Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 14 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ከዲሜጥሮስ የጦር አዛዥ ከዚቃኖር ጋር የተደረገ ግጭት የኒቃኖር ቀን የሊቀ ካህኑ አልቂሞስ ጣልቃ መግባት

1 ከአምስት ዓመት በኋላ የሰላውቂስ ልጅ ዲሜጥሮስ ከብዙ ወታደሮችና መርከቦች ጋር ወደ ትሪፖሊ ጠረፍ መድረሱንና

2 አገሩንም ይዞ አንጥዮኩስንና መምህሩን ሊስያስን መግደሉን ይሁዳና የእርሱ ሰዎች ሰሙ።

3 አንድ አልኒቀውስ የተባለ ሰው በፊት ሊቀ ካህናት ሆኖ የነበረ፥ በግርግሩ ጊዜ በፈቃዱ የረከሰ፥ በምንም ዓይነት ደኀንነት እንደማይኖረው አውቆ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ወደተቀደሰው መሠዊያው መቅረብ እንደማይችል ተረድቶ

4 ወደ 151 ዓመተ ዓለም ገደማ ወደ ንጉሥ ዲሜጥሮስ ሄደና የወርቅ አክሊል ከዘንባባ ጋር አቀረበለት፤ ከዚህም በላይ በቤተ መቅደስ እንደተለመደው የወይራ ዝንጣፊ አቀረበለትና በዚያን ቀን ምንም ሳይናገር ዝም ብሎ ዋለ።

5 ዲሜጥሮስ ወደ ምክር ቤቱ ጠርቶት የአይሁዳውያንን ሁናቴና ሐሳብ በጠየቀው ጊዜ የማይጨበጠውን እቅዱን ለመግለጽ ጊዜ አገኘ፤ እንዲህም ሲል መለሰ፥

6 “ይሁዳ መቃቢስ የሚመራቸው አሲዳውያን የሚባሉ አይሁዳውያን ጦርነትና ሁከትን ያነሣሣሉ፤ መንግሥት በጸጥታ እንዲኖር አይተውም።

7 ስለዚህ ከአባቶች የወረስኩትን የሊቀ ካህናትነት ክብሬን ተገፍፌ ወደዚህ መጣሁ፤

8 ወደዚህ የመጣሁበትም በመጀመሪያ በእውነት ለንጉሥ የሚያስፈልጉትን ገነሮች በማሰብ ቀጥሎም እነዚያ ክፉ ሰዎች ሕዝባችን በታላቅ ችግር ውስጥ ስለ ጨመሩት ሰለ ሕዘቤ በማሰብ ነው።

9 ስለዚህ አንተ ንጉሥ ሆይ እያንዳንዱን ነገር ባወቅህ ጊዜ እባክህ ስለ ሀገራችን ስለ ተቸገረው ሕዝባችን ለሁሉም በምታደርገው በተወደደው ደግነትህ አስብ፤

10 ምክንያቱም ይሁዳ በሕይወት እስካለ ድረስ መንግሥትህ ሰላምን ማግኘት አይችልም።”

11 ንግግሩን ባቆመ ጊዜ ወዲያውኑ ሌሎቹ የንጉሡ ወዳጆች የይሁዳን ሥራ በማጥላላት ንጉሡን ዲሜጥሮስን ለማነሣሣት ተጣደፉ።

12 ወዲያውኑ የዝሆኖች አለቃ የነበረው ኒቃኖርን ጠርቶ የይሁዳ ምድር ገዥ አደረገውና ላከው፤

13 ይሁዳን እንዲያጠፋና ከእርሱ ጋር ያሉትን እንዲበታትን አለቂሞስንም የታላቁ ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህናት አድርጐ እንዲሾመው አዘዘ።

14 ከይሁዳ ሸሽተው የነበሩ የይሁዳ ምድር አረማውያንም ከኒቃኖር ወታደሮች ጋር ተደባለቁ (አብረው ሆኑ)፤ የአይሁዳውያን ጭንቅና መከራ ለእነርሱ የሚበጅ ነው ብለውም አስበው ነው።


ኒቃኖር የይሁዳ ወዳጅ ሆነ

15 አይሁዳውያን የኒቃኖርን መቃረብና የአረማውያንን አብረው መምጣት በሰሙ ጊዜ በራሳቸው ላይ አመድ ነስንሰው ሕዘቡን ለዘወትር ያኖረና በሚታዩ ተአምራተ ርስቱን ለመርዳት የማያቋርጠውን አምላክ ይለምኑ ጀመር።

16 በአለቃቸው ትእዛዝ መሠረት ከነበሩበት ቦታ በቶሎ ሄዱና በዴሳው መንደር አጠገብ ከጠላት ጋር ጦርነት ገጠሙ።

17 የይሁዳ ወንድም ስምዖን ከኒቃኖር ጋር ጦርነት ገጥሞ ነበር፤ ግን ጠላቶች በድንገት በመምጣታቸው ጥቂት እንደ መረበሽ አለ።

18 ሆኖም ኒቃኖር የይሁዳ ወታደሮች ብርታት ምን መሆኑን፥ ስለ ሀገራቸው ሊዋጉ ያላቸውን ድፍረት ስላወቀ ነገሩ በደም መፋሰስ ይፈታል የሚል ግምት አልነበረውም።

19 ስለዚህ የሰላም እጁን ለአይሁዳውያን ለመዘርጋትና እነርሱም እንዲጨብጡ ብሎ ጶሊየንን፥ ቴዎዱትንና ማታትያስን ላከባቸው።

20 ስለዚህ በቀረቡት ሐሳቦች ላይ ብዙ ውይይት ከተደረገ በኋላ የጦር መሪው ለወታደሮቹ አስታወቀ፤ በጉዳዩ ስለተስማሙ ውሉን ለመቀበል እሺ ማለታቸውን ገለጹ።

21 የጦር አለለቆች በተለይ የሚገናኙበት አንድ ቀን ወሰኑ፤ ከዚህም ከዚያም መቀመጫ ተሰጠ፤ የክብር ወንበሮችም ተዘጋጁ።

22 ይሁዳ ምናልባት በድንገት ከጠላት በኩል ክፉ ነገር ቢመጣ የሚደርሱ የጦር መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች በምቹ ቦታዎች አዘጋጅቶ ነበር፤ ግን ንግግሩ በመልካም ተፈጸመ።

23 ኒቃኖር ምንም ክፉ ነገር ሳያደርግ በኢየሩሳሌም ሰነበተ፤ በእርሱ ዙሪያ ተሰብስበው የነበሩትንም አረማውያን አሰናበተ።

24 ለይሁዳ ልቡን ሰጥቶ ከእርሱ ምንም አልተለየም።

25 ሚስት እንዲያገባና ልጆች እንዲወልድ ይሁዳን ለመነው፤ ሚስት አገባ፤ ተገቢውን ሕይወት ለመምራት ተደላድሎ ተቀመጠ።


ኒቃኖር በቤተመቀደሱ ላይ የሰነዘረው ዛቻ

26 ነገር ግን አልቂሞስ መስማማታቸውን አይቶ፥ የውላቸውን ጽሑፍ ይዞ ወደ ዲመትሪዮስ መጣና ኒቃኖር ይሁዳን ወራሹ አድርጐ በመንግሥት ላይ ተቃውሞ አድርጓል ሲል ነገረው።

27 ንጉሡ ተቆጣ፤ በዚህ በክፉ ሰው ምክንያት ተቆጥቶ፥ በስምምነቱነ ያልተደሰተ መሆኑን ገልጾ ይሁዳ መቃቢስን አስሮ በቶሎ ወደ አንጾኪያ እንዲልከው ትእዛዙን ለኒቃኖር ጻፈለት።

28 ይህን በሰማ ጊዜ ኒቃኖር ደገነጠ፤ ምንም በደል በሌለበት ሰው ላይ እንዴት ውል ማፍረስ ይቻላል ሲል ተበሳጨ።

29 ነገር ግን ንጉሡን መቃወም ሰለማይቻል ይህን ትእዛዝ ለመፈጸም ምቹ አጋጣሚ ጊዜ በጥበብ ይፈልግ ነበር።

30 ይሁዳ መቃቢስም በበኩሉ ከኒቃኖር ጋር ያለው ግንኙነት እየቀዘቀዘ መሄድንና ሲገናኘውም ቁጣ ቁጣ የሚለውም መሆኑን በመገንዘብ ይህ ነገር መልካም አለመሆኑን አሰበ። ስለዚህ ከሰዎቹ ብዙዎቹን ሰበሰበና ይዞ ከኒቃኖር ተሠወረ።

31 ኒቃኖር ይህ ሰው በብልጠት እንደረታው አውቆ ካህናት የተለመደውን መሥዋዕት በሚያቀርቡበት ጊዜ ወደ ታላቁና ቅዱስ ቤተ መቅደስ ሄዶ ሰውዬውን አሳልፈው እንዲሰጡት አዘዘ።

32 የምትፈልገው ሰው የት መሆኑን አናውቅም ብለው በመሐላ በነገሩ ጊዜ

33 ኒቃኖር ቀኝ እጁን ወደ ቤተ መቅደሱ ዘርግቶ እንዲህ ሲል በመሐለ ተናገረ፥ “ይሁዳን አስራችሁ ካልሰጣችሁኝ ይህን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ደምስሸ ሜዳ አደርገዋለሁ፤ መሠዊያውንም አፈርሰዋለሁ፤ በዚህ ቦታ ላይ ለዲዩናስዩስ ያማረ መቅደስ አቆማለሁ”፤

34 ይህን ተናግሮ ሄደ፤ ካህናት ግን እጆቻቸውን ወደ ሰማይ ዘርግተው ዘወትር ስለ ሕዝባቸው የተዋጋውን አምላክ እንዲህ ሲሉ ለመኑት፥

35 “አንተ ምንም የማይቸግርህ አምላክ ሆይ በእኛ መካከል የምትኖርበት ቤተ መቅደስ እንዲኖርህ ፈለግህ፤

36 አሁን እንግዲህ የቅዱሳን ሁሉ ቅዱስ አምላክ ሆይ ይህን ከጥቂት ጊዜ በፊት የነጻውን ቤት ከመርከስ ዘወትር ጠብቀው”።


የራዝያስ ሞት

37 ከኢየሩሳሌም ሽማግሌዎች አንዱ ራዝያስ የተባለ ሰው በኒቃኖር ፊት ተከሰሰ፤ ይህ ሰው የሀገሩን ሕዝብ የሚወድ እጅግ ጥሩ ስም ያለው፥ ሰለ ፍቅሩ የአይሁዳውያን አባት ይባል የነበረ ጐምቱ ነው።

38 ሕዝቡ ለጦርነት ከመነሣቱ በፊት ባሉት ጊዜዎች አይሁዳዊነቱን በማራመድ ተከሶ ነበረ፤ በታላቅ ወኔ ስለእምነቱ አካሉንና ሕይወቱን ሰጥቶ ነበር፤

39 ኒቃኖር በአይሁዳውያን ላይ ያለውን ጥላቻ ለመግለጽ ፈልጐ እንዲይዙት ከአምስት መቶ የሚበልጡ ወታደሮች ላከ፤

40 ምክንያቱም ይህን ሰው ከገደለ አይሁዳውያን ላይ ከባድ ምት እንዳሳረፈ ያምን ነበር።

41 የእርሱ ወታደሮች የምሽጉን ግንብ ለመያዝና የውጪውን በር ለማፈረስ በመታገል ላይ ነበሩ፤ መዝጊያዎችንም ለማቃጠል ታዘው ነበረ። ራዝያስ በሁሉም ቦታ ስለተከበበ የገዛ ራሱን በሰይፍ ወጋ፤

42 በጨካኞች እጅ ከመውደቅና ክብሩን ከማዋረድ ይልቅ በክብር መሞትን መረጠ።

43 ነገር ግን በወቅቱ ጦርነቱ በጣም ተፋፍሞ ስለ ነበር ሰይፈ በደንብ አልወጋውም ነበር፤ ወታደሮቹም በበሩ እየተጋፉ ወደ ውስጥ ገቡ፤ እርሱ በድፍረት ወደ ትልቁ ግንብ እየሮጠ ሄደና ምንም ሳይፈራ ወደ ሰዎቹ ተወርውሮ ወደቀ፤

44 ሁሉም በፍጥነት ወደ ኋላ ስላሉና ከቦታው ገለል ስላሉ በሆድ በምድር ላይ ወደቀ፤

45 ገና ስላልሞተ በመንፈሱ ተነሣሥቶ ብድግ አለ፤ ደሙን እየዘራና በቁስሎቹ በጣም እየተሠቃየ በሰዎቹ መካከል ሮጠ፤ በትልቅ ዓለት ድንጋይ ላይ ወጣ፤

46 ደሙ ሁሉ ፈስሶ አለቀ፤ አንጀቱን ከሆድ አወጣና በሁለት እጁ ይዞ በሰዎች መካከል ወረወረው፤ የሕይወትና የመንፈስ ጌታ አንድ ቀን መልሶ አንጀቱን እንዲሰጠው ጸልዮ፥ በዚህ ዓይነት ሞት ሞተ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች