Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ

- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የሄልዮድሮስ ታሪክ፥ የሄልዮድሮስ ወደ ኢየሩሳሌም መድረስ

1 በዚያን ጊዜ የቅድስት ከተማ ነዋሪዎች በተደላደለ ሰላም ይኖሩ ነበር፤ ሊቀ ካህናትቱ ኦንያ መንፈሳዊና ክፋትን የሚጠላ ስለ ነበር።

2 ነገሥታቱም ሳይቀሩ ቅዱሱን ቦታ ያከብሩ ነበር፤ ለቤተ መቅደስም እጅግ ከፍ ያሉ እጅ መንሻዎች ያቀርቡ ነበር።

3 እንዲያውም የእስያ ንጉሥ ስለወቀሰው ለመሥዋዕት አገልግሎት የሚያስፈልገውን ከግል ገንዘቡ ወጪ እስከማድረግ ደርሶ ነበር።

4 ነገር ግን ከቢልጋ ነገድ የሆነው፥ የቤተ መቅደሱ አስተዳዳሪ ሆኖ የተሾመው ሰምዖን የተባለ ሰው ስለ ከተማይቱ ሕግ ጉዳይ ከሊቀ ካህናቱ ጋር ሳይስማማ ቀረ።

5 ኦንያን ማሸነፍ ስላልቻለ በዚያን ጊዜ የቀለስርያና የፌኒቄስ ሹም ወደነበረው ወደ ተረስያ ልጅ ወደ አጶሎበንዮስ ሄደ፤

6 በኢየሩሳሌም ግምጃ ቤት ውስጥ ተቆጥሮ የማይዘለቅ ሀብት መኖሩንና ይህም ሀብት መኖሩንና ይህም ሀብት ለመሥዋዕቶች ከሚወጣው ገንዘብ ጋር የማይደባለቅ መሆኑን በተጨማሪም ይህን ሀብት ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ማስገባት የሚቻል መሆኑን ነገረው።

7 አጶሎንዮስ ለመነጋገር ወደ ንጉሡ በገባ ጊዜ ስለዚህ ሀብት ጉዳይ የተነጋገረውን ገለጸለት፤ ንጉሡ ጠቅላይ አስተዳዳሪውን ሄልዮድሮስን መርጦ ይህንን ሀብት እንዲያመጣ በማዘዝ ላከው።

8 ሄልዮድሮስ የቀላሱርያንና የፊኒቴን ከተሞች ለመጐብኘት የሚሄድ አስመስሎ በፍጥነት ሄደ፤ የሄደው ግን የንጉሡን ትዕዛዝ በሥራ ላይ ለማዋል ነበር።

9 ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜና በከተማው ውስጥ ሊቀ ካህናቱ የወዳጅነተ አቀባበል ባደረገለት ጊዜ ስለ ሀብቱ ጉዳይ የተነገረውንና እርሱም የመጣበትን ምክንያት ገለጸለት፤ ጉዳዩ እውነት ነው? ሲል ጠየቀው።

10 ሊቀ ካህናቱ “ግምጃ ቤት ውስጥ ያለው ገንዘብ ለመበለቶችና ለሙት ልጆች የተቀመጠ ነው” ብሎ መለሰለት፤

11 “እንዲሁም በከፍተኛ ቦታ ላይ ስምዖን እንደ ተናገረው ሳይሆን በጠቅላላው ያለው ገንዘብ አራት መቶ የብር መክሊትና ሁለት መቶ የወርቅ መክሊት ነው።

12 በተረፈ ሰዎች በአደራነት በተቀደሰው ቦታ ያስቀመጡትን መንካት በፍጹም የማይቻል ነው፤ ይህም በመላው ዓለም የተከበረው ቤተ መቅደስ እጅግ ታላቅና የማይደፈር በመሆኑ ነው” አለው።


ጭንቀት በኢየሩሳሌም

13 ሄልዮድሮስ ግን ከንጉሡ በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት እነዚህ ሀብቶች ተወርሰው ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት መግባት አለባቸው ብሎ ቆረጠ።

14 በተወሰነው ቀን ሀብቶቹን ለማየትና ለመቁጠር ገባ፤ በዚያን ጊዜ በመላው ከተማ ትልቅ ሁከት ሆነ።

15 ካህናት የክህነት ልብሶቻቸውን ለብሰው በመሠዊያው ፊት ተደፍተው በአደራነት ያስቀመጡ ሰዎች ገንዘባቸው እንዳይነካባቸው ጸሎት በማድረግ የአደራ አስቀማጭነትን ሕግ ወዳወጣው አምላክ ልመናቸውን ያቀርቡ ነበር።

16 የሊቀ ካህናቱን ፊት የተመለከተ ሁሉ ልቡ በኀዘን ሳይቆስል የቀረ የለም፤ የፊቱ መጐሳቆል የልቡን ኀዘን የሚያመለክት ነበር።

17 በመላው ሰውነቱ፥ በእርሱ ላይ የነበረው ፍርሃትና መንቀጥቀጥ ለሚመለከተው ሰው ሁሉ የሰውዬውን የልብ ጭንቀት የሚገልጽ ነበር።

18 ይህ የተቃጣው ውርደት ከቅዱስ ቦታ እንዲወገድ በኀብረት ለመጸለይ ሰዎች ተሰብስበው ከየቤታቸው ይወጡ ነበር።

19 ሴቶች የተለተለ ልብስ አሸርጠው መንገዶቹን ሞልተው ነበር፤ በቤት የቀሩ ልጃረገዶች፤ አንዳንዶቹ ወደ በሮች፤ አንዳንዶቹ ወደ ግንቦች አጥር እየሮጡ፤ አንዳንዶቹም በየመስኮቱ ብቅ እየሉ

20 ሁሉም ወደ ሰማይ እጆቻቸውን ዘርግተው ይጸልዩ ነበር

21 የተሰበሰበው ሕዝብ በምድር ላይ ተደፍቶ ሊቀ ካህናቱም በታላቅ ጭንቀት ተይዞ ማየት የሚያሳዝን ነበር።

22 ሰዎቹ በአደራነት ያስቀመጡትን ገንዘብ ማንም ሳይነካው ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር እንዲጠብቀው ጸሎት በሚደረግበት ጊዜ

23 ሄልየድሮስ የታዘዘውን በመፈጸም ላይ ነበር።


የሄልዮድሮስ ቅጣት

24 ሄልዮድሮስ ከወታደሮቹ ጋር ሆኖ ግምጃ ቤቱ አጠገብ ነበር። በዚያን ሰዓት የመናፍስትና የኃያላት ሁሉ ጌታ ታየና ሄልዮዶሮስን ለማጀብ ወደዚያ የመጡትና የደፈሩት ሰዎች ሁሉ በአምላክ ኃይል ተመቱ፤ ኃይላቸውና ብርታታቸውም ጠፋ።

25 አንድ ፈረስ ታያቸው፤ ፈረሱ በጌጠኛ የፈረስ ዕቃ ተሸልሞ ነበር። በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ሰው እጅግ አስደንጋጭ ነበር። ፈረሱ በኃይል ወደ ፊት ዘለለና በፊት እግሮቹ ሄልዮድሮስን መታው፤ በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ሰው የወርቅ የጦር መሣሪያ የያዘ ይመስል ነበር።

26 በዚያኑ ጊዜ ሁለት ጐልማሶች ለሄልዮድሮስ ታዩት፤ ታላቅ ኃይልና ታላቅ ውበትም ነበራቸው፤ እጅግ ያማረ ልብስም ለብሰው ነበር። በሂልዮድሮስ ግራና ቀኝ ሆነው ያለማቋረጥ ይገርፉት ነበር፤ ግርፋቱን እንደ በረዶ ያወርዱበት ነበር።

27 ሄልዮድሮስ ወዲያውኑ በምድር ላይ ወደቀ፤ ጥቅጥቅ ያለ ጨለማም ለበሰ፤ ሰዎች አንስተው በወሳንሣ ላይ አስቀመጡት፤

28 ተሸክመውም ወሰዱት። ይህ ሰው ከጥቂት ጊዜ በፊት በብዙ ሰዎችና ወታደሮች ታጅቦ ወደ ተባለው ግምጃ ቤት ገብቶ ሰዎች ተሸክመው ወሰዱት።

29 ይህ ሰው እንግዲህ በእግዚአብሔር ኃያልነት መናገር ተስኖት፥ ተስፋ ቆርጦ የሚረዳውም አጥቶ ተጋድሞ ነበር።

30 አይሁዶች ግን ቅዱስ ቦታውን በተአምር ያከበረውን እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር፤ ከጥቂት ጊዜ በፊት በፍርሃትና በችግር ተሞልቶ የነበረው ቤተ መቅደስ ሁሉን የሚል እግዚአብሔር በፍርሃትና በችግር ተሞልቶ የነበረው ቤተ መቅደስ ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር በመገለጹ በደስታ ተሞላ።

31 ከሂልዮድሮስ ወዳጆች አንዳንዶቹ ወደ ኦንያ ሮጠው ሄዱና ይህን የተጋደመውንና ሊሞት የታቀረበውን ሰው ሁሉን የሚችል አምላክ እንዲያድነው ጸልዩለት ሲሉ ለመኑት።

32 ንጉሡ አይሁዳውያን በሂልዮድሮስ ላይ ክፉ መሥዋዕት አቀረረበ።

33 ሊቀ ካህናቱ የስርየት መሥዋዕት ሲያቀርቡ ሳለ እነዚያ ጐልማሶች ያንኑ ልብሳቸውን ለብሰው እንደገና ለሂልዮድሮስ ታዩት፤ በአጠገቡ ቆመውም፤ “ሊቀ ካህናቱን ኦንያን በጣም አመስግን፤ ምክንያቱም በእርሱ ምክንያት ነው እግዚአብሔር ሕይወትህን ያዳናት፤

34 በአምላክ የተገረፍህ አንተ ግን ሂድና ታላቁን የአምላክ ኃይል ተናገር” አሉት፤ ይህን ከተናገሩ በኋላ ተሠወሩ። የሄልዮድሮስ መለወጥ

35 ሄልዮድሮስ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ካረቀበና ሕይወቱን ላተረፈለት አምላክ ብዙ ስእለት ካደረገ በኋላ ኦንያን በወዳጅነትና በፍቅር ተሰናብቶ ከነሠራዊቱ ወደ ንጉሡ ተመለሰ።

36 የታላቁን እግዚአብሔር ሥራና እግዚአብሔርንም በዐይኖቹ ማየቱን በሰዎች ሁሉ ፊት መሰከረ።

37 ንጉሡ ሄልዮድሮስን፥ “ወደ ኢየሩሰሌም እንደገና ለመላክ ብቁ የሆነ ማነው” ብሎ ቢጠይቀው እሱም እንዲህ ሲል መለሰለት፤

38 “የአንተ ጠላት የሆነና በመንግሥትህም ላይ የሚዶልት ሰው ካለ እርሱን ላከው፤ በዚያ ቦታ ላይ የአምላክ ኃይል ስላለ የሚላከው ሰው ተገርፎ ይመለስልሃል፤ ያውም ሕይወቱ የተረፈ እንደሆነ ነው።

39 ምክንያቱም ይህን ቦታ በሰማይ የሚኖረው አምላክ ይጠብቀዋል፤ ክፉ ለማድረግ አስበው ወደዚያ የሚሄዱትን ሰዎች ይመታቸውና ያጠፋቸዋል።”

40 የሄልዮድሮስ ነገርና ግምጃ ቤቱም ምንም አለመነካቱ የተፈጸመው በዚህ ዓይነት ነው።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች