Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ

- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


በአንጥዮኩስ ኤጲፋንዮስ ዘመን የግሪካውያን ሥርዓት ኘሮፖጋንዳ እና ስደት የቤተ መቅደሱ አስተዳዳሪ፥ የስምዖን ክፉ ተግባር

1 ግምጃ ቤቱን ለማስወረስ የተናገረውና ሀገሩን የከዳ፥ ያ ስምዖን በኦንያ ላይ ክፉ መናገሩን ቀጠለ፤ ጌልዮድሮስን ያስደበደበና እነዚያን መከራዎች ያወረደበት እርሱ ነው እያለ ይናገር ነበር።

2 የከተማዋ መልካም አድራጊ፥ የወንድሞቹ ጠባቂ፥ እርሱን ለመክሰስ ደፈረ፥

3 ጥላቸውም እያደገ ሄዶ በሰምዖን የተቀጠሩ ወኪሎች ግድያዎችን እስከ መፈጸም ደረሱ፤

4 ኦንያ ይህ ጥላቻ ምንኛ የከፋ መሆኑንና የቀለሲርያና የፊኒቄስ አስተዳዳሪ የሆነው የምነስጤዬ ልጅ አጶሎንዮስ የስምዖንን ክፋት እያበረታታ የሚሄድ መሆኑንም በማየት

5 ወደ ንጉሡ ሄዳ፤ የሄደውም የሀገሩን ሰዎች ለመክሰስ ሳይሆን የሕዝቡን ሁሉ የጋራና የግል ጥቅማቸውን በመፈለግ ነው፤

6 ከእንግዲህ ወዲህ ያለ ንጉሥ ውሳኔ በአስተዳደሩ ውስጥ ሰላምን ማግኘት እንደማይቻልና ስምዖንም እብደቱን እንደሚያቆም ስለተገነዘበም ጭምር ነው።


ሊቀ ካህናት ኢያሶን የግሪካውያንን ሥርዓት አስተዋወቀ

7 ሴሌውከስ ከሞተ በኋላ ኤጲፊንዮስ አንጥኩስ መንግሥቱን በያዘ ጊዜ የኦንያም ወንድም ኢያስን የሊቀ ካህንነትን ሹመት ተመኘ፤

8 ወደ ንጉሡ ሄደና ሦስት መቶ ስለሳ የብር መክሊት እንደሚሰጠውና ሰማንያ መክሊትም ሌላ ጊዜ እንደሚጨምርለት ቃል ገባለት።

9 ጅምናሲዩም እና የወጣት ማእከል ቦታ ለመሥራትና የኢየሩሳሌም አንጾኪያውያን ለመመዝገብ ሥልጣን የሰጠው እንደሆነ አንድ መቶ ሃምሳ መክሊት በተጨማሪ እንደሚሰጠውም ቃል ገባለት፤

10 ንጉሡ እሺ አለውና ኢያሶን ሥልጣኑን በጨበጠ ጊዜ ወዲያውኑ የገዛ ራሱን ሕዝብ ሥርዓት አስለውጦ እንደ ግሪካውያን እንዲኖሩ አደረጋቸው።

11 ነገሥታት በመልካም ፈቃዳቸው ስለ ዮሐንስ ሲል ለአይሁዳዊያን የሠሩትን ሥርዓት አፈረሰ፤ ዮሐንስ የኤውጶለም አባት ነው፤ ኤውጶለም ከሮማውያን ጋር የወዳጅነትና የስምምነት ውል ለመዋዋል ወደ ሮም የተላከ ሰው ነው። ኢያሶን እንዲሁም የሀገሩን ሥርዓት አፍርሶ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚጻረሩ ሥርዓቶች አስገባ።

12 በቤተ መቅደስ ተራራ አጠገብ የሚገኘው ምሽግ ግርጌ ጅምናሲዩም እስከሚቋቋም ደረሰ፥ ምርጥ የሆኑ ታዋቂ ስፖርተኞችንም ልብስ አልብሶ ወደ እዚያ አስገባቸው።

13 አምላኩን የከዳ እና እውነት ሊቀ ካህንም ባለመሆኑ ኢያሶን ለትዕቢቱ ገደብ አልነበረውም፤ የግሪካውይንን ሥርዓት የማስፋፋቱ ተግባር ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ

14 ካህናት እንኳ የመሠዊያውን አገልግሎት ለመፈጸም አይተጉም፤ ቤተ መቅደሱን ንቀው መሥዋዕቶቹን ችላ ብለዋል፤ ልክ ደወል ሲደወል በሕግ ወደ ተከለከው ዘይት በማደሉ ጨዋታ ለመሳተፍ ይሽቀዳደማሉ።

15 የሀገራቸውን ክብር ንቀው የአረማውያን ክብር ንቀው የአረማውያንን ክብር መረጡ።

16 በዚህ ምክንያት ብዙ ችግር ወደቀባቸው፤ ሥርዓታቸውን መከተልና እነርሱን መምሰል ፈለጉ፤ እነርሱ ግን ጠላቶቻቸውና ገራፊዎቻቸው ሆኑ።

17 የአምላክን ሕግ መጣስ በቀላሉ የሚታለፍ ነገር አይደለም፤ መጪው ዘመን እንደሚያሳየው የእግዚአብሔርን ቃል መሻር እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

18 በጢሮስ በየአራቱ ዓመት ንጉሡ ባለበት የማከበር ታላቅ የስፖርት በዓል ነበር፤

19 ርኩሱ ኢያሶን ከኢየሩሳሌም የአንጾኪያ ሰዎችን እንደ መልእክተኞች አድርጐ ወደዚያ ላካቸው፤ እነርሱ ለህርቆል መሥዋዕት ሊባክን አይገባውም፤ ይልቁንም ለሌሎች ወጪዎች መቀመጥ አለበት ብለው ወሰኑ።

20 ለህርቆል መሥዋዕት እንዲሆን ብሎ ኢያሶን የላከው ብር ይዘውት በሄዱት ሰዎች አሳሳቢነት ለመርከቦች ማሰሪያ ዋለ። አንጥዮኩስ ኤጲፋኒዮስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም ገባ

21 የምነስጢዩስ ልጅ አጶሎንዮስ በንጉሥ ፊልመትሮስ የጋብቻ በዓል ላይ እንዲገኝ ወደ ግብጽ ተላከ፤ አንጥዮኩስ ንጉሥ ፊልመትሮስ እርሱን በሚመለከቱ ነገሮች ሁሉ በጠላትነት ዐይን እንደሚያየው በማወቅ ስለ ደህንነቱ ማሰብ ጀመረ። በዚህም ምክንያት ወደ ኤዮጴ ደረሰና ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ።

22 ኢያስንና የከተማው ሰዎች በክብር ተቀበሉት። በችቦ ብርሃንና በዕልልታ አስገቡት። ከዚህ በኋላ ሠራዊትን ወደ ፌንቄስ አዘመተ። መነላዎስ ሊቀ ካህናት ሆነ

23 ከሦስት ዓመት በኋላ ኢያሶን የዚያን የስምዖን ወንድም መነላዎስን ለንጉሡ ገንዘብ እንዲወስድና አጣዳፊ ስለሆኑት ጉዳዮች እንዲነጋገር ላከው።

24 መነላዎስ ወደ ንጉሡ ቀርቦ እንደ ባለ ሥልጣን እራሱን ከፍ ከፍ በማድረግ ተናግሮ የሊቀ ካህንነት ሹመት እንዲሰጠው አደረገ፤ ከኢያስን አብልጦም ሦስት መቶ የብር መክሊት ሰጠው።

25 ከነጉሡ የተሰጠውን የሹመት ደብዳቤ ይዞ ተመለሰ፤ ይሁን እንጂ ለሊቀካህንነት የሚያበቃው ምንም ዓይነት ችሎታ አልነበረውም፤ የጨካኝነት መዓቱን፥ የአውሬነት ቁጣውን ከማሳየት በቀር ሌላ ነገር አያውቅም።

26 ኢያሶን የወንድሙን ሹመት በግፍ እንደወሰደ እንዲሁም የእርሱም ሹመት በሌላ ሰው ተወሰደበትና ወደ አምናቡያን አገር ተሰዶ ሄደ።

27 መነላዎስ ግን ሥልጣንን ጨበጠ፤ ሆኖም እስጣለሁ ብሎ ለንጉሡ ቀል የገባለትን ገንዘብ አይሰጥም ነበር።

28 ነገር ግን የምሽጉ አዛዥ ነበር። ስለዚህ ሁለቱም ተጠርተው ወደ ንጉሡ ሄዱ።

29 መነላዎስ ለሊቀ ካህንነቱ ሠራ ወንድሙን ሊሲኰማስን ተካ፤ ሶስትራትም የቆጅሮሳውያን ሹም የነበረውን ክራቴምን ተካ። ኦንያ ተገደለ

30 አገራቸው የንጉሥ ዕቁባት ለሆነችው ለአጥናዩኪዶ ስለተሰጠባቸው የተርሲስና የማሎ አገር ሰዎች ከዚህ በኋላ ሁከት አስነሡ።

31 ስለዚህ ንጉሡ ከሹማምንቱ አንዱን አንድሮኒቆስን በቦታው ተክቶ ሁከቱን ለማረጋገጋት በፍጥነት ሄደ።

32 መነላዎስ ጥሩ አጋጣሚ እንደመጣለት ተረድቶ የቤተ መቅደሱን የወርቅ ዕቃዎች ወሰደና ለአንድ ሮኒቆስ ሰጠ፤ ሌሎችንም ዕቃዎች ለጤሮስና በአካባቢው ለሚገኙ አገሮች ሸጠ።

33 ኦንያ ይህን ነገር ካረጋገጠ በኋላ በአንጾኪያ አጠገብ በምትገኝ በተጠበቀች ከተማ በጻፍን ሆኖ ተግሣጹን አሰማው።

34 ስለዚህ መነላወስ አንድሮኒቆስን ብቻውን ገለል አድርጐ ኦንያን እንዲገድለው መከረው፤ አንድሮኒቆስም ወደ ኦንያ ሄዶ በተንኰል በማታለል፥ ቀኝ እጁን ዘርግቶ በመማል ምንም እንኳ ቢጠራጠር ከተሸሸገበት ቦታ እንዲወጣ አደረገውና ፍትሕን በመጣስ ወዲያውኑ አስገደለው።

35 በዚህ ምክንያት አይሁዳውያን ብቻ ሳይሆኑ የሌሎች አገሮች ሰዎችም ፍትሕ በጐደለበት በዚህ ሰው ግድያ እጅግ በጣም ተቆጡ።

36 ንጉሡ ከቂልቅያ በተመለሰ ጊዜ በከተማው የሚገኙ አይሁዳውያንና ግሪካውያን ይህን የዓመፅ ሥራ አብረው በመንቀፍ ወደ ንጉሡ ቀርበው ያለ ፈርድ የተፈጸመውን ግድያ ገለጹለት፤

37 አንጥዮኩስ በልቡ አዝኖና ራርቶ የሟቹን ጥበብና ደግነት በማስታወስ እንባውን በማፈሰስ አለቀሰ።

38 በጣም ተናዶ ወዲያውኑ ከአንድሮኒቆስ ክብሩን ገፈፈ፤ ልብሶቹንም ቀደደበት፤ በኋላም በከተማው ዙርያ እየዞሩ በኦንያ ላይ ግድያ እስከፈጸመበት ድረስ እንዲወስዱት አድርጐ ይህን ነፍሰ ገዳይ አስገደለው፤ አንድሮኒቆስ በእግዚአብሔር ተቀስፎ እንዲህ የተገባ ቅጣቱን አገኘ። የሊሲማቆስ በዓመፅ መገደል

39 ሊሲማቆስ ከመነላዎስ ጋር በመስማማት ብዙ የቤተ መቅደስ ዕቃዎችን ሰርቆ ወስዶ ነበር፤ የዚህ ነገር ወሬ በውጭ ስለ ተሰማ ሕዝቡ በሊሲማቆስ ላይ ተነሣበት፤ እርሱ ብዙ የወርቅ ዕቃዎችን አውጥቶ አጥፍቶ ነበር።

40 ሕዝቡ በጣም ተቆጥቶ በተነሣበት ጊዜ ሊስማቆስ ሦስት ሺህ ወታደር አሰልፎ፥ አንድ የጦር አለቃ ሾሞ ያልተገባ ውጊያ አደረገ፤ ይህ የጦር ሹም ስሙ አውራኖስ የተባለ በዕድሜ የገፋና ዕብድ መሣይም ነበር።

41 ውጊያው የተሠነዘረባቸው ከሊሲማቆስ መሆኑን አውቀው አንዳንዶቹ ድንጋይ፥ ሌሎቹ ዱላ ይዘው ለመዋጋት ተነሡ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ እዚያ የነበረውን አመድ በእጆቻቸው እያፈሱ በሊሲማቆ ሰዎች ለይ በመበተን ተዋጉ።

42 በዚህ ዓይነት ብዙዎችን አቆሰሉ፤ አንዳንዶቹን ገደሉ፤ የተቀሩትንም አባረሩ፤ የቤተ መቅደሱን ዕቃዎች የወሰደውን ሊሲማቆስንም በቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት አጠገብ ገደሉት።


መነላዎስ በገንዘብ ነጻ ወጣ

43 በእነዚህ ነገሮች መነላዎስ ለፍርድ ቀረበ፤

44 ንጉሡ ወደ ጢሮስ በመጣ ጊዜ ከሽማግሌዎች ምክር ቤት የተላኩት ሦስት ሰዎች ለንጉሡ ክሳቸውን አቀረቡ።

45 መነላዎስ እንደሚረታ አውቆ ለጰጠሎሜዮስ ልጅ ለይሪመን ከንጉሡ እንዲያማልደው ብሎ ብዙ ወርቅ ሰጠው።

46 ስለዚህ ጰጠሎሜዮስ ንጉሡ ነፋስ እንዲቀበል ብሎ ወደ ውጪ ወሰደውና መክሮ ፍርድ እንዲለውጥ አደረገው።

47 በዚህ ዓይነት ንጉሡ ብዙ ክፋት የሠራው መነላዎስን ከክሱ ነጻ አድርጐ ለቀቀው፤ ምስኪኖቹ ግን ሞት ፈረደባቸው፤ እነዚህ ምስኪን ሰዎች ጨካኞች ለተባሉት ለሲጢ ሰዎች እንኳ አቤት ቢሎ ኖሮ ነጻ በተለቀቁ ነበር።

48 ከተማዋንና አካባቢዎችዋን፥ የተቀደሱ ዕቃዎችንም ለማዳን የተከላከሉት ሰዎች የግፍ ፍርድ ወደቀባቸው።

49 የጢሮስ ሰዎች እንኳ በጣም አዝነውላቸው በደንብ እንዲቀበሩ አደረጓቸው፤

50 መነላዎስ ግን በባለሥልጣኖች ገንዘብ ወዳድነት ምክንያት በክፋቱ እየገፋ ሄዶ ተሾመ፤ ሥልጣን አገኘ፤ ለሀገሩ ሰዎችም ትልቅ ጠላት ሆነ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች