Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ

- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ሁለተኛው የግብጽ ዘመቻ

1 በዚያን ጊዜ አንጥዮኩስ በግብጽ ላይ እንደገና ለመዝመት ይዘጋጅ ጀመር፤

2 አርባ በሚሆኑ ቀኖች ውስጥ በከተማዋ ሁሉ የወርቅ ልብስ ለብሰው በአየር የሚወረወሩ ፈረሰኞች ታዩ፤

3 ለጦር የተሰለፉ ወታደሮች፥ ለጦር በተሰለፉ ፈረሰኞች ከወዲያ ወዲህ የሚወረወሩ የጦር መሳሪያዎችና መውጊያዎች፥ የሚወዛወዙ ጋሻዎች፥ ተከምረው የቆሙ ጦሮች፥ የተመዘዙ ሰይፎች፤ ተወርዋሪ መሳሪያዎች፥ የሚብለጨለጩ የወርቅና የተለያዩ የብረት ልብሶች ታዩ።

4 ስለዚህ ይህ የጦር ልምምድ መልካም ውጤት እንዲኖረው ሁሉም ይጸልዩ ነበር።


የኢያሶን ዐመጽ፤ የአንጥዮኩስ ኤጲፋኒዮስ ተቃውሞ

5 የአንጥዮኩስ ሞት በሐሰት ስለተወራ ኢያሶን ከሺህ ያላነሱ ሰዎችን ይዞ በድንገት የኢየሩሳሌምን ከተማ ወጋ፤ ግንብዋ ፈርሶ ከተማዋ በተያዘች ጊዜ መነላዎስ ሸሽቶ ወደ ምሽግ ገባ።

6 ኢያስን ያለርኀራኄ የገዛ ገሩን ሰዎች አጠፋ፤ የገዛ ዘሮቹን፥ ወንድሞቹን ማሸነፍ ትልቅ ጉዳት መሆኑን አላሰበም፤ ድል የነሳቸው ጠላቶቹን እንጂ ወገኖቹን አልመሰለውም።

7 በአንድ በኩል ሥልጣን ለመያዝ አልተቻለውም፤ በሌላ በኩል ደግሞ በከዳተኛነቱ ዕፍረትን ተከናነበ፤ እንደገናም ወደ ስደቱ ቦታ ወደ አሞን አገር ሄደ።

8 የጭካኔ ድርጊቱ ፈጻሜውን አገኘ፤ በዓረብ ንጉሥ በአርስጣስዩስ ታሰረ፤ ከከተማ ወጥቶ ሸሸ። በሁሉም ይታደን ነበር፤ ምክንያቱም ሕግ በማፍረሱ ተጠልቷል። ሀገሩንና ሕዝቡን በማጥፋቱ ተተፍቷል። ወደ ግብጽ ተሰዶ ሄደ።

9 ይህ ሰው ብዙ ሰዎችን ከግዛታቸው ምድር ያባረረ፥ ዘሩን ፍለጋና መጠጊያ አገኛለሁ በሚል ወደ እስፖርታ የተጓዘ፤ ነገር ግን በባዕድ አገር ባክኖ የቀረ ሰው ነው።

10 እርሱ የብዙ ሰዎችን ዓፅም ላለመቅበር ወርውሮ ጥሏል፤ አሁን ግን ለእርሱ የሚያለቅስለት የለም፤ የቀብር ሥርዓት አልተፈጸመለትም፤ ከአባቶቹ የመቃብር ቦታም አላገኘም።

11 ንጉሡ እነዚህን ነገሮች በሰማ ጊዜ የአይሁድ አገር ሰዎች መሸፈታቸውን አወቀ፤ እንደ ዱር አውሬ በቁጣ ተናዶ ከግብጽ ተነሣና ከተማዋን ማመስ ጀመረ።

12 ቀጥሎም ወታደሮቹን፥ የሚያገኙዋቸውን ያለርህራሄ እንዲጨፈጭፉና በየቤታቸው የሚገቡትንም እየያዙ እንዲያርዷቸው አዘዘ።

13 ወጣቶችንና ሸማግሌዎችንም ፈጁ፤ ወንዶችን፥ እናቶችን እና ሕፃናትንም አረዱ፥ ወጣት ልጃገረዶችንና የሚጠቡ ሕፃናትን ቀነጠሱ።

14 በሦስት ቀን ውስጥ ሰማንያ ሺህ ሰዎች የወረራው ሰለባ ሆኑ፤ አርባ ሺህ በውጊያ ላይ ሞቱ፤ ቀሪዎች ደግሞ በባርነት ተሸጡ።


የቤተ መቅደሱ መበዝበዝ

15 ይህም አልበቃ ብሎት እጅግ በጣም በተቀደሰው ቤተ መቅደስ ውስጥ መግባት ደፈረ፤ መሪውም ሕጉንና ሀገሩን የካዳው መነላዎስ ነበር።

16 በረከሱ እጆቹ የተቀደሱ ዕቃዎችን፥ ሌሎች ነገሥታት ለቤተ መቅደሱ እድገትና ክብር ይሆናሉ ብለው ያቀረቡዋቸውን መባዎች ወሰደ፤ በርኩስ እጁ ዳሰሳቸው።

17 አንጥዮኩስ በትዕቢት ሐሳብ ተወጠረ፤ ለጥቂት ጊዜ ልዑል ጌታ በሕዝቡ ኃጢአት ምክንያት እንደተቆጣና ቅዱስ ቦታ ሲደፈርም ዝም ብሎ እንዳየ አልተገነዘበም።

18 እነርሱ እንዲህ በብዙ ኃጢአት ላይ ባይወድቁ ኖሮ እርሱም የቤተ መቅደሱን ግምጃ ቤት ለመመርመር ሴሌውከስ ተልኮ እንደነበረው እንደ ሄልዮድሮስ በገረፈው ነበረ፤ ከእዚህ ከድፍረት ሥራው በተቆጠበም ነበር።

19 እግዚአብሔር ግን ቅዱስን ቦታ የመረጠው ስለ ሕዝቡ ነው እንጂ ሕዝቡን የመረጠው ስለ ቅዱስ ቦታ አይደለም።

20 ስለዚህ የተቀደሰውም በሕዝቡ ላይ የደረሰው መከራ ከመጋራቱ በኋላ በሰላምም ጊዜ ተገቢውን ክብር ተካፍሏል፤ ሁሉን የሚችል አምላክ በተቆጣ ጊዜ እንደ ተጣለ፥ ልዑል ጌታ በታረቀ ጊዜ በክብር ታድሷል።

21 አንጥዮኩስ ከበቤተ መቅደሱ አንድ ሺህ ስምንት መቶ መክሊቶች ከወሰደ በኋላ በፍጥነት ወደ አንጾኪያ ተመለሰ፤ በትዕቢቱና እራሱን ከፍ ከፍ በማድረጉ በየብስ ላይ የሚቀዝፈና በባሕር ላይ የሚራመድ መስሎ ታይቶ ነበር፤

22 ግን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ሹማምንት ትቶ ሄደ፤ ከእርሱም ይብስ የከፋውን የፍርግያ ሰውን ፊሊጾስን በኢየሩሳሌም ላይ ሾመው፤

23 በጋሪዝም ተራራ አንድሮኒቆስን የበላይ አደረገው፤ ከዚህም በላይ በክፋቱ ከሁሉም የባሰውን በሀገሩ ሰዎች ላይ ጨካኝ የሆነውን መነላዎስን ሾሞ እዚያ ተወው።


የማሳርኩ አጵሎንዮስ ያከናወናቸው ተግባራት

24 አይሁዶችን በጣም ስለጠላቸው ንጉሡ የማሳርኩን አጵሎንዮስን ከሃያ ሁለት ሺህ ሰው ጋር ሆኖ በዕድሜ ከፍ ያሉትን ሰዎች እንዲገድል፤ ሴቶችንና ልጆችን እንዲሸጥ አዘዘ።

25 ስለዚህ አጵሎንዮስ ወደ ኢየሩሳሌም ከደረሰ በኋላ ሰላማዊ መስሎ አይሁዶች ሥራ በማይሠሩበት በተቀደሰው ቀን፥ በሰንበት ወታደሮች መሣሪያ ይዘው በሠልፍ እንዲወጡ አዘዘ።

26 እነርሱን ለመመልከት ወጥተው የነበሩትን አይሁዳውያንን ሁሉ አስገደለ፤ ከተማዋንም ከወታደሮቹ ጋር ሆኖ ለጦር መሣሪያ ወረራት፤ ብዙ ሰዎችንም ገደለ (ጨፈጨፈ)።

27 ይሁዳ መቃቢስ ግን ከዘጠኝ ሌሎች ሰዎች ጋር ሆኖ ወደ በረሃ ገባ፤ እርሱና ጓደኞቹ እንዳይረክሱ በማለት ሣር እየበሉ እንደ አራዊት በበረሃ ይኖሩ ነበር።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች