2 ነገሥት 8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የሱነም ከተማ ነዋሪ የነበረችው ሴት ከስደት መመለስ 1 ልጇን ከሞት ያስነሣላትን፥ በሱነም ትኖር የነበረችውን ሴት እነሆ፥ ኤልሳዕ አስቀድሞ እንዲህ ሲል ነግሮአት ነበር፥ “እግዚአብሔር እስከ ሰባት ዓመት የሚቆይ ራብ በዚህች ምድር ላይ ልኮአል፤ ከቤተሰብሽ ጋር በሕይወት ለመትረፍ ከዚህ ተነሥተሽ ወደ ሌላ ስፍራ ሂጂ።” 2 ስለዚህም የኤልሳዕን ምክር ሰምታ ከነቤተሰብዋ ወደ ፍልስጥኤም አገር በመሰደድ እስከ ሰባት ዓመት ቆየች። 3 ከሰባቱም የራብ ዓመቶች ፍጻሜ በኋላ ወደ እስራኤል ተመለሰች፤ መኖሪያ ቤትዋና የእርሻ መሬትዋ እንዲመለስላት ለመጠየቅ ወደ ንጉሡ ቀረበች። 4 ንጉሡንም የኤልሳዕ አገልጋይ ከሆነው ከግያዝ ጋር ሲነጋገር አገኘችው፤ ንጉሡ ከግያዝ ጋር የሚነጋገረውም ኤልሳዕ ስላደረጋቸው ተአምራት ለማወቅ ፈልጎ ነበር፤ 5 ኤልሳዕ የሞተ ሰው ማስነሣቱን ግያዝ ለንጉሡ በሚነግርበት ጊዜ ሴቲቱ መጥታ አቤቱታዋን ለንጉሡ አቀረበች፤ ግያዝ “ንጉሥ ሆይ! ሴትዮዋ እነሆ፥ ይህች ናት፤ ኤልሳዕ ከሞት ያስነሣውም ልጇ ይሄ ነው!” በማለት ለንጉሡ አስረዳ። 6 ግያዝ ለንጉሡ የሰጠውን መልስ ሴትዮዋ ለንጉሡ እውነት መሆኑን አረጋገጠችለት፤ ስለዚህም ንጉሡ አንድ ባለ ሥልጣን ጠርቶ፥ የእርሷ የሆነው ማናቸውም ነገርና እንዲሁም የእርሻ መሬትዋ በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ያስገኘው የእህል ሰብል ጭምር እንዲመለስላት ትእዛዝ ሰጠላት። ኤልሳዕና የሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ 7 የሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ በታመመ ጊዜ ኤልሳዕ ወደ ደማስቆ ሄደ፤ ንጉሡም የኤልሳዕን መምጣት ሰማ፤ 8 ባለሟሎቹ ከሆኑት ባለ ሥልጣኖች አንዱ የሆነውን አዛሄልን ጠርቶ፥ “ለነቢዩ ስጦታ ይዘህ ሂድና እኔ ከዚህ በሽታ እድን ወይም አልድን እንደሆነ እግዚአብሔርን እንዲጠይቅልኝ ለምነው” አለው። 9 ስለዚህም አዛሄል በደማስቆ ከሚገኘው ምርጥ የምድር በረከት ሁሉ በአርባ ግመሎች ጭኖ ወደ ኤልሳዕ ሄደ፤ አዛሄልም ኤልሳዕን ባገኘው ጊዜ “ልጅህ ንጉሥ ቤንሀዳድ ከሕመሙ ይድን ወይም አይድን እንደሆነ እንድትነግረው እጠይቅህ ዘንድ ልኮኛል” አለው። 10 ኤልሳዕም “ቤንሀዳድ እንደሚሞት እግዚአብሔር ገልጦልኛል፤ አንተ ግን ትድናለህ ብለህ ንገረው” አለው፤ 11 ከዚህ በኋላ ኤልሳዕ ፊቱን በማጥቆር በሚያስፈራ ሁኔታ አዛሄልን ተመለከተው፤ ከዚህም የተነሣ አዛሄል ተጨነቀ፤ ወዲያውም ኤልሳዕ እንባውን ማፍሰስ ጀመረ፤ 12 አዛሄልም “ጌታዬ ስለምን ታለቅሳለህ?” ሲል ጠየቀው። ኤልሳዕም “በእስራኤል ሕዝብ ላይ የምትፈጽመውን አሠቃቂ ነገር ስለማውቅ ነው፤ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ምርጥ የሆኑ ወጣቶቻቸውን ታርዳለህ፤ ሕፃናታቸውን በድንጋይ ላይ ትፈጠፍጣለህ፤ እርጉዞች የሆኑ ሴቶቻቸውንም ሆድ ትሰነጥቃለህ” ሲል መለሰለት። 13 አዛሄልም “እኔ ለምንም የማልጠቅም ኢምንት ነኝ! ታዲያ ይህን ሁሉ ለማድረግ የሚያስችለውን ኃይል ከቶ ከየት አገኛለሁ?” ሲል ጠየቀ። ኤልሳዕም “አንተ የሶርያ ንጉሥ እንደምትሆን እግዚአብሔር ገልጦልኛል” ሲል መለሰለት። 14 ከዚህም በኋላ አዛሄል ተመልሶ ሲመጣ “ኤልሳዕ ምን አለህ?” ሲል ቤንሀዳድ ጠየቀው። አዛሄልም “አንተ በእርግጥ እንደምትድን ነግሮኛል” ሲል መለሰለት። 15 ነገር ግን በማግስቱ አዛሄል ብርድልብስ ወስዶ ውሃ ውስጥ ነከረ፤ በዚያም ንጉሡን አፍኖ ገደለው። አዛሄልም በቤንሀዳድ እግር ተተክቶ የሶርያ ንጉሥ ሆነ። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮራም ( 2ዜ.መ. 21፥1-20 ) 16 የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም በይሁዳ ላይ ነገሠ፤ 17 እርሱም በነገሠ ጊዜ ሠላሳ ሁለት ዓመቱ ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ስምንት ዓመት ገዛ። 18 ሚስቱም የአክዓብ ልጅ ስለ ነበረች እንደ አክዓብ ቤተሰብ የእስራኤል ነገሥታት ይፈጽሙት የነበረውን የክፋት መንገድ ተከተለ፤ በደል በመሥራትም እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ 19 እግዚአብሔር ግን ከዘሩ መንግሥትን እንደማያጠፋ ለአገልጋዩ ለዳዊት ተስፋ ሰጥቶት ስለ ነበር ይሁዳን መደምሰስ አልፈለገም። 20 በኢዮራም ዘመነ መንግሥት ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐመፀ፤ የራሱንም ነጻ መንግሥት ዐወጀ፤ 21 ስለዚህም ኢዮራም ሠረገሎቹን በመላ አሰልፎ ወደ ጻዒር ዘመተ፤ የኤዶም ሠራዊትም ከበባቸው፤ በሌሊትም እርሱና የሠረገላዎቹ አዛዦች ከበባውን ጥሰው ሲያመልጡ፥ ወታደሮቹ ወደየቤታቸው ተበታተኑ፤ 22 ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ኤዶም ከይሁዳ ተገዢነት ነጻ ወጣች፤ በዚያኑ ጊዜም የልብና ከተማ ዐመፀች። 23 ኢዮራም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ 24 ኢዮራም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ ውስጥ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አካዝያስ ነገሠ። የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ ( 2ዜ.መ. 22፥1-6 ) 25 የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት የኢዮራም ልጅ አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 26 በነገሠም ጊዜ የሀያ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ አንድ ዓመት ብቻ ገዛ፤ እናቱ ዐታልያ ተብላ የምትጠራው የአክዓብ ልጅ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው የዖምሪ የልጅ ልጅ ነበረች። 27 አካዝያስ የንጉሥ አክዓብ ዐማች ከመሆኑ የተነሣ ልክ እንደ አክዓብ ቤተሰብ ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ። 28 በሶርያው ንጉሥ አዛሄል ላይ በታወጀው ጦርነት፥ ንጉሥ አካዝያስ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራም ተባባሪ በመሆን ዘመተ፤ የሁለቱም ነገሥታት ሠራዊት ከሶርያውያን ሠራዊት ጋር በገለዓድ በምትገኘው በራሞት ጦርነት በገጠመ ጊዜ ኢዮራም በውጊያው ላይ ቆሰለ፤ 29 ኢዮራምም ከንጉሥ አዛሄል ጋር ሆኖ በሬማት በተደረገው ጦርነት የደረሰበትን ቁስል ለመፈወስ ወደ ኢይዝራኤል ከተማ ተመለሰ። የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በደረሰበት ጉዳት እርሱን ለመጠየቅ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ሊጠይቀው ወደ ኢይዝራኤል ከተማ ሄደ። |