ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ 2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 9 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የአንጥዮኩስ ኤጲፋኒዮስ የመጨረሻ ቀናት 1 በዚሁ ጊዜ አንጥዮኩስ ከፋርስ አገር ተዋርዶ ተመለሰ። 2 ዓላማው ጰርስጶሊስ ወደምትባል ከተማ ገብቶ እዚያ የሚገኘውን ምኵራብ (የአይሁድ ጸሎት ቤት) መበርበርና ከተማዋንም መያዝ ነበር፤ ሕዝቡ ግን ሮጠና የጦር መሳሪያ አነሳ፤ አንጥዮኩስ በዚያ አገር ሰዎች ተባርሮና ተዋርዶ ተመለሰ። 3 ወደ ኤቅባጥን በደረሰ ጊዜ በኒቃኖርና በጢሞቶዎስ ሰዎች ላይ የደሰረባቸውን ነገር ሰማ። 4 በጣም ተቆጥቶ ያበረሩትን ሰዎች በቀለ በአይሁዳውያን ላይ ለመውጣት አሰበ፤ ስለዚህ ሠረገላ ነጂውን ሰረገለውን በፍጥነት እየነዳ እንዲሄድ አዘዘው፤ ግን በእርሱ ላይ ከሰማዩ ፍርድ ወድቆበት ነበር፤ በትዕቢት ተነፍቶ፥ “በደረስሁ ጊዜ ኢየሩሳሌምን የአይሁዳውያን መቃብር አደርጋታለሁ” ሲል ተናገረ። 5 ሁሉን የሚያይ እግዚአብሔር ግን የእስራኤል አምላክ በማይድንና በማይታይ በሽታ ቀሠፈው፤ ምክንያቱም ያንን ንግግሩን ተናግሮ ሲጨርስ ወዲያውኑ ብርቱ የሆድ በሽታና የመረረ የአንጀት ሠቃይ ያዘው፤ 6 በሌሎች ሰዎች ሆድ ዕቃ ላይ ከባድ ሥቃይ እንዲደረስ ሁሉ ትክክለኛ ፍርድ በእርሱ ላይ ወደበቀት። 7 ሆኖም ከትዕቢቱ ምንም አልታቀበም፤ ሁልጊዜ በትዕቢቱ ተሞልቶ በአይሁዳውያን ላይ በንዴት ይቃጠል ነበር፤ ጉዞውም እንዲፋጠን ያዝዝ ነበር። ከሚሮጠው ሠረገላ ክፉና ወደቀና የአካሉ መገጣጠሚያዎች ከቦታቸው ተዛነፉ፤ 8 ይህ ሰው ከጥቂት ጊዜ በፊት በጭካኔ አስተሳሰቡ የባሕርን ማዕበል ማዘዝ እንኳ የሚችል መስሎ ይታየው፥ የተራሮችን ጫፍ መመዘን፥ ክብደታቸውን ለማሳወቅ የሚችል አድርጐ ራሱን ይቆጥር የነበረ፥ አሁን ግን መሬት ላይ ተጋድሞ በቃሬዛ ተሸክመው ወሰዱት። የእግዚአብሔርን ታላቅነት ሁሉም ማወቅ ቻሉ። 9 ከዚህ ክፉ ሰው ሥጋ ትሎች እስኪወጡ ድረስ ገና በሕይወቱ ሳለ በበሽታና በሥቃይ እየተቆራረጠ ይወድቅ ነበር፤ የገዛ ሠራዊቱ በሙሉ በመበስበሱና በመግማቱ ያቅለሸለሻቸው ነበር። 10 ይህ ከጥቂት ጊዜ በፊት የሰማይን ከዋክብት በእጁ ይነካ የመሰለው ሰው ከሰውነቱ የሚመነጨው ክርፋት የተነሣ አንስቶ ሊሸከመው የሚደፍር እንኳ ጠፋ። 11 በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ በኀዘን ተሰብሮ ከታላቅ ትዕቢቱ መላቀቅና በእግዚአብሔር መቅሠፍት ውስጥ ሆኖ በሚያስጨንቅ ስቃይ ተይዞ የገዛ ራሱን ሁኔታ መገንዘብ የጀመረው። 12 ከእርሱ የሚወጣውን ክርፋት እርሱ እራሱ እንኳ መታገስ (መሸከም) አቅቶት፥ “ለእግዚአብሔር መገዛት ትክክለኛ ነገር ነው፤ አንድ ሙት ሰው ከእግዚአብሔር መተካከልን እንዲተው የተገባ ነው ይል ነበር”። 13 ነገር ግን ይህ ክፉ ሰው ጸሎት ቢያደርግም ጌታ ምሕረቱን አቋርጦበት ነበር፤ 14 የአይሁድ መቃብር አደርጋታለሁ፥ አወድማታለሁ ብሎ በፍጥነት ወደ እርሷ ይገሰግስባት የነበረችውን ቅድስት ከተማ በነጻ እለቃታለሁ አለ፤ 15 የተገባ መቃብር እንኳ እንዳያገኙና የአሞራዎች ምግብ ሆነው እንዲቀሩ፥ ልጆቻቸውም ለአውሬዎች እንዲጣሉ ብሎ የፈረደበቸውን አይሁዳውየን ከአቴና ሰዎች ጋር አስተካክላቸዋለሁ አለ፤ 16 በፊት የበዘበዘውን ቤተ መቅደስ በመረጡ መባዎች አጌጠዋለሁ፤ ዕቃዎቹን አብዝቼ እመልሳለሁ፤ ለመሥዋዕት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከገዛ ራሴ ወጪ አደርጋለሁ አለ፤ 17 ከዚህም በላይ አይሁዳዊ ለመሆንና የእግዚአብሐርን ኃይል እየሰበክሁ በየሀገሩ ሁሉ እዞራለሁ ሲል ተስፋ ሰጠ። አንጥዮኩስ ለአይሁዳውያን ደብዳቤ ጻፈ 18 ነገር ግን በእርሱ ላይ የአምላክ ፍርድ ወድቆበት ስለ ነበር በምንም ዓይነት ሥቃዩ ስላልተቀነሰለት በሁናቴው ተስፋ በመቁረጥ እንዲህ ሲል ለአይሁዳውያን ልመና ጻፈ፤ 19 እጅግ ለተከበራችሁ አይሁዳውያን ዜጐች ከንጉሡና ከመሪው አንጥዮኩስ ሰላምና ጤና፥ ብልጽግናም ይድረሳችሁ፤ 20 እናንተና ልጆቻችሁ በደኀና ከተገኛችሁ ጉዳያችሁ እንደ ሐሳባችሁ ከተፈጸመላችሁ በአምለክ ተማምነን ታላቅ ምስጋና እናቀርበለን። 21 እኔ ግን ከጥቂት ጊዜ ጀምሮ ታምሜ አልጋ ላይ ነኝ፤ አክብሮታችሁና መልካም ፍቃዳችሁን አስታውሳለሁ። ከፋርስ አገር ስመለስ በአስጊ ሕመም ላይ ወድቄ ሁሉም በደህና እንዲኖሩ አስፈላጊ መሆኑን አሰብሁ። 22 ግን በሁኔታዬ ተስፋ አልቆርጥም፤ ከዚህ ሕመሜ ለመዳን ብርቱ ተስፋ አለኝ፤ 23 ሆኖም አባቴ በላይኞቹ ሀገሮች ላይ ጦርነት ባደረገበት ጊዜ ተተኪውን እንደወሰነ አሰብኩ፤ 24 ያልታሰበ ነገር ወይም አንድ አስቸጋሪ ነገር በመጣ ጊዜ ያገሩ ሰዎች ለማን ሥልጣን እንደተሰጠ እንዲያውቁና እንዳይቸገሩ፥ 25 ከእኛ አቅራቢያ ነገሥታትና የመንግሥታችን ጐረቤቶች ምቹ ጊዜ አግኝተናል ብለው እንዲያስቡና እንዳይጠብቁ ወደ ላይኛው ሀገር በፍጥነት በሄድኩበት ጊዜ ከእናንተ ለብዙዎቹ አደራ ብሎ የሰጠኋችሁን ልጄን አንጥዮኩስን ንጉሥ እንዲሆን ወስኛለሁ፤ ደብዳቤም እንዲህ ብዬ ጽፌለታለሁ፤ 26 “እያንዳንዱ ግለሰብም ሆነ ለማኀበረሰቡ ያደረግሁትን ደግ ሥራ እንድታስታውሱና በእኔ ላይና በልጄ ላይ ያላችሁን መልካም አስተሳሰባችሁን ጠብቃችሁ እንድትኖሩ እለምናችኋላሁ፥ እጠይቃችኋለሁ። 27 እርሱ በታዛዥነት የእኔን ሐሳብ እንደሚከተልና ከእናንተ ጋር እንደሚስማማ እርግጠኛ ነኝ”። 28 በዚህ ዓይነት ይህ ነፍስ ገዳይና ስም አጥፊ ሌሎቹን ባሰቃየው መጠን አሰቃቂ ስቃይ ከተቀበለ በኋላ በሰው ሀገር አሳዛኝ ሞት ሞተ። 29 ሬሳውን ወዳጁ ፊሊጶስ ወሰደው፤ ግን እርሱ በንጉሡ ልጅ በአንጥዮኩስ ስላልተማመን ወደ ግብጽ ወደ ጰጠሎሜዮስ ሄደ። |