2 ተሰሎንቄ 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ስለ ጸሎት የቀረበ ጥያቄ 1 በቀረውስ ወንድሞች ሆይ! በእናንተ መካከል እንደ ሆነው ሁሉ የጌታ ቃል ፈጥኖ እንዲስፋፋና እንዲከበር ስለ እኛ ጸልዩ፤ 2 እንዲሁም እምነት የምትገኘው በሁሉም ሰው ዘንድ አይደለምና ከዓመፀኞችና ከክፉዎች ሰዎች እንድንድን ጸልዩልን። 3 ነገር ግን ጌታ የታመነ ነው፤ እርሱም ያጸናችኋል ከክፉውም ይጠብቃችኋል። 4 የምናዛችሁን ነገሮች አሁንም ወደፊትም ደግሞ እንደምታደርጉ ስለ እናንተ በጌታ እንመካባችኋለን። 5 ጌታም ወደ እግዚአብሔር ፍቅርና ወደ ክርስቶስ ትዕግሥት ልባችሁን ያቅናው። ስለ ሥራ ፈትነት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ 6 ወንድሞች ሆይ! ከእኛ እንደ ተቀበሉት ትውፊት ሳይሆን ሥራን በመፍታት ከሚኖሩ ወንድሞች ሁሉ እንድትለዩ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን። 7 ስለዚህም እኛን ልትመስሉ እንዴት እንደሚገባችሁ እናንተው ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ በነበርንበት ጊዜ ሥራ ፈቶች አልነበርንም፤ 8 ከእናንተ ዘንድ በማንም ላይ ሸክም እንዳንሆንበት ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖር ነበር እንጂ የማንንም ሰው እንጀራ እንዲያው በነፃ አልበላንም። 9 ይህም እኛን እንድትመስሉ ራሳችንን እንደ ምሳሌ አድርገን ሰጠናችሁ እንጂ ሥልጣን ስላልነበረን አይደለም። 10 እንዲሁም ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ “ማንም ሊሠራ የማይወድ አይብላ፤” ብለን አዘናችሁ ነበር። 11 ይህም የሆነው ሥራ ፈትተው ሥራን ከቶ የማይሰሩ ይልቁንም በሰው ነገር ጣልቃ የሚገቡ አንዳንዶች በእናንተ መካከል እንደሚኖሩ ስለ ሰማን ነው። 12 እንደነዚህ ያሉትንም ሥራቸውን በጸጥታ እየሠሩ የገዛ እንጀራቸውን እንዲበሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናዛቸዋለን፤ እንመክራቸዋለንም። 13 እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ! መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ። 14 በዚህ መልእክት በኩል ለተላከው ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፥ ይህን ሰው በምልክት ለዩት፤ እንዲያፍርም ከእርሱ ጋር አትተባበሩ። 15 ነገር ግን እንደ ወንድም ገሥጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቁጠሩት። የመጨረሻ ሰላምታ 16 የሰላምም ጌታ ራሱ በሁሉ መንገድ ዘወትር ሰላምን ይስጣችሁ። ጌታ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። 17 እኔ ጳውሎስ በራሴ እጅ ይህን ሰላምታ ጽፌአለሁ፤ ይህ በማንኛውም መልእክቴ ውስጥ የሚገኝ ምልክት ነው፤ እንዲህ እጽፋለሁ። 18 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። |