ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ 2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ሁለተኛ መቃብያን በግብጽ ላሉ አይሁዳውያን የተጻፈ ደብዳቤ የመጀመሪያው ደብዳቤ 1 የኢየሩሳሌም አይሁዳውያን፤ ወንድሞቻቸውና በአይሁድ አገር የሚገኙ ሰዎች፥ በግብጽ አገር ለሚገኙ አይሁዳውያን ወንድሞቻቸው ሰላምታ ያቀርባሉ፤ ሰላምና ብልጽግና ይመኙላቸዋል። 2 እግዚአብሔር መልካሙን ነገር ያድርግላችሁ፤ ከታማኝ አገልጋዮቹ ከአብርሃም፤ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን ያስታውስ። 3 እርሱን የምታመልኩበትንና በለጋስነት፥ በመልካም ፈቃድ የእርሱን ፈቃድ የምትፈጽሙበትን ልብ ለሁላችሁም ይስጥ። 4 ለእርሱ ሕግና ትዕዛዞች ልባችሁ እንዲከፈት ያድርግላችሁ፤ ሰላምም ያድርግላችሁ። 5 ጸሎታችሁን ሰምቶ ይታረቃችሁ፤ በመከራ ጊዜ አይተዋችሁ፤ 6 በዚህ ጊዜ ከእርሱ የምንለምንላችሁ ይህንኑ ነው። 7 በዲሜጥሮስ መንግሥት ጊዜ እኛ አይሁዳውያን በመቶ ስልሳ ዘጠኝ ዓመተ ዓለም እንዲህ ስንል ጽፈንላችኋል፤ “በእነዚያ ዓመታት ኢያሶንና የእርሱ ሰዎች ከቅድስት ምድር ከመንግሥት ተለይተው ከከዱበት ጊዜ ጀምሮ በወደቀብን መከራና ስደት ዘመን፤ 8 የቤተ መቅደሱን ታላቅ መዝጊያ እስከ ማቃጠልና ንጹሕ ደም እስከ ማፍሰስ ደርሰዋል፤ መሥዋዕትና የስንዴ ዱቄት አቅርበናል፤ መብራት አብርተናል፤ ኀብስትም አስቀምጠናል”። 9 አሁንም የምንጽፍላችሁ በከሴሎ ወር የሚውለውን የቂጣ (የድንኳን) በዓል እንድታከብሩ ነው። 10 በመቶ ሰማንያ ስምንት ዓመተ ዓለም ተጻፈ። ሁለተኛው ደብዳቤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ አገር የሚገኙ ሰዎች፤ የይሁዳ ምክር ቤትና የይሁዳ ንጉሥ ጰጠሎሜዎስ አማካሪ፤ ከተቀቡት የካህናት ዘር ወገን ለሆነው ለአርስጦብሎስና በግብጽ አገር ለሚገኙ አይሁዳውያን ሰላምና ጤና ይሁን። አንጥዮኩስ በመቀጣቱ የቀረበ ምስጋና 11 እኛ በአምላክ ቸርነት ከታላላቅ አደጋዎች የዳንን ከንጉሡ ጋር ባደረግነው ውጊያ ለረዳን አምላክ ትልቅ ምስጋና እናቀርባለን፤ 12 ምክንያቱም የጦር መሣሪያ ይዘው በቅድስት ከተማ ላይ የመጡትን እርሱ ራሱ አባሮልናል። 13 መሪያቸው የማይበገር ይመስል ከነበረው ከብዙ ሠራዊቱ ጋር ወደ ፋርስ ሄደ፤ እርሱም፥ ሠራዊቱም የጣዖቷ የናንያ ካህናት በተንኮል ባጠመዱባቸው ወጥመድ ውስጥ ገብተው በጣዖቷ በናንያ ቤት ውስጥ ተጨፈጨፉ፤ 14 አንጥዮኩስ ወዳጆቹን አስከትሎ ጣዖቷን ሚስት ለማድረግ ያሰበ መስሎ የጣዖቷን ከፍተኛ ሀብት በጥሎሽ መልክ ለመውሰድ ወደ እዚያ ቦታ ሄደ፤ 15 የናንያ ካህናት ወርቁንና ብሩን አወጡና አሳዩት፤ ንጉሡም አንዳንድ አጃቢዎች አስከትሎ ወደ ጣዖቷ ቤት ውስጥ ገባ፤ እነርሱ ግን አንጥዮኩስ ወደ ጣዖቷ ቤት እንደ ገባ ወዲያውኑ በሩን ዘጉ። 16 በጣሪያው በኩል ያለውን የምሥጢር (ሥውር) በር ከፍተው ድንጋይ እየወረወሩ ሹሙን ቀጠቀጡት፤ ሰውነቱንና ራሱንም ቆራርጠው በውጭ ወዳሉት ሰዎች ጣሉባቸው። 17 ቅዱስ ነገርን ያረከሱ ሰዎችን ለሞት አሳልፎ የሰጠ አምላካችን በሁሉ ነገር የተመሰገነ ይሁን። የተቀደሰው እሳት ተጠብቆ የቆየበት ተአምር 18 በኬሰሎ ወር በሃያ አምስተኛው ቀን የቤተ መቅደሱን መንጻት በዓል ስለምናከብር ነህምያ ቤተ መቅደሱንና መሠዊያውን ሠርቶ መሥዋዕትን ባቀረበ ጊዜ እንደታየው እሳትና እንደ ቂጣ (ድንኳን) በዓል ዓይነት እናንተም በዓሉን እንድታከብሩ ለእናንተ ማስታወቅ የተገባ ሆኖ ታየን። 19 ምክንያቱም አባቶቻችን ተማርከው ወደ ፋርስ በተወሰዱ ጊዜ በዚያን ጊዜ የነበሩ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ካህናት ከመሠዊያው እሳት ወስደው ውሃ በሌለበት ደረቅ ጉድጓድ በሚመስለው ቀዳዳ ውስጥ በስውር ደበቁት፤ ማንም ሳያውቀው እዚያ እንዲቀመጥ አደረጉት። 20 ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ ነህምያ በፋርስ ንጉሥ ተልኮ እነዚያ እሳቱን ደብቀውት የነበሩ ካህናት የልጅ ልጆቻቸው እንዲፈልጉት አዘዛቸው፤ ግን ያገኙት እሳት ሳይሆን የረጋ ውሃ መሆኑን ተናገሩ፤ እሱም ለምርመራ ቀድተው እንዲያመጡ አዘዛቸው። 21 መሥዋዕት ለማቅረብ ሁሉ ነገር በተዘጋጀ ጊዜ ነህምያ በእንጨትና በቀረቡት መሥዋዕቶች ላይ ካህናቶቹ ይህን ፈሳሽ እንዲረጩ አዘዛቸው። 22 ይህን ባደረጉ ጊዜ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በደመና ተሸፍና የነበረችው ፀሐይ ወጣችና አበራች፤ ሁሉም እስኪደነቁ አንድ ትልቅ እሳት ነደደ። 23 እሳቱ መሥዋዕቱን በሚያቃጥልበት ጊዜ ካህናት ይጸልዩ ነበር፤ ከካህናቱ ጋር እዚያ የነበሩት ሁሉ፥ ዮናታን እያቀነቀነ፥ ሎሎቹ ከነህምያ ጋር ሆነው እየመለሱ ይዘምሩ ነበር። 24 ጸሎቱም እንዲህ ይል ነበር፥ “ጌታ እግዚአብሔር አምላካችን የሁሉ ነገር ፈጣሪ፤ አስፈሪ፥ ኃያል፥ ጻድቅ፥ መሐሪ፥ አንተ ብቻ ንጉሥ ነህ፤ አንተ ብቻ ደግ ነህ፤ 25 አንተ ብቻ ለጋስ፥ አንተ ብቻ ጻድቅ፥ ሁሉን የምትችልና ዘላለማዊ እስራኤልን ከክፉ ሁሉ የምታድን፥ አባቶቻችን ለአንተ የተመረጡ እንዲሆኑ ያደረግሃቸውና የቀደስሃቸው፥ 26 ስለ እስራኤል ሕዝብ ሁሉ ይህን መሥዋዕት ተቀበል፤ ርስትህን ጠብቀው፤ ቀድሰውም። 27 ከመካከላችን ርቀውና ተበታትነው የሚገኙትን ሰብስባቸው፥ በአረማውያን መካከል በባርነት የሚገኙትን ነጻ አውጣቸው፤ አንተ የእኛ አምላክ መሆንህን አረማውያን እንዲያውቁ የተናቁትንና የተጣሉትን በመልካም ዐይን ተመልከታቸው፥ 28 የሚጨቁኑንንና በትዕቢት የሚበድሉንን ቅጣቸው፤ 29 ሙሴ እንዳለው ሕዝብህንም በቅዱስ ሀገር ላይ ትከለው።” 30 ካህናቱ ይከምሩ ነበር፤ 31 መሥዋዕት ተቃጥሎ ባለቀ ጊዜ የተረፈውን ውሃ በታላላቅ ድንጋዮች ላይ እንዲያፈሱ ነህምያ አዘዘ፤ 32 ይህ በተደረገ ጊዜ ነበለባል ነደደ፤ ግን ከመሠዊያው የሚወጣው ብርሃን ዋጠው። 33 ነገሩ በታወቀ ጊዜና ተማርከው የተወሰዱ ካህናት እሳት በደበቁበት ቦታ ነህምያና ጓደኞቹ መሥዋዕት የተቀደሱበት ውሃ መገኘቱን ለፋርስ ንጉሥ በነገሩት ጊዜ፤ 34 ንጉሡ ይህን ቦታ አሳጠረና ነገሩን ካረጋገጠ በኋላ ቅዱስ ቦታ አደረገው። 35 ንጉሡ ለፈቀደላቸው ሰዎች ከዚያ ከሚገኘው ግቢ ብዙ ስጦታዎች ይሰጣቸው ነበር። 36 ነህምያና ከእርሱ ጋር ያሉት ሰዎች ይህን ውሃ ኔፍታር ብለው ጠሩት፤ ትርጉሙ “ንጽሕና” ማለት ነው፤ ብዙ ሰዎች ግን “ናፍታ” ይሉታል። |