Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 11 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የሊስያስ የመጀመሪያው ጦርነት (ዘመቻ)

1 ከጥቂት ጊዜ በኋላ የንጉሡ መምህርና ዘመድ የሆነው ሊስያስ የመንግሥት ጉዳይ ዋና ኃላፊ ስለሆነ በቅርቡ በተደረገው ነገር መታገሥ አቃተው፤

2 ከፈረሰኛ ጦሩ ጋር ሰማንያ ሺህ ያህል እግረኛ ጦረኞች ሰብስቦ አይሁዳውያንን ለመውጋት ይገሠግሥ ጀመር፤ ከተማዋን የግሪኮች መኖሪያ ሊያደርጋት አስቦ ነበር፤

3 ቤተ መቅደስን እንደ ሌሎቹ የአረማውያን ጣዖት ቤቶች ማስገበርና የሊቀ ካህናቱን ክብር በየዓመቱ እንዲሸጥ ማድረግ አስቦ ነበር፤

4 የእግዚአብሔርን ሥልጣን ከምንም አልተቆጠረም፤ በትዕቢት የተነፍቶ እምነቱን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ እግረኞች ጦረኞቹ፥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ፈረሰኞቹ፥ በሰማንያ ዝሆኖቹም ላይ ጥሎ ነበር።

5 በይሁዳ አገር በደረሰ ጊዜ ስድስት ኪሎ ሜትር ያህል ከኢየሩሰሌም ርቃ ወደምትገኘው ምሽግ ወደ ቤተሱር ተጠጋና ከበባት፤

6 ይሁዳ መቃቢስና የእርሱ ሰዎች ሊስያስ ምሽጐቹን እንደከበበ አወቁ፤ እስራኤልን የማይድን ደግ መልአክ እንዲልክ ከሕዝቡ ጋር ሆነው እየተጨነቁና እንባቸውን እያፈሰሱ እግዚአብሔርን ለመኑት።

7 ይሁዳ መቃቢስ ራሱ አስቀድሞ የጦር መሳሪያ በመያዝ ወንድሞቻቸውን ለማዳን ከእርሱ ጋር አደጋውን እንዲጋፈጡ ሌሎቹን መከረ፤ እነርሱም በጀግንነት ተነሣስተው አብረው ወጡ፤

8 ገና በኢየሩሳሌም አጠገብ እያሉ ወርቃዊ የጦር መሣሪያ የጨበጠ፤ ነጭ ልብስ የለበሰ ፈረሰኛ መሪአቸው ሆኖ አዩ፤

9 ሁለም በአንድ ላይ መሐሪውን እግዚአብሐርን አመሰገኑ፤ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ጨካኝ አውሬዎችንና የብረት ግንቦችን እንኳ ለመውጋት ብርታትን አገኙ።

10 እግዚአብሔር ሰለራራላቸውና ከሰማይ ረዳት ስላገኙ ለውጊያ ተሰልፈው ገሠገሡ፤

11 እንደ አንበሶች ዘልለው ወደ ጠላት መሀል ገቡና ዐሥራ አንድ ሺህ እግረኛ ጦረኞችና አንድ ሺህ ስድስት መቶ ፈረሰኞችን ወግተው ጣሉ፤ የጠላት ጦር እንዲሸሽ አደረጉ።

12 ከእነርሱ አብዛኞቹ ቆስለው መሣሪያዎቻቸውን እየጣሉ አመለጡ፤ ሊስያስም በሚያሳፍር ሁኔታ ሸሽቶ አመለጠ።


በአይሁዳውያንና በሊስያስ መካከል ሰላም ሆነ ስምምነቱን የተመለከቱ አራቱ ዳብዳቤዎች

13 ነገር ግን ሊስያስ ነገሩን ልብ አድርጐ ተመለከተና የደረሰበትን መሸነፍ አሰበ፤ ሁሉን የሚችል አምላክ ረዳታቸው በመሆኑ ዕብራውያን የማይሸነፉ መሆናቸው ስለገባው መልእተኞች ወደ እነርሱ ላከ፤

14 በሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ለመስማማት ሐሳብ አቀረበ፤ ንጉሡም ወዳጃችሁ እንዲሆን አስረዳዋለሁ ሲል ተስፋ ሰጣቸው።

15 ይሁዳ መቃቢስ ለሁሉም ጥቅም መሆኑን አስባ ሊስያስ ያቀረበለት ሐሳብ ተቀበለ፤ ይሁዳ መቃቢስም ስለ አይሁዳውያን ጉዳይ በጽሑፍ ለሊስያስ ያቀረበውን ነገር ሁሉ ንጉሡ እሺ ብሎ ተቀበለ።

16 ሊስያሰ ለአይሁዳውያን የጻፈው ደብዳቤ እንዲህ የሚል ነበር፥ “ሊስያስ ለአይሁዳውያን ሁሉ ሰላምታ ያቀርባል።

17 እናንተ የላካችኋቸው ዮሐንስና አቤሴሎም የጻፋችሁትን አቅርበውልን የጻፉትን ነገሮች እንድቀበል ጠይቀውኛል።

18 በእኔ በኩል የሚቻለውን ሁሉ ከተቀበልሁ በኋላ ለንጉሡ ማቅረብ የሚገባውን ለንጉሡ አቅርቤአለሁ፤ (እርሱም ተቀብሏል)

19 እናንተ ለመንግሥት መልካም አሳቢዎች ናችሁ ከተገኛችሁ እኔም ለእናንተ ወደ ፊት መልካም ነገር አደርጋለሁ።

20 ስለ ዝረዝሩ መልእክተኞቻችሁና የእኔም ሰዎች ከእናንተ ጋር እንዲነጋገሩ ትእዛዝ ሰጥቻለሁ።

21 ደኀና ሁኑ፤ በ 148 ዓመት በ 24 የዲዮ ስቆሪንቶስ ወር”። (አዳር ከ 26 የካቲት እስከ 27 መጋቢት ያለው ወር ነው።)

22 የንጉሡ ደብዳቤም እንዲህ ይል ነበር፤ “ንጉሥ አንጥዮኩስ ለወንድሙ ለሊስያስ ሰላምታ ያቀርባል፤

23 “አባታችን ወደ አማልክት ሄዷል (ሞቷል)፤ እኛም የመንግሥታችን ሰዎች ሁሉ የውስጥ ጉዳያቸውን እየፈጸሙ ያለ ችግር እንዲኖሩ እንፈልጋለን፤

24 አይሁዳውያን አባታችን የፈለገውን የግሪካውያን ልማድ መከተል እንደማይወዱ ሰምተናል፤ የራሳቸውን ልዩ መንገድ ይመርጣሉ፤ ሕጋቸውን ለመጠበቅ እንዲፈቀድላቸውም ይፈልጋሉ፤

25 ስለዚህ ይህ ሕዝብም ከችግር ነጻ እንዲሆን በመመኘት ቤተ መቅደሳቸው እንዲመለስላቸውና በአባቶቻቸው ልማድ መሠረት ዜጐች ሆነው እንዲኖሩ ወስነናል።

26 አንተ ወደ እነርሱ ሰው ብትልክና የሰላም እጅህን ብትዘረጋላቸው መልካም ነው፤ በዚህ ዓይነት እኛ የተከተልነውን መንገድ አውቀው እምነት ይኖራቸዋል፤ በመልካመ ሁኔታም ሥራቸውን ያከናውናሉ”።

27 ወደ አይሁዳውያን የተላከው የንጉሡ ደብዳቤ እንዲህ የሚል ነበር፤


ንጉሡ አንጥዮኩስ ለአይሁዳውየን ምክር ቤትና ለሌሎችም አይሁዳውያን ሰላምታ ያቀርባል

28 “ደኀና እንድትሆኑ ምኞታችን ነው፤ እኛ በመልካም ጤና ላይ እንገኛለን፤

29 መነላዎስ እናንተ ወደ ሀገራችሁ ተመልሳችሁ ጉዳያችሁን እንድትፈጽሙ መፈለጋችሁን ነግሮናል፤

30 “ከ 30 ጻንጢቆ (የካቲት-መጋቢት) በፊት ወደ ሀገራቸው ለሚመለሱ ሁሉ የሰላም እጃችንን እንደምንሰጣቸው እናረጋግጣለን።

31 አይሁዳውያን እንደ ቀድሞው ጊዜ ሕጋቸውን መከተልና ልዩ ምግባቸውን መመገብ ይችላሉ፤ ከእነርሱ ማንም ባለማወቅ በሚያደርገው ስሕተት በምንም ዓይነት አይጠይቅም።

32 ከእናንተ ጋር ተነጋግሮ የሚያረጋግጥላችሁን መነላዎስን ልኬላችኋለሁ። ደኀና ሁኑ”።

33 በ 148 ዓመት በ 15 በጻንጢቆ ወር (የካቲት-መጋቢት)

34 ሮማውያንም በበኩላቸው ለአይሁዳውያን እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጽፈዋል። “ኩዋንቶስ መማዮስ፥ ቲቶ ማንሊዮስ፥ ማኒዮስ ሰርጅዮስ፥ ሮማውያን መልእክተኞች ለአይሁድ ሕዝብ ሰላምታ ያቀርባሉ፤

35 “የንጉሡ ዘመድ ሊስያስ የፈቀደላችሁን ሁሉ እኛም ፈቅደናል።

36 ነገር ግን ለንጉሡ አቀርባቸዋለሁ ስላላቸው ነገሮች ከመረመራቸው በኋላ በቶሎ ወደ እኛ ሰው ላኩና እኛ ወደ አንጾኪያ ከመሄዳችን በፊት ለእናንተ በሚጠቅማችሁ ዓይነት ነገሮቹን ለንጉሡ እንድንገልጽለት ይሁን።

37 ሐሳባችሁ ምን መሆኑን እኛም እንድናውቅ ቶሎ ብላችሁ ሰው ላኩብን።

38 ደኀና ሁኑ።” በ 148 ዓመት በጻንጢቆ ወር በ 15 ተፃፈ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች