ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ 2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የአይሁዳውያን ድል የአሳዳጆች ሞትና የቤተ መቅደሱ መንጻት ይሁዳ መቃቢስና ተቃዋሚዎቹ 1 ይሁዳ መቃቢስና ጓደኞቹ በሥውር ወደ መንደሮች ገቡ፤ የአገራቸውንም ሰዎች ጠሩ፤ በአይሁዳቹ ሕግ ተጠብቀው የኖሩትን ወደ እነርሱ አምጥተው ስድስት ሺህ የሚያህሉ ሰዎችን ሰበሰቡ። 2 በሁሉም አቅጣጫ የተገፉትን ሕዝቦች እንዲመለከት፥ በአረማውያኑ የተሠራው ቤተ መቅደስ ወደ ነበረበት እንዲመለስ፥ በመውደም ላይ ስላለች 3 ከተማ ምሕረት እንዲያደርግ፥ በግፍ የፈሰሰ ደማቸው ለሚያሰማው ጩኸት ምሕረት እንዲሰጥ፥ 4 በክፋት የተደመሰሱትን ንጹሓን ሕፃናት እንዲያስታውስና ስሙን በተሳደቡት ሰዎች ላይ መዓቱን እንዲያወርድበባቸው ለመኑት። 5 ይሁዳ መቃብስ የወታደሮች አለቃ በሆነ ጊዜ የእግዚአብሔር ቁጣ ወደ ይቅርታ ስለተለወጠ፥ ለአረማውያን የማይበገር ሰው ሆነ። 6 በከተሞችና በመንደሮች ላይ በድንገት አደጋ ጥሎ አቃጠላቸው፤ ምቹ ቦታዎችን ይዞ በጠላት ላይ ከፍ ያለ ጉዳት አደረሰ። 7 እንደዚህ ያለውን ውጊያ የሚያደርገው ጨለማን ተገን በማድረግ በሌሊት ነበር፤ የጀግንነቱም ዝና በሁሉ ቦታ ተሰማ። የኒቃሮንና የጐርጊያስ ዘመቻ 8 ይሁዳ መቃቢስ ጥቂት በጥቂት ከፍ ከፍ እያለና ነገሩ ሁሉ ብዙ ጊዜ እየተቃናለት በመሄድ ፊሊጶስ ለቀርለሲርያና ለፊኒቆስ መስፍን (ገዥ) ለጰጠሎሜዮስ ሰለ ንጉሡ ጉዳይ እንዲረዳው ጻፈለት። 9 ጰጠሎሜዮስ የጳጥርኩልን ልጅ ኒቃኖርን በደረጀ ከንጉሡ ወዳጆች ጋር የሚቆጠረውን የአይሁድን ዘር እንዲደመሰስ ከተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ከሃያ ሺህ በማያንሱ ወታደሮች ላይ አለቃ አድርጐ ላከው። በጦር ስልት የታወቀውን ተዋጊ ሰው ጐርጊያስንም ጨመረለት። 10 ኒቃኖር የሚማረኩት አይሁዳውያን ተሽጠው ንጉሡ ለሮማውያን የሚሰጠው ሁለት ሺህ መክሊት ግብር ይከፈላል ብሎ ያስብ ነበር። 11 ወዲያውኑም በባሕር አጠገብ የሚገኙትን ከተሞች አይሁዳውያን ባሮችን ለመግዛት እንዲመጡ ጥሪ አደረገላቸው፤ በአንድ መክሊት ዘጠኝ ሰዎች እንደሚሸጥላቸው ተስፋ ሰጣቸው፤ ሁሉን ከሚችል አምላክ የሚመጣበትን በቀል አላሰበም ነበር። 12 ኒቃኖር ወደ እርሱ እንደሚገሠግሥ ይሁዳ ሰማ፤ የጠላት ጦር መቃረቡን ለሰዎቹ አስታወቃቸው፤ 13 ፈሪዎችና በእግዚአብሔር ጽድቅ ላይ እምነት የጐደላቸው ሰዎች ሸሽተው ወደ ሌላ ቦታ ሄዱ። 14 ሌሎች ያላቸውን ንብረት ሁሉ ሸጡ፤ ገና ውጊያው ከመጀመሩ በፊት ክፉው ኒቃኖር የሸጣቸውን አይሁዳውያን እንዲያድናቸው እግዚአብሔርን ይለምኑ ነበር። 15 የሚያድናቸውም በእነርሱ ምክንያት ሳይሆን ከአባቶቻቸው ጋር ውል በገባው መሠረትና በእነርሱ ላይ በተጠራው ቅዱስና ታላቅ ስሙ ምክንያት ነው። 16 ይሁዳ መቃቢስ ስድስት ሺህ ሰዎችን ሰብስቦ እንዲህ ሲል መከራቸው፥ “በጠላቶች ፊት አትፍሩ፤ ያለ ፍትሕ የሚወጉንን የአረማውያን ታላቅ ጦር በማየት ሐሳብ አይግባችሁ፤ በጀግንነት ተዋጉ፤ 17 በቅዱሱ ቦታ ላይ የፈጸሙትን የዓመፅ ሥራ በከተማይቱ ላይ ያደረጉትን የማይገባ ተግባርና ውርደት፥ የአባቶችን ባህል መጥፋትም ተመልከቱ፤ 18 እነርሱ በጦር መሣሪያዎቻቸውና በድፍረታቸው ይመካሉ፤ እኛ ግን ተስፋችን (እምነታችን) ሁሉን በሚችል እግዚአብሔር ላይ ነው፤ እርሱ በሚሰጠው በእራሱ ምልክት ብቻ ወደ እኛ የሚመጡትንና ከእነርሱም ጋር መላውን ዓለም መገልበጥ የሚችል ነው”። 19 እንዲሁም ለቀድሞ አባቶቻቸው የተደረገላቸውን ድጋፍ ቆጠረላቸው። “በሰናክሬም ጊዜ መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰዎች ተደመሰሱ። 20 በባቢሎን አገር በገላትያ ሰዎች ላይ በተደረገው ጦርነት ላይ ተካፋዮች የነበሩ ሰዎች ቁጥራቸው በአራት ሺህ መቄዶያናውያን ሌላ ስምንት ሺህ አይሁዳውያን ነበሩ፤ የመቄዶንያ ሰዎች ጦር ወደ ኋላ ባለ ጊዜ ስምንቱ ሺህ አይሁዳውያን መቶ ሃያ ሺህ ጠላቶች ደምስሰዋል፤ ይህንን ማድረግ የቻሉት ከእግዚአብሐር በተደረገላቸው እርዳታ ነው፤ ብዙ ምርኮም አግኝተዋል”። 21 በቃሉ ካደፋፈራቸውና ስለ ሕጋቸውና ስለ ሀገራቸው እንዲሞቱ ካዘጋጃቸው በኋላ ጦሩን በአራት ክፍል ከፋፈለው፤ 22 ለእያንዳንዱ ክፍል ወንድሞቹን ስምዖንን፥ ዮሴፍን፥ ዮናታንን መሪዎች አደረጋቸው፤ እያንዳንዳቸው አንድ ሺህ አምስት መቶ ሰዎችን እንዲያዝዙ አደረገ። 23 አልዓዛር ቅዱሱን መጽሐፍ በከፍተኛ ድምፅ እንዲያነብ ካዘዘ በኋላ ለወታደሮቹ “የእግዚአብሔር እርዳታ” የሚል መፈክር ሰጣቸውና እሱ የመጀሪያው ጦር ሠራዊት መሪ ሆኖ ከኒቃኖር ጋር ጦርነት ገጠመ። 24 ሁሉን የሚችል አምላክ ረዳታቸው ሆኖ ከዘጠኝ ሺህ በላይ ጠላቶች ገደሉ፤ የኒቃኖርን ወታደሮች አብዛኖቹን አቆሰሉ፥ ቆራረጡዋቸው፥ ሁሉንም አባረሪቸው። 25 እንደ ባሮች ሊገዟቸው ከመጡት ሰዎችም ላይ ብሩን ወሰዱባቸው፤ 26 ሰዎቹን ወደ ሩቅ ካባረሩዋቸው በኋላ የሰንበት ዋዜማ ስለሆነና ጊዜውም ስላልፈቀደላቸው ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ስለዚህ እነርሱን ማበረራቸውን አልቀጠሉም፤ 27 የጠላቶችን መሣሪያዎች ከሰበሰቡና ምርኮአቸውንም ከወሰዱ በኋላ የምሕረቱ መጀመሪያ ቀን በሆነው በዚህ ቀን ስለጠበቃቸው እግዚአብሔርን ብዙ እያመሰገኑና እያወደሱ የሰንበትን ቀን ያከብሩ ጀመር። 28 ከሰንበት ቀን በኋላ ከምርኮ ያገኙትን ከፍለው በስደት ለተጐዱ ሰዎች፥ ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች፥ ለሙት ልጆች አከፋፈሉ፥ የቀረውን እነርሱ ከልጆቻቸው ተከፋፈሉት። 29 ምርኮውን እንዲህ ካከፋፈሉ በኋላ የኀብረት ጸሎት አደረጉ፤ መሐሪው እግዚአብሔር አገልግጋዮቹን ለዘወትር እንዲታረቃቸው ለመኑት። የጢሞቴዎስ እና የባቂደስ መሸነፍ 30 ከጢሞቴዎስና ከባቂደስ ወታደሮች ጋር ተዋግተው ከሃያ ሺህ የሚበዙ ሰዎችን ገደሉ፤ ረዣዥም ምሽጐችንም ያዙ፤ የማረኩትንም ብዙ ምርኮ በሁለት ከፍለው ግማሹን እነርሱ ወሰዱት፤ የቀረውን ግማሽ ለስደተኞች፤ ለሙት ልጆች፥ ለመበለቶችና ለሸማግሌዎች አከፋፈሉ። 31 ከጠላቶች የተገኘውን የጦር መሣሪያ ሁሉ በጥንቃቄ ለቃቅመው በልዩ ቦታዎች አስቀመጧቸው፤ የቀረውን ምርኮ ግን ወደ ኢየሩሳሌም አመጡ። 32 በአይሁዳውያን ላይ ብዙ ግፍ የሠራውን፥ ከጢሞቴዎስ ጋር የነበረውን እና እጅግ ክፉ ሰው የሆነውን የጎሣ አለቃ ገደሉት። 33 በሀገራቸው የድል በዓልን በሚያከበሩበት ጊዜ የተቀደሱ መዝጊያዎችን ያቀጠሉና ከካልሲስቴናውያን ጋር በአንዲት ቤት ተሸሽገው የነበሩበትን ሰዎች በእሳት አቃጠሏቸው፤ በዚህ ዓይነት የተገባ የክፋት ዋጋቸውን አገኙ። የኒቃኖር ፍርጠጣና ምስክርነት 34 ባለ ሦስት ቀለማቱ ሸፈጠኛ የነበረው አይሁዳውያንን እንደ ባሮች የሚገዙ አንድ ሺህ ነጋዴዎችን ያመጣ፤ ኒቃኖር የማይረቡ ብሎ የገመታቸው በነበሩ ሰዎችና 35 በእግዚአብሔር እርዳታ ሊያዋርዳቸው ፈልጐ በነበሩት ሰዎች ተዋረደ። የክብር ልብሱን አውጥቶ ጥሎ እንዳመለጠ ባርያ ወደ ሜዳ ሸሸ። ብቻውን ተጥሎ እንደ ምንም ብሎ ወደ አንጾኪያ ደረሰ፤ ጦር ሠራዊቱም ተደመሰሰ። 36 የኢየሩሳሌምን ምርኮኞች ሽያጭ ግብር እሰጣችኋለሁ ብሎ ለሮማውያን ተስፋ ሰጥቶ የነበረው ሰው አይሁዳውያን ተከላካይ እንዳላቸው አመነ፤ ይህ የሚከላከልላቸው “አምላክ” የሰጣቸውን ሕግ በመከተላቸው ምክንያት አይሁዳውያን የማይበገሩ መሆናቸውን ተረዳ። |