Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

2 ተሰሎንቄ 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የዓመፅ ሰው

1 ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን ይህን እንለምናችኋለን፤

2 ከእኛ በሚመስል መልእክት ወይም በቃል ወይም በመንፈስ፦ “የጌታ ቀን መጥቷል፤” ብላችሁ አእምሮአችሁ በቀላሉ አይናወጥ አይደንግጥም።

3 ማንም ሰው በማናቸውም መንገድ አያታልላችሁ፤ ከሐዲው አስቀድሞ ሳይመጣ የዓመፅም ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ ያ ቀን አይመጣምና።

4 እርሱም ሰው የሚያመልከውን ነገር ወይም አማልክት ነን ከሚሉት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ በማድረግና በመቃወም፦ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ” ብሎ ያውጃል፤ በእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ ይቀመጣል።

5 ከእናንተ ጋር በነበርሁ ጊዜ እነዚህን ነገሮች ነግሬአችሁ እንደ ነበረ አታስታውሱምን?

6 አሁን ምን እንደከለከለው አውቃችኋልና በራሱ ጊዜ የተገለጠ ይሆናል።

7 አስቀድሞም የዓመፅ ሚስጢር በሥራ ላይ ነው፤ አሁን ግን እርሱ ብቻ ይከለክለዋል፤ እርሱም እንዲህ የሚያደርገው ከመንገድ እስከሚወገድ ድረስ ነው።

8 በዚያም ጊዜ ዓመፀኛው ይገለጣል፤ ጌታ ኢየሱስም በአፉ እስትንፋስ ይገድለዋል፤ በመምጣቱም መገለጥ ያጠፋዋል፤

9 ዓመፀኛው ከሙሉ ኃይልና ምልክቶች፥ ከሐሰትም ተአምራቶች ጋር ሆኖ በሰይጣን አሠራር ይመጣል።

10 እንዲሁም ለመዳን እውነቱን ወድደው ባለ መቀበላቸው ለሚጠፉት በማታለል ክፋት ሁሉ ይመጣባቸዋል።

11 ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የሐሰትን ኑፋቄ በመላክ በስሕተት እንዲያምኑ ያደርጋቸዋል።

12 በዚህም እውነቱን ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ የሚሰኙ ሁሉ ይፈረድባቸዋል።


ለመዳን የተመረጡ ሰዎች

13 በጌታ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ! እኛ ግን ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ ልናመሰግን ይገባናል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ከመጀመሪያው አንሥቶ በመንፈስ በመቀደስና በእውነት በማመን እንድትድኑ መርጦአችኋልና፤

14 ለዚህም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ለማግኘት በወንጌላችን ጠራችሁ።

15 ስለዚህም ወንድሞች ሆይ! ጸንታችሁ ቁሙ፤ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ትውፊት ያዙ።

16 ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና፥ የወደደን በጸጋም የዘለዓለምን መጽናናትና መልካሙን ተስፋ የሰጠን እግዚአብሔር አባታችን

17 ልባችሁን ያጽናናው፥ በቃልና በመልካም ሥራ ሁሉ ያጽናላችሁም።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች