Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

2 ሳሙኤል 8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ዳዊት የተቀዳጃቸው ድሎች

1 ከዚህ በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረጋቸው፤ በቁጥጥሩም ሥር አደረጋቸው፥ ሜተግ አማ የተባለችውንም ከተማ ዳዊት ከፍልስጥኤማውያን እጅ ወሰደ።

2 እንዲሁም ዳዊት ሞዓባውያንን ድል አደረገ፤ በመሬት ላይ አጋድሞ በገመድ ለካቸው፤ በገመድ ከተለኩትም ሁለት እጅ ሲገድል፥ አንድ እጅ ግን በሕይወት ይተው ነበር። ስለዚህ ሞዓባውያን የዳዊት ተገዢዎች ሆኑ፤ ገበሩለትም።

3 ዳዊት በተጨማሪ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ያለውን ግዛት መልሶ ለመያዝ በሄደ ጊዜ፥ የጾባን ንጉሥ የረሖብን ልጅ ሀዳድዔዜርን ወጋው።

4 ዳዊትም አንድ ሺህ ሠረገሎች፥ ሰባት ሺህ ፈረሰኞችና ሃያ ሺህ እግረኞች ማረከበት። ቁጥራቸው መቶ የሆነ የሠረገላ ፈረሶች ብቻ ሲቀሩ ሌሎቹን በሙሉ ቋንጃቸውን ቆረጠ።

5 የደማስቆዎቹ ሶርያውያን የጾባን ንጉሥ ሀዳድዔዜርን ለመርዳት በመጡ ጊዜ ዳዊት ሃያ ሁለት ሺህ ሰው ገደለባቸው።

6 ከዚያም የደማስቆ ክፍል በሆነው የሶርያውያን ግዛት የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ። ሶርያውያን ተገዙለት፤ ገበሩለትም። ጌታም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድልን ሰጠው።

7 ዳዊት የሀዳድዔዜር ሹማምንት ያነገቧቸውን የወርቅ ጋሻዎች ወስዶ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣቸው።

8 ንጉሡ ዳዊት ቤጣህና ቤሮታይ ከተባሉ ከሀዳድዔዜር ከተሞችም እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ።

9 የሐማት ንጉሥ ቶዒ ዳዊት መላውን የሀዳድዔዜርን ሠራዊት ማሸነፉን በሰማ ጊዜ፥

10 ቶዒ ከሀዳድዔዜር ጋር ሁልጊዜ ይዋጋ ስለ ነበር፥ ልጁን ዮራምን ወደ ንጉሥ ዳዊት ለሰላምታና በሀዳድዔዜር ላይ ሰለተቀዳጀውም ድል ደስታውን እንዲያቀርብለት ላከው፤ ልጁም የብር፥ የወርቅና የናስ ዕቃ ይዞ መጣ።

11 ንጉሥ ዳዊትም ቀድሞ ካስገበራቸው መንግሥታት ሁሉ በገባለት ብርና ወርቅ እንዳደረገው እነዚህንም ለጌታ ቀደሳቸው።

12 የገበሩትም መንግሥታት ኤዶምና ሞዓብ፥ አሞናውያን፥ ፍልስጥኤማውያንና አማሌቃውያን ነበሩ። እንዲሁም ከጾባ ንጉሥ ከረሖብ ልጅ ከሀዳድዔዜር የወሰደውን ምርኮ ለጌታ ቀደሰ።

13 ዳዊት የጨው ሸለቆ በተባለው ስፍራ ዐሥራ ስምንት ሺህ ኤዶማውያንን ገድሎ ከተመለሰ በኋላ ስሙ ገነነ።

14 በመላው ኤዶም የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ፤ ኤዶማውያን ሁሉ ለዳዊት ተገዙ፤ ጌታም ዳዊት በሄደበት ስፍራ ሁሉ ድልን ሰጠው።


የዳዊት ሹማምት

15 ስለዚህ ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ትክክለኛ ፍርድ አሰፈነላቸው።

16 የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የሠራዊቱ አለቃ ሲሆን፥ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥም ታሪክ ጸሓፊ ነበረ።

17 እንዲሁም የአሒጦብ ልጅ ሳዶቅና የአብያታር ልጅ አሂሜሌክ ካህናት ሲሆኑ፥ ሠራያ ጸሓፊ ነበረ፤

18 የዮዳሔ ልጅ በናያ የከሪታውያንና የፈሊታውያን አለቃ ሲሆን፥ የዳዊት ወንዶች ልጆች ደግሞ አማካሪዎች ነበሩ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች