንድነው?” ብሎ ጠየቀው። 20 እርሱም “አይሁድ ስለ ጳውሎስ ከፊት ይልቅ አጥብቀህ እንደምትመረምር መስለህ፥ ነገ ወደ ሸንጎ ታወርደው ዘንድ ሊለምኑህ ተስማምተዋል። 21 እንግዲህ አንተ በጅ አትበላቸው፤ እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ ተማምለው ከእነርሱ ከአርባ የሚበዙ ሰዎች ያደቡበታልና፤ አሁንም የተዘጋጁ ናቸው፤ የአንተንም ምላሽ ይጠብቃሉ፤” አለው። 22 የሻለቃውም “ይህን ነገር ለእኔ ማመልከትህን ለማንም እንዳትገልጥ፤” ብሎ ካዘዘ በኋላ ብላቴናውን አሰናበተው። ጳውሎስ ወደ አገረ ገዢው ወደ ፊልክስ እንደ ተላከ 23 ከመቶ አለቆቹም ሁለት ጠርቶ “ወደ ቂሣርያ ይሄዱ ዘንድ ሁለት መቶ ወታደሮችንና ሰባ ፈረሰኞችን ሁለት መቶም ባለ ጦር መሣሪያዎችን ከሌሊቱ በሦስተኛው ሰዓት አዘጋጁ፤” አላቸው። 24 ጳውሎስንም ወደ አገረ ገዢው ወደ ፊልክስ በደኅና እንዲያደርሱት የሚያስቀምጡበትን ከብት ያዘጋጁ ዘንድ አዘዛቸው። 25 እንዲህ የሚል ደብዳቤም ጻፈ፤ 26 ከቀላውዴዎስ ሉስዮስ ወደ ክቡር አገረ ገዢው ወደ ፊልክስ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን። 27 ይህን ሰው አይሁድ ይዘው ሊገድሉት ባሰቡ ጊዜ ከጭፍሮቹ ጋር ደርሼ አዳንሁት፤ ሮማዊ እንደሆነ አውቄ ነበርና። 28 የሚከሰስበትንም ምክንያት አውቅ ዘንድ አስቤ ወደ ሸንጎአቸው አወረድሁት፤ 29 በሕጋቸውም ስለ መከራከር እንደ ከሰሱት አገኘሁ እንጂ ለሞት ወይም ለእስራት የሚያደርስ ክስ አይደለም። 30 በዚህም ሰው አይሁድ ሤራ እንደሚያደርጉበት ባመለከቱኝ ጊዜ ወዲያውኑ ወደ አንተ ላኩት፤ ከሳሾቹንም ደግሞ በፊትህ እንዳይከሱት ዘንድ አዘዝኋቸው። 31 ወታደሮቹም እንደ ታዘዙት ጳውሎስን ይዘው በሌሊት ወደ አንቲጳጥሪስ አደረሱት፤ 32 በነገውም ከእርሱ ጋር ይሄዱ ዘንድ ፈረሰኞችን ትተው ወደ ሰፈር ተመለሱ። 33 እነዚያም ወደ ቂሣርያ ገብተው ደብዳቤውን ለአገረ ገዢው በሰጡ ጊዜ ጳውሎስን ደግሞ በፊቱ አቆሙት። 34 ካነበበውም በኋላ የወዴት አውራጃ እንደሆነ ጠየቀው፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑንም ባወቀ ጊዜ 35 “ከሳሾችህ ደግሞ ሲመጡ እሰማሃለሁ፤” አለው፤ በሄሮድስም ግቢ ውስጥ ይጠብቁት ዘንድ አዘዘ። |