ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ 2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 13 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)አንጥዮኩስና ሊስያስ ያካሄዱት ጦርነት የመነላዎስ አሰቃቂ ሞት 1 በ 149 ዓመት አንጥዮኩስ ኤውጳጥሮስ ብዙ ሠራዊት ይዞ ለጦርነት ወደ ይሁዳ አገር በመገሥገሥ ላይ መሆኑን ይሁዳና የእርሱ ሠራዊት ሰሙ፤ 2 የጉዳዮቹ ፈጻሚ የሆነው የእርሱ መምህር ሊስያስም ከእርሱ ጋር መሆኑን ሰሙ። የአረማውያን (የግሪካውያን) ጦር ቁጥሩ መቶ ዐሥር ሺህ እግረኛ ጦር፥ አምስት ሺህ ሦስት መቶ ፈረሰኛ ጦር፥ ሃያ ሁለት ዝሆኖችና መቶ ባለ ማጨድ ሠረገላዎች ነበር። 3 መነላዎስም ከእነርሱ ጋር ተባብሮ ስለ ሀገራችን ደኀንነት ሳይሆን የቀድሞ ቦታውን አግኝቶ እንዲሾም ሲል በብዙ ተንኮል አንጥዮኩስን ያበረታታ ነበር። 4 ነገር ግን የነገሥታት ንጉሥ የሆነው አምላክ በዚህ በእርጉም ሰው ላይ የአንጥዮኩስን ቁጣ አስነሣበት፤ መነላዎስን የክፉ ነገሮች ሁሉ ምክንያት መሆኑን ሊስያስ ለንጉሡ ባስረዳ ጊዜ ነጉሡ ወደ ቤሪያ እንዲወስዱትና እንደ ሀገሩ ልማድ እንዲገድሉት አዘዘ። 5 በዚያ ቦታ አመድ የሞላበት ርዝመቱ ወደ ላይ ሃምሳ ክንድ የሆነ አንድ ግንብ ነበር፤ ይህ ግንብ ወደ አመዱ ያዘነበለ የሚሽከረከር መሳሪያ ነበረው። 6 የተቀደሰ ነገር የበዘበዘ ወይም ትልቅ ወንጀል የሠራ ሰውን ከዚህ ከግንብ ላይ አውጥተው እንዲሞት እዚያ ይጥሉታል፤ 7 ይህ ክፉ ሰው የሞተውና ያለመቃብር የቀረው በእንደዚህ ያለ ሞት ነው። 8 እርሱ በመሠዊያ ላይ ብዙ ኃጢአት ስለ ሠራ ይህ ፍርድ ትክክለኛ ነው፤ የመሠዊያው እሳትና አመድ ንጹሕ ነበር፤ እርሱም የሞተው በአመድ ውስጥ ሆነ። በሞዲን አጠገብ የአይሁዶች ጸሎትና ድል 9 ንጉሡ በጨካኝ አስተሳሰብ ተሞልቶ በመታበይ በአባቱ ሥልጣን ጊዜ በአይሁዳውያን ላይ ከተደረገው ክፉ ሥራ የባሰ ለማድረግ ይገሠግሥ ነበር፤ 10 ይሁዳ ይህን በሰማ ጊዜ ሕጋቸውን፥ ሀገራቸውን፥ ቤተ መቅደሳቸውን ከሚያሳጧቸው ሰዎች ይልቁንም በዚህ ሰዓት አምላክ እንደ ቀድሞው እንዲያድናቸው ሕዝቡ ሌት ተቀን እንዲጸልዩ አዘዘ፤ 11 ጥቂት ማረፍ የጀመረውን ይህን ሕዝብ እንዳይተወውና በከፉዎች አረማውያን እጅ እንዳይወድቁ አምላክን ለምኑ ብሎ አዘዘ። 12 ሁሉም ሳያቋርጡ ሦስት ቀን ተደፍተው በዕንባና በደም ወደ እግዚአብሔር ከጸለዩ በኋላ ይሁዳ ሰዎቹ በእርሱ አጠገብ እንዲሆኑ መከራቸው፤ አበረታች ቃላትን ሰነዘረ። 13 እርሱ ብቻውን ከሽማግሌዎች ጋር ከተማከረ በኋላ የንጉሡ ሠራዊት የይሁዳን ምድር ከመውረራቸውና ከተማዋን ከመያዛቸው በፊት በእግዚአብሔር እርዳታ ተማምኖ ወደ ጦርነቱ ለመገሥገሥ ወሰነ። 14 የጉዳዩን ውሳኔ ለዓለም ፈጣሪ ትቶ ሰዎች ስለ ሕጎቻቸው፥ ስለ በተመቅደሳቸው፥ ስለ ከተማቸው፥ ሰለ ሀገራቸው፥ ስለ ኑሮአቸው እንዲዋጉ መከረ፤ ሠራዊቱም በሞዲን አቅራቢያ እንዲሰፍር አደረገ። 15 ለወታደሮቹም “ድል የአምላክ ነው” የሚል መፈክር ሰጣቸው። ከዚህ በኋላ ምርጥ ምርጥ ወታደሮችን አሰልፎ በለሊት የንጉሡን ሰፈር ወጋ፤ ከሰፈሩ ሰዎች ሁለት ሺህ የሚያህሉትን ደመሰሰ። የእርሱ ሰዎች ከሁሉ ይበልጥ ትልቅ የነበረውን ዝሆን ከነሳቢው ገደሉ። 16 በሰፈሩ ውስጥ ድንጋጤና ሁከት ገባ፤ ከዚህ በኋላ ቀንቷቸው ተመለሱ። 17 ሊነጋጋ ሲል እግዚአብሔር ለይሁዳ ባረገው ጥበቃ ድል ተገኘ። አንጥዮኩስ ከአይሁዳውያን ጋር ስለ ሰላም ተደራደረ 18 የአይሁዳውያኑን ጀግንነት የተመለከተው ንጉሥ ቦታቸውን በማጭበርበር ለመያዝ ፈለገ። 19 ንጉሡ የአይሁዳውያኑ ብርቱ ምሽግ ወደነበረው ወደ ቤተሱር ተቃረበ፤ ግን እርሱ ተቃወሙት፥ አባረሩት፥ አሸነፉት። 20 ይሁዳ በጥበቃ ላይ ሆነው የከላከሉ ለነበሩት ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ስንቅ ሁሉ ላከላቸው፤ 21 ነገር ግን ከአይሁዳውያን ጦር ውስጥ የነበረ ሮዶክስ የተባለ ሰው ለጠላቶች ምስጢር መረጃዎችን ስለሰጠ ታሰረ፤ አስፈላጊውም እርምጃ ተወስደበት። 22 ሁለተኛ ጊዜ ንጉሡ ከቤተሱር ሰዎች ጋር ተነጋገረና የሰላም እጁን ዘረጋላቸው፤ ጨበጣቸውምና ተመልሶ ሄደ። ከዚህ በኋላ ይሁዳንና ሰዎቹን ወጋ፤ ግን ተሸነፈ። 23 የጉዳዮቹ ፈጻሚ አድርጐ የተወው ፊሊጶስ በአንጾኪያ እንደተነሣበት በሰማ ጊዜ አንጥዮኩስ ተደናገጠ። ከአይሁዳውያን ጋር የሰላም ድርድር ማድረግና መስማማት ፈለገ፤ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ማለ፤ ከእነርሱ ጋር ታረቀ። መሥዋዕት በማቅረብ ቤተ መቅደስን አከበረ፤ ለተቀደሰው ቦታ መልካም በማድረግ ልግስናውን ገለጸ። 24 ይሁዳ መቃቢስን በመልካም አቀባበለ ተቀበለው፤ ከጰጠሎማይዳ አንሥቶ እስከ ጌሬኖስ ድረስ ሄጌሞኒደስን ገዥ እንዲሆን አድርጐ ተወው። 25 ወደ ጰጠሎማይዳም ሄደ፤ ግን የከተማው ሕዝብ በተደረገው የሰላም ውል ተቆጥቶ ውሉ እንዲፈርስ ፈለገ። 26 በዚያን ጊዜ ሊስያስ በመድረክ ላይ ወጣና የሚቻለውን ያህል ስለውሉ ተከላከለና አሳመናቸው (አበረዳቸው)። ወደ መልካሙ ነገር መለሳቸውና ወደ አንጾኪያ ሄደ። የንጉሡ ማጥቃትን ሽሽትን በተመለከተ ይህን ያህል ከተባለ በቂ ነው። |