ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ 2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ኤርምያስ ድንኳኑን፤ ታቦቱን፤ መሠዊያውን ደበቀ 1 ነቢዩ ኤርምያስ ተማርከው የሚሄዱትን ሰዎች ከላይ እንደተመለከተው እሳት ይዘው እንዲሄዱ ያዘዛቸው መሆኑ በመጽሐፍ ይገኛል፤ 2 እንዲሁም ነቢዩ የእግዚአብሔርን ሕግ ከሰጣቸው በኋላ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንዳይረሱ የወርቅና የብር ምስሎችን የለበሱትንም ጌጣጌጥ በማየት ልባቸው ከእግዚአብሔር እንዳይርቅ አደራ ብሏቸዋል። 3 ይህንኑ ዓይነት ምክር ከሰጣቸው በኋላ የእግዚአብሔርን ሕግ ከልባቸው እንዳያርቁ መክሯቸዋል። 4 ነቢዩ እግዚአብሔር በነገረው መሠረት ድንኳኑንና ታቦቱን ይዞ ሙሴ ወደ ወጣበትና እዚያ ሆኖ የእግዚአብብሔርን ርስት ወደ ተመለከተበት ተራራ ላይ መውጣቱ በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ ተነግሮአል፤ 5 ኤርምያስ እዚያ ከደረሰ በኋላ የዋሻ ቤት አግኝቶ ድንኳኑንና ታቦቱን፥ የዕጣን መሠዊያውንም እዚያ አስቀመጠ። ከዚህ በኋላ መግቢያውን ጥርቅም አድርጐ ዘጋ። 6 ከጓደኞቹ አንዳንዶቹ እርሱ በሄደበት ሄደው መንገዱን ምልክት ሊያደርጉበት ፈለጉ ግን ሊያገኙት አልቻሉም። 7 ኤርምያስ ይህን በሰማ ጊዜ ገሠጻቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “እግዚአብሔር ሕዝቡን እስኪሰበስብና ምሕረቱን እስኪያሳያቸው ድረስ ይህ ቦታ ሥውር ሆኖ ይቆያል። 8 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር እነዚህን ዕቃዎች ገልጾ ያሳያል፤ በሙሴ ጊዜና ሰሎሞን ቤተ መቅደሱ በክብር እንደቀደስ በጸለየ ጊዜ እንደታየው ዓይነት የእግዚአብሔር ክብርም ከደመናው ጋር ይታያል”። 9 ሰሎሞን ጥበበኛ ሆኖ ቤተ መቅደሱ ሲቀደስ በጥበብ መሥዋዕቱን እንዴት እንደቀረበና የቤተ መቅደሱም ሥራ እንዴት እንደ ተፈጸመ ተነግሮአል። 10 ሙሴ ወደ እግዚአብሔር በጸለየ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ መሥዋዕቱን እንዳቃጠለ እንዲሁም ሰሎሞን ጸልዮ ከሰማይ የወረደው እሳት መሥዋዕቱን አቃጠለው። 11 “በኃጢአት ምክንያት የሚቀርበው መሥዋዕት ስላልተበላ በእሳት ተቃጥሎ አለቀ” ብሎ ሙሴ ተናግሮ ነበር፤ 12 እንዲሁ ሰሎሞንም ስምንት ቀን በዓል አደረገ። የነህምያ ቤተ መጻሕፍት 13 በዚሁ መጽሐፍና ነህምያ በጻፋቸው ማስታወሻዎች እነዚህ ነገሮች ተነግረዋል፤ ነህምያ ቤተ መጻሕፍት አቋቁሞ ስለ ነገሥታትና ስለ ነቢያት የሚናገሩትን መጻሕፍት፤ የዳዊትን መጻሕፍትንና ስለ መሥዋዕቶች የሚናገሩትን የነገሠታት ደብዳቤናዎች እዚያ መሰብሰቡ ተነግሮአል። 14 እንዲሁም ይሁዳ በተደረገብን ጦርነት ምክንያት የተበታተኑትን መጻሕፍት ሁሉ ሰብስቧል፤ በእጃችን ይገኛሉ። 15 የሚያስፈልጋችሁ ከሆነ የሚያመጡላችሁን ሰዎች ወደ እኛ ላኩ። የተሐድሶን በዓል ለመካፈል የቀረበ ጥሪ 16 ይህን ደብዳቤ የጻፍንላችሁ የቤተ መቅደሱን መንጻት በምናከብርበተ ጊዜ ነው፤ እናንተም እነዚህን ቀኖች ብታከብሩ መልካም ነው። 17 ሕዝቡን የዳነና ለሁሉም ርስትን፤ መንግሥትን፤ ክህነትን፥ ቅድስናን የሰጠ አምላክ፤ 18 እርሱ በኦሪት ሕግ ተስፋ ሰጥቶን እንደ ነበር ተስፋ የጣልንበትን ይህ አምላክ ይራራልናል፤ ከሰማይ በታች ካሉ አገሮች ወደተቀደሰው ቦታ ይሰበስበናል፤ ምክንያቱም እርሱ ከታላላቅ ጭንቆች አውጥቶናል። ቅዱሱንም ቦታ (ቤተ መቅደሱንም) አንጽቷል። የአዘጋጁ መቅድም 19 ስለ ይሁዳ መቃቢስና ወንድሞቹ፤ ስለ ታላቁ ቤተ መቅደስ፥ ሰለ መሠዊያው መቅደስ፤ 20 እንዲሁም በአንጥዮኩስ ኤጲፋኔስና በልጁ በኤውጳጥሮስ ላይ ስለተደረጉት ጦርነቶች፤ 21 ስለ አይሁድ ሕዝብ በጀግንነት ለተዋጉት ምንም እንኳን ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም፤ አገሩን ሁሉ ዘርፈው አረመኔውን ሕዝብ ላባረሩ ሰዎች ስለታያቸው ብርሃንና፤ 22 በመላው ዓለም የታወቀውን ቤተ መቅደስ ያስመለሱትን፤ ከተማዋን ነጻ ያወጡ እግዚአብሔር በታላቅ ምሕረቱ ራርቶላቸው ለመደምሰስ የቀረቡትን ሕጐች መልሰው ያቋቋሙ ስለእነርሱና፤ 23 ቀሬናዊው ኢያሱ በአምስት መጻሕፍት ውስጥ ስለጻፋቸው ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ አሳጥረን ባንድ መጽሐፍ ለማጠቃለል እንሞክራለን። 24 የቁጥሩን ብዛትና ታሪኩን ለማወቅ በሚፈልጉ ሰዎች ላይ ከነገሩ ብዛት የተነሣ የሚወድቀውን ችግር በማሰብ፤ 25 ሊያነቡት የሚፈልጉትን ሰዎች እንዲያስደስታቸው፤ የሚማሩት ሰዎች በቀላሉ እንዲያጠኑት፤ ለሚያነቡትም ሁሉ ጥቅም እንዲሰጣቸው በማለት ተጋንበት። 26 ባጭሩ ለመጻፍ አሰቸጋሪውን ሥራ ለተቀበልነው ለእኛ ቀላል ነገር አይደለም፤ ላብ ማንጠፍጠፈንና ታላቅ ትጋትን (እንቅልፍ ማጣትን) የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። 27 ይህ አስቸጋሪ ሥራ ሰዎችን ለማገልገል ብለን ይህን ከባድ ሥራ ወደን ተቀብለናል፤ 28 ነገሮቹን ሁሉ ተጠንቅቆና አሳምሮ ለጻፈው ለመጀመሪያው ጸሐፊ ትተን እኛ በአጠቃላይ በአጭሩ ለመጻፍ እንሞክራለን። 29 የአዲስ ሕንፃ ሥራ በሙሉ ዋናውን አናጺ እንደሚመለከትና ቀለም ቀቢው ሕንጻውን ለማስጌጥ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ መሰብሰብ እንደሚያሻው የእኛም ሥራ እንዲሁ ዓይነት ይመስለኛል። 30 በጉዳዩ ጠልቆ መግባት፤ ዙሪያውን መመልከት፤ እያንዳንዱን ሥራ በጥንቃቄ መመርመር የታሪኩን ጸሐፊ የሚመለከት ነው። 31 ነገር ግን ነገሩን ሳያስፋፋ ባጭሩ መግለጽ የሚመለከተው ጸሐፊውን ነው። 32 አሁን እንግዲህ እስካሁን ከተባለው ይበልጥ ምንም ሳንጨምር ታሪኩን እንጀምራለን፤ ምንያቱም መቅድሙን አስፍቶ ማብራራት ፋይዳ የሌለው ከመሆኑም በላይ ታሪኩን እራሱን ያሳጥረዋል። |