2 ነገሥት 6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ሰጥሞ የነበረው መጥረቢያ በተአምር መውጣቱ 1 በኤልሳዕ ኀላፊነት ሥር የነበሩት የነቢያት ጉባኤ አባላት፥ “የምንኖርበት ስፍራ ጠባብ ነው፤ 2 ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄደን ዛፍ በመቁረጥ የምንኖርበት ቤት በዚያ እንድንሠራ ፍቀድልን!” አሉት። ኤልሳዕም “እሺ መልካም ነው!” አላቸው። 3 ከነቢያቱም አንዱ ኤልሳዕን አብሮአቸው እንዲሄድ ጠየቀው፤ ኤልሳዕም በጥያቄው ተስማማ፤ 4 አብረውም ሄዱ፤ ወደ ዮርዳኖስም በደረሱ ጊዜ ዛፍ የመቁረጥ ተግባራቸውን ጀመሩ፤ 5 ከእነርሱም አንዱ ዛፍ በመቁረጥ ላይ ሳለ በድንገት መጥረቢያው ከዛቢያው ላይ ወድቆ ውሃ ውስጥ ገባ፤ እርሱም ድምፁን ከፍ አድርጎ በመጮኽ “ጌታዬ ሆይ! እንግዲህ ምን አደርጋለሁ? መጥረቢያው የተውሶ ነው!” ሲል ለኤልሳዕ ነገረው። 6 ኤልሳዕም “በየት በኩል ነው የወደቀው?” ሲል ጠየቀው። ሰውየውም መጥረቢያው የወደቀበትን ስፍራ ባሳየው ጊዜ እርሱ አንድ እንጨት ቆርጦ ወደ ውሃው ውስጥ በመጣል መጥረቢያው እንዲንሳፈፍ አደረገው፤ 7 ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ “አውጥተህ ውሰድ” አለው፤ ሰውየውም ጐንበስ ብሎ አነሣው። የሶርያ የጦር ሠራዊት ድል መሆን 8 እነሆ፥ የሶርያ ንጉሥ ከእስራኤል ጋር በጦርነት ላይ ነበር፤ እርሱም ከጦር አዛዥውቹ ጋር ተማክሮ የሚሰፍሩበትን ቦታ መረጠ፤ 9 ኤልሳዕ ግን “ሶርያውያን ደፈጣ አድርገው ስለሚጠብቁህ ወደዚያ ስፍራ አትቅረብ” ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ላከ። 10 ስለዚህም የእስራኤል ንጉሥ በዚያ የሚኖሩትን ወታደሮቹን ስላስጠነቀቃቸው ነቅተው ይጠባበቁ ነበር፤ ይህም ድርጊት ብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ ተፈጸመ። 11 “ከእኛ መካከል ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ግኑኝነት ያለው ማን እንደሆነ አትነግሩኝምን?” ሲል ጠየቃቸው። 12 ከእነርሱም አንዱ “ንጉሥ ሆይ፥ ከእኛ መካከል ይህን የሚያደርግ ማንም የለም፤ በመኝታ ክፍልህ እንኳ ሆነህ የምትናገረውን ሁሉ ሳይቀር ለእስራኤል ንጉሥ ምሥጢሩን የሚገልጥለት ኤልሳዕ የተባለው ነቢይ ነው” ሲል መለሰለት። 13 የሶርያም ንጉሥ “እርሱ የሚገኝበትን ስፍራ ፈልጉ፤ እኔም ልኬ እማርከዋለሁ” አላቸው። በዚህም ጊዜ ኤልሳዕ በዶታን የሚኖር መሆኑ ተነገረው፤ 14 ንጉሡ በፈረሶችና በሠረገሎች የተጠናከረ ሠራዊት ወደዚያ ላከ፤ እነርሱም በሌሊት ደርሰው ከተማይቱን ከበቡ። 15 በማግስቱም ማለዳ የኤልሳዕ አገልጋይ ከመኝታው ተነሥቶ፥ ከቤት ሲወጣ በፈረሶችና በሠረገሎች የታጀቡ የሶርያ ወታደሮች ከተማይቱን መክበባቸውን አየ፤ ወደ ኤልሳዕም ተመልሶ ድምፁን ከፍ በማድረግ “ጌታዬ ወዮ! ምን ማድረግ ይሻለናል?” ሲል ጠየቀው። 16 ኤልሳዕም “አይዞህ አትፍራ፤ ከእነርሱ ጋር ከተሰለፈው ይልቅ ከእኛ ጋር የተሰለፈው ሠራዊት ይበልጣል” አለው። 17 ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ “እግዚአብሔር ሆይ! ማየት እንዲችል ዐይኖቹን ክፈትለት!” ሲል ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የኤልሳዕ አገልጋይ ዐይኖቹ እንዲከፈቱለት ስላደረገ፥ በኰረብታው ጐን ብዙ የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተሰልፈው የሚጠብቁት መሆናቸውን ተመለከተ። 18 ሶርያውያንም ወደ እርሱ በወረዱ ጊዜ ኤልሳዕ “እግዚአብሔር ሆይ! እነዚህ ሰዎች እንዲታወሩ አድርግ!” ብሎ ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የኤልሳዕን ጸሎት በመስማት፥ ዐይኖቻቸው እንዲታወሩ አደረገ። 19 ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ ወደ እነርሱ ቀረብ ብሎ “መንገድ ተሳስታችኋል፤ የምትፈልጓት ከተማ ይህች አይደለችም፤ ይልቅስ ወደምትፈልጉት ሰው እኔ ልመራችሁ ስለምችል ተከተሉኝ” ብሎ ወደ ሰማርያ መራቸው። 20 ወደ ከተማይቱም እንደ ገቡ ኤልሳዕ “እግዚአብሔር ሆይ! ማየት እንዲችሉ ዐይኖቻቸውን ግለጥላቸው!” ሲል ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ዐይኖቻቸውን በከፈተላቸው ጊዜ በሰማርያ ውስጥ መሆናቸውን ተረዱ። 21 የእስራኤልም ንጉሥ ሶርያውያንን ባያቸው ጊዜ “ጌታዬ ሆይ! ልግደላቸውን? ልግደላቸውን?” ሲል ኤልሳዕን ጠየቀው። 22 ኤልሳዕም “አይሆንም! እንኳን እነዚህን፥ በሰይፍህና በቀስትህ የማረክኻቸውን ወታደሮች መግደል አይገባህም፤ ይልቅስ የሚበሉትና የሚጠጡትን ምግብ አቅርብላቸውና ወደ ንጉሣቸው ተመልሰው እንዲሄዱ አድርግ” አለው። 23 ስለዚህም የእስራኤል ንጉሥ ለእነርሱ ታላቅ ግብዣ አደረገላቸው፤ ከበሉና ከጠጡም በኋላ ወደ ሶርያ ንጉሥ መልሶ ላካቸው፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ሶርያውያን በእስራኤል ምድር ላይ ወረራ ማድረጋቸውን አቆሙ። የሰማርያ መከበብ 24 ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ መላ ሠራዊቱን በእስራኤል ላይ በማዝመት፥ የሰማርያን ከተማ ከበበ፤ 25 ከበባውም የምግብን እጥረትና ብርቱ ራብ ከማስከተሉ የተነሣ፥ የአንድ አህያ ራስ ዋጋ እስከ ሰማኒያ ጥሬ ብር፥ ሁለት መቶ ግራም የሚያኽል የርግብ ኩስ ዋጋ ደግሞ አምስት ጥሬ ብር ማውጣት ጀመረ። 26 አንድ ቀን የእስራኤል ንጉሥ በከተማይቱ የቅጽር ግንብ ላይ በሚመላለስበት ጊዜ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “ንጉሥ ሆይ፥ እባክህ እርዳኝ!” ስትል ጮኸች። 27 ንጉሡም “እግዚአብሔር ሊረዳሽ ካልፈቀደ እኔ ምን ዓይነት እርዳታ ልሰጥሽ እችላለሁ? ከአውድማው ወይስ ከወይን መጭመቂያው? ምን ያለኝ ይመስልሻል? 28 ለመሆኑ ችግርሽ ምንድነው?” ሲል ጠየቃት። እርሷም እንዲህ ስትል መለሰችለት፤ “ባለፈው ቀን ይህች ሴት ‘ዛሬ የአንቺን ልጅ እንብላ፤ በማግስቱ ደግሞ የእኔን ልጅ እንበላለን’ ስትል ሐሳብ አቀረበች። 29 ስለዚህም የእኔን ልጅ ቀቅለን በላን፤ በማግስቱም ‘ልጅሽን አምጪና እንብላ’ ብዬ ጠየቅኋት፤ እርሷ ግን ደበቀችው።” 30 ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ በኀዘን ልብሱን ቀደደ፤ በግንቡ ላይ በመሆኑ በአቅራቢያው የነበረው ሕዝብ ንጉሡ ከልብሱ በውስጥ በኩል ማቅ ለብሶ እንደ ነበር አዩ። 31 ንጉሡም ድምፁን ከፍ በማድረግ “የዛሬይቱ ጀንበር ከመጥለቅዋ በፊት የሳፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ሳይቆረጥ ቢያድር እግዚአብሔር እኔን በሞት ይቅጣኝ!” ሲል ተናገረ። 32 ወዲያውኑም ኤልሳዕን ይዞ የሚመጣ መልእክተኛ ላከ። በዚህም ጊዜ ኤልሳዕ ሊጐበኙት ከመጡ ጥቂት ሽማግሌዎች ጋር በቤት ውስጥ ነበር፤ የንጉሡ መልእክተኛ ከመድረሱም በፊት ኤልሳዕ ሽማግሌዎቹን “ያ ነፍሰ ገዳይ እኔን ለማስገደል አንድ ሰው ልኮአል! እነሆ፥ እርሱ እዚህ በሚደርስበት ጊዜ በሩን ዝጉ፤ ወደ ውስጥም እንዲገባ አትፍቀዱለት፤ ንጉሡም እርሱን ተከትሎ መጥቶ በኋላው ይገኛል” አላቸው። 33 ገና ይህን ተናግሮ ሳይጨርስ ንጉሡ ድንገት ከተፍ ብሎ “ይህን መከራ በእኛ ላይ ያመጣብን እግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ እርሱ አንድ ነገር ያደርግ ዘንድ ከዚህ በላይ ምን ልጠብቅ?” አለ። |