ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ 2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 10 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የቤተ መቅደስ መንጻት 1 ይሁዳ መቃቢስ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ እግዚአብሔር እየመራው ቤተ መቅደሱንና ከተማዋን እንደገና አስተካከለ፤ 2 የውጭ አገር ሰዎች ለሕዝቡ ያቋቋሙዋቸውን መሠዊያዎችና የአምልኮ ቦታዎች አፈራረሱ። 3 ቤተ መቅደሱ ካነጸ በኋላ ሌላ መሠዊያ ሠሩ፤ ከድንጋይ አዲስ እሳት አውጥተው ሁለት ዓመት ከተቋረጠ በኋላ መሥዋዕት አቀረቡ፤ ዕጣን አጨሱ፤ ፋኖሶቹን አበሩ፤ የተቀደሱትን ዳቦዎች አወጡ። 4 እነዚህን ሥርዓቶች ከፈጸሙ በኋላ በግምባራቸው ተደፍተው፤ እግዚአብሔር እንደዚህ ዓይነት መቅሰፍት ላይ እንዳይጥላቸው፥ ኃጢአት ላይ ቢወድቁም በመጠኑ እንዲያርማቸው (እንዲቀጣቸው) እንጂ ከተሳዳቢዎችና ከጨካኞች አረማውያን እጅ እንዳይጥላቸው ለመኑት። 5 ይህ የቤተ መቅደስ መንጻት የሆነው ልክ ባዕዳን ቤተ መቅደሱን ባረከሱበት ቀን በ 25 በሴከሎ ወር ነው። 6 ስምንቱን ቀን ልክ እንደ ዳስ በዓል በደስታ አከበሩ፤ ከጥቂት ጊዜ በፊት ይህን በዓል ያከበሩት እንደ ዱር አራዊት በተራራና በዋሻዎች ውስጥ ሆነው እንደ ነበር አስታወሱ። 7 ስለዚህ የዛፍ ቅርንጫፎችና ቅጠል ዘንባባም ይዘው ቅዱሱን ቦታ እንዲያነጹ ያበቃቸውን አምላክ በዘማሬ አመሰገኑ። 8 በድምፅ ብልጫ ወስነው እነዚህን ቀኖች የአይሁድ ሕዝብ በየዓመቱ እንዲያከብሯቸው አዘዙ። 5ኛ ሹም ከሊሲያስ ጋር የደረገው ትግል የአንጥዮኩስ ግዛት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ይሁዳ ከጎረቤቶቹ ሕዝቦች እንዲሁም ከአንጥዮኩስ 9 እንግዲህ የአንጥዮኩስ ኤጲፋኔስ ሞት በእንደዚህ ሁኔታ ተፈጸመ፤ 10 አሁን በአንጥዮኩስ ኤውጶጥሮስ ጊዜ የሆነውን እንተርካለን። እርሱ የዚያ የክፉ ሰው ልጅ ነው፤ በጦርነት ሳቢያ የደረሰበትን ጭንቀት እንናገራልን። 11 መንግሥቱን ከወረሰ በኋላ እርሱ የቀለሲርያና የፊኒቆስ ገዥ የነበረውን ሊስያስን የጉዳዩ አለቃ አድርጐ ሾመው። 12 ማቅሮን የተባለው ጰጠሎማዮስ ግን በአይሁዳውያን ላይ በተደረገው በደል ፍትሕ እንዲያገኙ ያደረገ፥ በሰላም ለማሰተዳደር የሞከረ የመጀመሪያው ሰው እርሱ ነበር። 13 በዚህ ጉዳይ የንጉሡ ወዳጆች በኔውጳጥሮስ ላይ ከሰውት ፊሎመትሮስ አደራ የሰጠውን ቆጵሮስን ስለተወና ወደ አንጥዮኩስ ኤጲፋኔስጐን ስለዞረ የዘወትር ከሐዳ ተብሎ ተጠራ። በሠራውም ክብሩን ጠብቆ ስላልተገኘ መርዝ ጠጥቶ ሞተ። ጐርጊያስ እና የአዱማያውያን የመከለከያ ግንብ 14 ጐርጊያስ የሀገሩ የጦር መሪ ሆኖ ቅጥረኞች ወታደሮችን ያስተዳድር ነበር፤ ከአይሁዳውያን ጋር ጦርነት ለመግጠም ሁልጊዜ አጋጣሚ ነገር ይፈልግ ነበር። 15 በዚያኑ ጊዜ በደንብ የተዘጋጁትን ምሽጐች ይዘው የነበሩ ኤዱማውያን ይሁዳውያንን ያስቸግሩ ነበር፤ ከኢየሩሳሌም ሸፍተው የሄዱትን ሰዎች ተቀብለው ጦርነትን ያነሣሡ ነበር። 16 ነገር ግን ይሁዳ መቃቢስና የእርሱ ወታደሮች በግብጽ ጸሎት ካደረጉና እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንዲሆን ከለመኑ በኋላ ወደ ኤዱማውያን ምሽጐች መገሥገሥ ጀመሩ። 17 በጥንካሬ ተዋግተው ባታዎችን ያዙባቸው፤ በግንቡ ላይ ሆነው ይዋጉ የነበሩትን ሁሉ አስወገዷቸው፤ ሊቃወሙዋቸው የመጡትንም ገደሉዋቸው፤ ከሃያ ሺህ የማያንሱ ሞቱ። 18 ዘጠኝ ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ለውጊያ የሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ባላቸው በተለይ ጠንካራ በሆኑ ሁለት ግንቦች ውስጥ መሽገው ነበር፤ 19 ይሁዳ መቃቢስ ስምዖንንና ዮሴፍን፥ ዘኬዎስንም ከሰዎቹ ጋር ብዙዎችን እዚያ እንዲከብቡዋቸው አድርጐ እርሱ ራሱ በጣም አስፈላጊ ወደሆኑ ቦታዎች ሄደ። 20 ነገር ግን ለገንዘብ የተሰገበገቡትን የስምዖንን ሰዎች፥ ግንቦቹን የሚጠብቁ ሰዎች በገንዘብ አታለሏቸው፤ ሰባ ሺህ ድርሀም ተቀብለው እንዳንዶቹ እንዳያመልጡ አድርገዋል። 21 ይህን ነገር ለይሁዳ መቃቢስ በነገሩት ጊዜ የጦር አለቆቹን ሰብስቦ ጠላቶቻቸውን በእነርሱ ላይ በመለቀቅ ወንድሞቻቸውን ለገንዘብ ሲሉ ሸጠዋል ብሎ ጥፋተኞቹን ከሰሳቸው፤ 22 ስለዚህ እንደ ከሐዲዎች ተቆጥረው እንዲገደሉ አደረገና ሁለቱን ግንቦች ያዘ። 23 በሱ የሚመራውን ጦር በመልካም መርቶ በእነዚህ በሁለት ምሽጐች የነበሩትን ከሃያ ሺህ በላይ የሚሆኑትን ሰዎች ደመሰሰ። ይሁዳ ጢሞቴዎስን አሸንፎ ጋዜርን ያዘ 24 በፊት ጊዜ አይሁዳውያን አሸንፈውት የነበረ ጢሞቴዎስ ብዙ የውጭ አገር ሰዎች አሰልፎ፥ ከእስያ የመጡ ብዙ ፈረሶች ሰብስቦ፥ በጦር መሣሪያ ሰዎቹን ለማንበርከክ አስቦ ወደ ይሁዳ ምድር መጣ። 25 ጦሩ በተቃረበ ጊዜ ይሁዳ መቃቢስና የእርሱ ሰዎች በራሳቸው ላይ አፈር ነሰነሱና በወገባቸው የተለተለ ልብስ አሸረጡ። 26 እግዚአብሔር ይቅር እንዲላቸውና በኦሪት ቃል መሠረት የጠላቶቻቸው ጠላት እንዲሆንላቸው የተቃዋሚዎቻቸው ተቃዋሚ እንዲሆን ይለምኑት ጀመር። 27 ከዚህ ጸሎት በኋላ የጦር መሣሪያዎቻቸውን ይዘው ከከተማው በጣም ርቀው ገሠገሡ፤ ከጠላት አጠገብ በደረሱ ጊዜ ቆሙ። 28 በጠዋት የፀሐይ ብርሃን በታየ ጊዜ በዚህም በዚያም ውጊያውን ጀመሩ፤ ግማሾቹ በእግዚአብሔር ተማጥነው በጀግንነታቸው እንደሚቀናቸውና ድል እንደሚነሱ ዋስትና ኖሯቸው፥ ሌሎቹ ቁጣቸውን የውጊያው መሪ አድርገው ይዋጉ ነበር። 29 ጦርነቱ እጅግ በተጋጋለም ጊዜ የወርቅ ልጓም ባላቸው ፈረሶች ላይ የተቀመጡ አይሁዳውያንን የሚመሩ አምስት መልከ መልካም ሰዎች ከሰማይ ለጠላቶች ታዩ። 30 ይሁዳ መቃቢስን በመካከላቸው አድርገው በጋሻቸው እየተከላከሉለት እንዳይነካ ይጠብቁት ነበር፤ በጠላቶች ላይ ግን ቀስትና መብረቅ ይወረውሩ ነበር፤ በዚህ ዓይነት ጠላቶች ተደናግጠውና ዐይኖቻቸውን ታውረው ወዲያና ወዲህ ተበታተኑ። 31 ሃያ ሺህ አምስት መቶ የእግረኛ ጦር ወታደሮችና ስድስት መቶ ፈረሰኞች ተገደሉ። 32 ጢሞቴዎስም ቀርአስ ወደሚያዝባት በብርቱ ወደምትጠበቀው ጋዜር ወደምትባለው ምሽግ ሄደ። 33 ግን ይሁዳ መቃቢስና የእርሱ ሰዎች ደስ እያላቸው አራት ቀን ከበው አስጨነቋት፤ 34 በውስጧ የሚገኙ ሰዎች በቦታው አለመደፈር ተማምነው ብዙ ይሳደቡ ነበር፤ መጥፎ ቃላትም በመናገር አልተቆጠቡመ ነበር። 35 አምስተኛው ቀን በሆነ ጊዜ የአይሁድ መቃቢስ ሃያ ወጣት ወታደሮች በስድባቸው በጣም ተናደው፥ በወንድነት ጀግንነትና በታላቅ ቁጣ ተነሣሥተው ወደ ታላቁ ግንብ እየዘለሉ ወጡና እዚያ ያገኟቸውን ሁሉ ገደሉ። 36 ሌሎችም በዚሁ ዓይነት በግንቡ ውስጥ ወደነበሩት ሰዎች በሌላ በኩል ገብተው ግንቦቹን አቃጠሉ፤ እሳት አንድደውም ተሳዳቢዎቹን በሕይወታቸው እያሉ አቃጠሉዋቸው። የፊተኞቹ ወታደሮች መዝጊያዎቹን ሰባበሩና የቀረውን ጦር ሠራዊት አስገቡ፤ ከተማዋን ለመያዝም የመጀመሪያዎቹ ሆኑ። 37 በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ተደብቆ የነበረውንም ጢሞቴዎስን ገደሉት፤ ከእርሱም ጋር ወንድሙን ቀሪያንና አጶሎፋንንም ገደሉ። 38 ይህንን ካደረጉ በኋላ በእስራኤል ብዙ መልካም ነገር ያደረገላቸውንና ድልን የሰጣቸውን አምላክ በዝማሬና በውዳሴ አመሰገኑት። |