ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ 2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 12 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የኢዮጴ እና የያምንያ አጋጣሚዎች 1 ይህን ውል ከፈጸሙ በኋላ ሊስያስ ወደ ንጉሡ ተመለሰ፤ አይሁዳውያንም እርሻቸውን ማረስ ጀመሩ። 2 ነገር ግን እዚያ ከነበሩት የጦር አለቆች መካከል ጢሞቴዎስና የጌኔይ ልጅ አጰሎንዮስ፤ እንዲሁም ሄሮኒሞስና ደሞፎን የቆጱሮሱ ኒቃኖር ሰላምና ጸጥታ ነሡዋቸው፤ 3 በተለይ የኢዮጴ ሰዎች ክፉ ሥራ ሠሩባቸው፤ ከእነርሱ ጋር የሚኖሩትን አይሁዳውያን ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ሆነው ባዘጋጅዋው መርከቦች እንዲሣፈሩ ጠሩዋቸው፤ በእነርሱ ላይ ክፉ ሐሳብ እንደሌላቸውም አስታወቁ፤ 4 የከተማው ሕዝብ ባደረገው ውሳኔ መሠረት አይሁዳውያን ሰላም ፈላጊዎችና ምንም የማይጠራጠሩ መሆናቸውን ለማስታወቅ ሲሉ ጥሪያቸውን ተቀበሉ፤ ግን በባሕሩ መካከል በደረሱ ጊዜ ሁለት መቶ ያህል ሰዎችን ወደ ባሕር ጣሏቸው። 5 ይሁዳ መቃቢስ በእርሱ ሀገር ሰዎች ላይ ይህ ጭካኔ መደረጉን በሰማ ጊዜ ትእዛዙን ወዲያው ለእርሱ ሰዎች አስተላለፈ። 6 ትክክለኛ ፍርድ ወደሚሰጠው አምላክ ጸሎት ካደረገ በኋላ ወንድሞቹን ወደገደሉ ሰዎች ገሠገሠ። መርከብ የሚቆምበትን ጠረፍ በሌሊት እሳት ለቀቀበት፤ መርከቦቹን አቃጠለ፤ መጠጊያ ፈለገው ይሸሹ የነበሩትን አስገደለ፤ 7 ግን የከተማው በር ተዘግቶ ስለ ነበር የኢዮጴን ሰዎች ሌላ ጊዜ ተመልሼ እደመስሳቸዋለሁ ብሎ ሄደ። 8 እንዲሁም የያምንያ ሰዎች ከእነርሱ ጋር በሚኖሩ አይሁዳውያን ላይ ክፉ ለማድረግ እንዳቀዱ ሰማ፤ 9 የያምንያ ሰዎችንም በሌሊት መጣባቸውና ጠረፉን ከመርከቦቹ ጋር በእሳት አጋየ፤ የእሳቱም ብርሃን እስከ ኢየሩሳሌም ማለትም እስከ ሠላም ምዕራፍ (45 ኪ. ሜትር) ርቀት ድረስ ታየ። በገለዓድ የተደረገ ጦርነት 10 ከጢሞቴዎስ ጋር ሊዋጉ ሲሄዱ ከዚያ አንድ ምዕራፍ (1.5 ኪ.ሜ) እንደራቁ አምስት ሺህ የሚያህሉ እግረኛ ጦረኞችና አምስት መቶ ፈረሰኞች ያሉት የዓረቦች ጦር ገጠሟቸው። 11 ብርቱ ውጊያ ከተካሄደ በኋላም የይሁዳ ወታደሮች በእግዚአብሔር እርዳታ አሸንፈው ዘላኖቹ ዓረቦች ተሸንፈው ይሁዳን የሰላም እጁን እንዲዘረጋላቸው ለመኑት፤ ከብት እንሰጥሃለን፥ በሰላም ጊዜ ሁሉ እንጠቅምሃለን ሲሉ ተስፋ ሰጡት፤ 12 ይሁዳም እነርሱ በእውነቱ ብዙ እንደሚያገለግሉት ተረድቶ ከእነርሱ ጋር ሰላም ማድረግ ፈለገ፤ ከተጨባበጡም በኋላ ዓረቦች ወደየድንኳኖቻቸው ገቡ። 13 እንዲሁም ይሁዳ ብዙ ድብልቅ ሕዝቦች የሚኖሩባትን በግንብ ምሽግ የከበበችውን ቃስጴስ የምትባለዋን ሀገር ወጋ። 14 እነዚያ በጦር የተከበቡ ሰዎች በግንባቸው ጥንካሬና በምግባቸው ክምችት ተማምነው የይሁዳን ወታደሮች በጣም ንቀዋቸው ነበር፤ ይራገሙና ይሳደቡም ነበር፤ የማይገባውን ነገር ይናገሩ ነበር። 15 ግን ይሁዳና የእርሱ ሰዎች ያለመዋጊያና ያለ ጦር መሣሪያ በኢያሱ ዘመን ኢያሪኮን የገለባበጠ ታላቁን የዓለም ጌታን ከለመኑ በኋላ በቁጣ ግንቡን ከበው ይዋጉ ጀመር፤ 16 በእግዚአብሔር ፈቃድ ከተማዋን ይዘው ለቍጥር የሚያስቸግር ሰው ፈጁ፤ ስፋቱ ሩብ ምዕራፍ (375 ሜትር) የነበረውን እዚያ አጠገብ የሚገኘውን ቀላይ የፈሰሰው ደም ሞላው። በቀርኒዩን የተደረገ ጦርነት 17 ከዚያ ዘጠና አምስት ምዕራፍ 138 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀው አይሁዳውያን ጦባውያን ወደሚሉት ወደ ካራስ ደረሱ። 18 ጢሞቴዎስን ግን እዚያ አላገኘሁትም፤ ምክንያቱም እርሱ ምንም ሳያደርግ ከዚያ ቦታ ርቆ ሄዶ ነበር፤ በአንድ ቦታ ላይ ግን ብርቱ ጦር ሠራዊት ትቶ ነው የሄደው። 19 የይሁዳ መቃቢስ ጦር መሪዎች ያስጦስና ሱሊ ጳጥሮስ ሄደው ከዐሥር ሺህ በላይ የሆኑትን ጢሞቴዎስ በምሽጉ ውስጥ ትቶአቸው የነበሩትን ሰዎች አጠፍዋቸው (ደመሰሱዋቸው)። 20 ይሁዳ መቃቢስ በበኩሉ ጦር ሠራዊቱን በክፍል በክፍል አሰልፎ፥ ለየክፍሉም አለቃ ሾሞ መቶ ሃያ ሺህ እግረኛ እና ሁለት ሺህ አምስት መቶ ፈረሰኞች አሰልፎ የነበረውን ጢሞቴዎስን ለመውጋት ገሠገሠ። 21 የይሁዳን መቃረብ በሰማ ጊዜ ጢሞቴዎስ ሴቶች ልጆች ከጓዝ ጋር ቀርንዮን ወደሚባል አገር ቀድመው እንዲጓዙ አደረገ፤ ምክንያቱም ቦታው የማይደፈርና በቦታው ጥበት ምክንያት መተላለፊያው የሚያስቸግር ስለ ነበር ነው። 22 በይሁዳ የሚመራው ጦር ሠራዊት በመጀመሪያ ብቅ ባለ ጊዜ ጠላት ተሸበረ፤ ሁሉን የሚያይ አምላክ በግልጽ ፍርሃት አሳደረባቸው፤ በያሉበት ሸሹ፤ እርስ በርሳቸው ተቋሰሉ፥ በጐራዴም (በሰይፍም) አንዱ ሌላውን ይወጋ ነበር። 23 ይሁዳ በልዩ ጥንካሬ ተከታተላቸው፤ እነዚህን ጨካኞች በሰይፍ ፈጃቸው፤ እስከ ሰላሳ ሺህ ሰዎች ተገደሉ። 24 ጢሞቴዋስም በጰሲጦስና በሱሊጳጥሮስ ወታደሮች እጅ ወደቀ፤ እንዳይገሉትና እንዲለቁት ለመናቸው፥ “ዘመዶቻችሁና ከወንድሞቻችሁ አብዛኞቹ በእኔ ሥልጣን ሥር ያሉ ናቸው፤ በእኔ ሞት ምክንያት እነርሱ ጉዳት እንዳይደርስባቸው” ሲል እንዲለቁት በተንኮል ተናገራቸው። 25 ግዴታውን ካረጋገጠላቸው በኋላና ሰዎቹን በደኀና እለቃቸዋለሁ ብሎ ብዙ በመናገር ቃሉን ከሰጣቸው በኋላ ወንድሞቻቸውን ለማዳን ለቀቁት። 26 ይሁዳ ወደ ቀርኒዮን ወደ አተርጋቶን ሄዶ ሃያ አምስት ሺህ ሰው ገደለ። በኤፍሮን እና በሽቶፖሊስ በኩል የተደረገው የመልስ ጉዞ 27 ጠላቶቹን ካሸነፈና ካጠፋ በኋላ ጦር ሠራዊቱን ወደ ኤፍሮን አዘመተ፤ ኤፍሮን ሊስያስ የሚኖርባት ምሽግ ከተማ ናት፤ እዚያ ጠንካራ ወጣቶች ከግንቡ ፊት ለፊት ቦታቸውን ይዘው በጥንካሬ ይዋጉ ነበር፤ በክልሉም ብዙ የጦር መሳሪያዎች ተምዘግዛጊዎች ነበሩ። 28 ግን አይሁዳውያን የጠላቶችን ኃይል የሚሰብረውን ጌታ ከለመኑ በኋላ ከተማዋን መያዝ ቻሉ፤ በግንቡ ውስጥ ከሚገኙት ሰዎች መካከል ሃያ አምስት ሺህውን አጋደሙ። 29 ቦታውን ትተው ከኢየሩሳሌም ሰባ አምስት ምዕራፍ፤ (አንድ ሺ አንድ መቶ ሃያ ሦስት ኪሎ.ሜ ተኩል) ርቃ ወደምትገኘው ወደ ሽቶፖሊስ ገሠገሡ። 30 ነገር ግን እዚያ የነበሩ አይሁዳውያን ሲቲያውን ያደረጉላቸውን መልካም ነገር ስለመሰከሩላቸውና በችግራቸው ጊዜ በመልካም የተቀበሏቸው መሆኑን ስለተናገሩላቸው 31 ይሁዳና የእርሱ ወታደሮች ሰዎቹን አመስግነው ለወደፊቱም ለሕዝበቸው ደጐች እንዲሆኑ መክረዋቸው የሳምንቱ በዓል (የጴንጤቆስጤ በዓል) ቀርቦ ስለ ነበር ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ። ከጐርጊያስ ጋር የተደረገ ጦርነት 32 ከጴንጤቆስጠ በዓል በኋላ የኤያምያስ ገዥ ከነበረው ከጐርጊያስ ጋር ለመዋጋት ገሠገሡ፤ 33 ጐርጊያስ ሦስት ሺህ እግረኛ ጦርና አራት መቶ ፈረሰኛ እየመራ መጣ። 34 በተደረገው ጦርነት ጥቂቶች አይሁዳውያን ወደቁ (ሞቱ)። 35 ይሲጦስ ከባኬኖር (ከጦብ) ሰዎች አንድ ጀግና ፈረሰኛ የሆነው ሰው ጐርጊያስን በልብሱ ይዞ ይህን እርጉም ሰው ለመማረክ ይጐትተው ነበር፤ ነገር ግን አንድ የትራኪስ አገር ፈረሰኛ ወደ ይሲጦስ ሮጠና ትከሻውን በሰይፍ መታው፤ ጐርጊያስም አመለጠና ወደ ማሬሳ ሸሸ። 36 የአዝሪ ወታደሮች ግን ብዙ ጊዜ ከተዋጉ በኋላ ድካም ተሰማቸው፤ እግዚአብሔር በጦርነቱ ላይ ረዳታቸውና መሪአቸው እንዲሆን ይሁዳ ጸለየላቸው። 37 በሀገሩ ቋንቋ ጮክ ብሎ የጦር መዝሙር ከዘመረ በኋላ የጐርጊያስን ሰዎች አባረራቸው። ስለ ሙታን የቀረበ መሥዋዕት 38 ይሁዳ ሠራዊቱን አስተባበረና ወደ አይላም አገር ሄደ፤ ነገር ግን የሳምንቱ ሰባተኛ ቀን ስለ ደረሰ እንደተለመደው የመንጻት ሥራን አደረጉና በዚያ ቦታ የሰንበትን በዓል አከበሩ። 39 በማግስቱ ይሁዳና የእርሱ ሰዎች በጦርነት የሞቱትን ሰዎች በጊዜው አስክሬናቸውን ለማንሣትና ከዘመዶቻቸው ጋር በአባቶቻቸው መቃብር ለመቅበር መጡ። 40 ከሞቱት ከእያንዳዳቸው ልብስ ውስጥ ለያመንያ ጣዖት የቀረበውን በአይሁድ ሕግ የተከለከለውን መባ አገኙ፤ 41 ስለዚህ ሁሉም የተሠወረውን ነገር የሚገልጽ ትክክለኛ ፈራጅ የሆነውን አምላክ አመሰገኑ፤ 42 የሠሩት ኃጢአትም በሙሉ እንዲሰረይላቸው ጸለዩ፤ ጀግናው ይሁዳም ወታደሮቹ በኃጢአታቸው ምክንያት በሞት የተቀጡትን ሰዎች (ወታደሮች) በማየት ከኃጢአት ሁሉ ንጹሕ እንዲሆኑ መከራቸው። 43 ከእያንዳንዳቸውም ገንዘብ በመሰብሰብ በኃጢአት ምክንያት መሥዋዕት እንዲቀርብ ሁለት ሺህ ድራህም ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፤ ይህንንም ያደረገው ስለ ትንሣኤ መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር በማሰብ ነው። 44 የሞቱት ወታደሮች ከሞት የሚነሡ መሆናቸውን ተስፋ ባያደርግ ኖሮ ለሙታን ጸሎት ማድረግ ሞኝነት እና የማያስፈልግ በሆነ ነበር፤ 45 በመንፈሳዊነት (በመልካም) የሞቱ ሰዎች መልካም ሽልማት የሚያገኙ መሆናቸውን ማሰቡ ቅዱስና መልካም ሐሳብ ነው። ስለዚህ ኃጢአታቸው ይቅር እንዲባልላቸው ይህ የኃጢአት ማስተሣረያ (ኃጢአት ይቅር ማሰኛ) የሆነው መሥዋዕት ለሙታን እንዲደረግላቸው አስደረገ። |