ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ 2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 15 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ኒቃኖር በእግዚአብሔር ላይ ጸያፈ ቃል ተናገረ 1 ኒቃኖር ይሁዳና የእርሱ ሰዎች በሰማርያ አካባቢ እንደሚገኙ ሰምቶ በሰንበት ቀን ያለ ምንም ፍርሃት ጦርነት ሊገጠማቸው ውሳኔ አደረገ፤ 2 ተገድደው ይከተሉበት የነበሩ አይሁዳውያን እንዲህ አሉት፥ “በእንዲህ ዓይነት አረመኔነትና ጭካኔ አታጥፋቸው፤ ሁሉን የሚያይ አምላክ ያከበረውንና የቀደሰውን ቀን አክብር”። 3 ይህ ባለ ሦስት ቀለሙ ክፋና ጨካኝ ሰው ግን፥ “ለመሆኑ ሰንበት ቀን እንዲከበር ያዘዘ በሰማይ ጌታ አለን?” ሲል ጠየቀ፤ 4 “በሰባተኛው ቀን እንዲከበር ትእዛዝ የሰጠ የሰማየ ጌታ ሕያው እግዚአብሔር ነው” ሲሉ መለሱለት፤ 5 እርሱም “እኔም እኮ የምድር ጌታ ሆኜ ሰዎች የጦር መሣሪያ እንዲያነሡና ንጉሡን እንዲያገለግሉ አዛለሁ” በማለት አሾፈ፤ ሆኖም የጭካኔ እቅዱን በሥራ ላይ ማዋል አልቻለም። ይሁዳ ለሰዎቹ ንግግር አደረገ፥ ሕልምም አየ 6 ኒቃኖር በታላቅ ትዕቢት ተነሣሥቶ ይሁዳንና የእርሱን ሰዎች በማሸነፈ የአሸናፊነት ምልክት ማቆመ ፈለገ፤ 7 ይሁዳ መቃቢስ በበኩሉ የማይበገር እምነት ነበረው፤ ከእግዚአብሔር እርዳታ እንደሚያገኝ ሙሉ ተስፋ ነበረው። 8 የአሕዛብ ሰዎች ጥቃት ቢሰነዝሩባቸው እንዳይፈሩ ነገር ግን ቀደም ሲል ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን እርዳታ እንዲያስታውሱ አሳሰባቸው፤ በኃያሉ አምላክ ድል የሚመጣላቸው መሆኑን እንዲጠባበቁም መከራቸው። 9 የሙሴን ሕግና ነቢያትን በመጥቀስ አበረታታቸው፤ ከዚህ ቀደም ያደረጉትን ጦርነትም በማስታወሰ አዲስ ጥንካሬ አሳደረባቸው። 10 በዚህ ዓይነት ከነቃቃቸው በኋላ አረማውያን ሕግ የማይጠብቁና መሐላቸውንም የሚያፈርሱ መሆናቸውን አስረድቶ ምክሩን አቆመ። 11 በጦርና በጋሻ ብቻ ሳይሆን ያስታጠቃቸው እያንዳንዳቸውን በመልካም ምክሩም አበረታታቸውና አንድ የታመነ ሕልም እንዲያውም እውነተኛ ራእይ ማየቱን አውርቶላቸው ሁሉንም አስደሰታቸው። 12 ያየውም ራእይ እንዲህ ነበር፥ አንድ በፊት ሊቀ ካህናት የነበረ የዋህና ደግ ሰው፥ መልኩ ግሩም፥ ሁኔታው ያማረ፥ አነጋገሩ መልከም የሆነ፥ ከልጅነቱ ጀምሮ በጽድቅ ሥራ የተጠመደ ስለ መላው የአይሁድ ሕዝብ እጆቹን ዘርግቶ ሲጸልይ አየ፤ 13 ቀጥሎም እንዲሁ አንድ ሽበታም ሰው እጅግ ክቡር የሆነ፥ ድንቅ የሆነ ግርማ ያለውና እጅግ ውብ የሆነ ሰው ለይሁዳ ታየው። 14 ኦንያ እንዲህ ሲል መለሰለት፥ “ይህ ሰው ወንድሞቹን የሚወድ ነው፤ ስለሕዝቡና ስለ ቅድስቲቱ ከተማ ብዙ ጸሎት የሚያደርግ የእግዚአብሔር ነቢይ ኤርምያስ ነው”፤ 15 ኤርምያስ በቀኝ እጁ የወርቅ ሰይፍ ለይሁዳ አቀረበለትና፥ 16 “እንካ ይህን የተቀደሰ ሰይፍ የአምላክ ስጦታ ነው፤ በእርሱ ጠላቶች ትጥላለህ አለው።” የተዋጊዎቹ ዝግጅት 17 ይሁዳ በተናገራቸው መልካምና በጀግነት በሚያነሣሡ፥ ለወጣቶችም በወንድነት ለመዋጋት ብርታት የሚሰጡ ቃላት ተጠናክረው አይሁዳውያን በሠፈር መቆየት ሳይሆን በድፈረት ወደ ጦርነት ለመሄድና በኃይል ለመዋጋት ቆረጡ፤ ምክንያቱም ከተማቸው፥ ሃይማኖታቸውና ቤተ መቅደሳቸው በአደጋ ላይ በመገኘታቸው ነው። 18 ስለ ሴቶችና ስለ ልጆች፥ ስለ ወንድሞችና ስለ ዘመዶች እምብዛም አልተጨነቁም ነበር፤ ያሳሰባቸውና የስፈራቸው የቤተ መቅደሱ ጉዳይ ነበር። 19 በከተማው ውስጥ የነበሩት ሰዎች ጭንቀት ትንሽ አልነበረም፤ ጭንቀታቸው በመካሄድ ላይ ስላለው ጦርነት ነበር። 20 ሁሉም እንግዲህ የነገሩን ፍጻሜ በመጠባበቅ ላይ እያሉ ጠላቶች ተሰብስበው ሠራዊታቸውን ለጦርነት በማሰለፍ ላይ ነበሩ፤ ዝሆኖቹን በምቹ ቦታ አድርገዋቸው ነበረ፤ ፈረሶችም በጐን በኩል ነበሩ። 21 ይሁዳ መቃቢስ የወታደሮቹን መቃረብ፥ ልዩ ልዩ የጦር መሣሪያዎቻቸውን ዝግጅትና የዝሆኖቹን አስፈሪነት ተመለከተ። እጆቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ ታምራትን ለሚያደርገው አምላክ ልመና አቀረበ፤ ምክንያቱም ማሸነፍ የሚቻለው በጦር መሣሪያ አለመሆኑንና ድል የሚገኘው በአምላክ ውሳኔና እሱ ድልን ለሚገባቸው ሰዎች ሲሰጥ ብቻ መሆኑን አወቀ። 22 ልመናውም እንዲህ ነበር፥ “አንተ ጌታ ሆይ በይሁዳ ምድር ንጉሥ በነበረው በሕዝቅያስ ዘመን መልአክህን ልከሀል፤ ከሰናክሬም ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰዎችን መልአኩ ገድበሏቸዋል። 23 እንዲሁም አሁን የሰማያት ጌታ ሆይ ፍርሃትንና መንቀጥቀጥን የሚያወርድባቸው መልአክ ላክልን። 24 የተቀደሰውን ሕዝብህን ለመውጋት እየተሳደቡ የመጡትን ሰዎች ታላቁ ክንድህ ይደቁሳቸው”። ጸሎቱን እዚህ ላይ አቆመ። የኒቃኖር መሸነፍና መሞት 25 የኒቃኖር ወታደሮች መለከት እየነፉና የጦር መዝሙር እየዘመሩ ወደፊታቸው በሚገሰግሱበት ጊዜ፥ 26 የይሁዳ ሰዎች በልመናና በጸሎት ከጠላቶቻቸው ጋር ጦርነት ገጠሙ። 27 በእጃቸው እየተዋጉና በልባቸው እየጸለዩ ከሠላሳ ሺህ ሰዎች የማያንሱ ገድለው ጣሉ፤ የእግዚአብሔርም መገለጽ በጣም አስደሰታቸው። 28 ጦርነቱን ፈጽመው በደስታ ሲመለሱ ኒቃኖር ከጦር መሣሪያው ወድቆ አገኙትና አወቁት። 29 ከእዚህ በኋላ በአባቶቻቸው ቋንቋ ታላቁን ጌታ እያመሰገኑ በታላቅ ድምፅ እልል ይሉ ጀመር፤ 30 በመጀመሪያ ደረጃ ሥጋውንና ነፍሱን ስለ ሀገሩ የሠዋው የጦር መሪ የሀገሩን ሰዎች በጣም ያፈቀረው ይሁዳ የኒቃኖርን ራሱንና ክንድን እስከ ትከሻው ቆርጠው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲወስዱ አዘዘ። 31 እርሱ ራሱም ወደ ኢየሩሳሌም ሄደና የሀገሩን ሰዎች ሰብስባ፥ ካህናትንም በመሠዊያው ፊት አቆመ፤ በምሽጉ ውስጥ የነበሩትነም እንዲጠሩ አዘዘ። 32 የዚያን የክፉ ሰው የኒቃኖርን ራስና ሁሉን በሚችል አምላክ ቤተ መቅደስ ላይ ያ ተሳዳቢ የዘረጋውን እጁን አሳየ፤ 33 የዚያን የክፉ ሰው የኒቃኖርን ምላስ ጐምዶ እየቆራረጠ ለወፎች እንዲሰጥና ስለ ፈጸመው በደል ሁሉ ዋጋው ይሆን ዘንድ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት እንዲሰቀል አዘዘ። 34 ይህን በሰሙ ጊዜ ሁሉም ወደ ሰማይ ለክቡር ጌታ ምስጋና አቀረቡ፥ “ቅዱስ ቦታውን ከመርከስ የጠበቀ አምላክ ይባረክ” አሉ። 35 ይሁዳ የእግዚአብሔርን እርዳታ ግልጽ አድርጐ የሚያሳይ ምልክት የሆነውን የኒቃኖርን ራስ በመሽጉ ላይ አሰቀለው። 36 ሁሉም በአንድ ቃል አብረው ይህ ቀን ሳይከበር እንዳይታለፍ ሲሉ ወሰኑ፤ ቀኑም በአረማይክ ቋንቋ (በሶሪያ) አዳር የተባለው የዐሥራ ሁለተኛው ወር ዐሥራ አንደኛው ቀን የመርዶክዮስ ቀን ነው። የጸሐፊው መደምደሚያ 37 የኒቃኖር ነገር እንዲህ ተፈጸመ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዕብራውያን ከተማዋን ይዘው ቀሩ። እኔም ሥራዬን በዚሁ ፈጸምሁ። 38 ዜናው መልካምና የተሳካ ሆኖ ከተገኘ የእኔም ምኞት ይኸው ነው፤ ጽሑፉ ዋጋ ቢስ ከሆነና ለጥቅስ ካልበቃ አቅሜ የፈቀደው ይሄን ብቻ ነው። 39 የወይን ጠጅ በደረቁ ቢጠጣ እንደሚጐዳ ሁሉ ውሃም ለብቻው አይወሰድም፤ ነገር ግን የወይን ጠጅ ከውሃ ጋር በተቀላቀለ ጊዜ ጣፋጭና የደስታን ስሜት የሚፈጥር ነው። እንደዚሁ ሁሉ የተለያዩ አጋጣሚዎችን በተገቢው መልክ የማቅረብ ችሎታ መጽሐፉን ለሚያነቡ ሁሉ የግንዛቤን ደስታ ይሰጣል። እኔም ጽሑፌን በዚህ አበቃለሁ። |