Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

2 ነገሥት 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


በእስራኤልና በሞዓብ መካከል የተደረገ ጦርነት

1 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ዐሥራ ሁለት ዓመት ገዛ፤

2 እርሱም ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ ይሁን እንጂ እርሱ የአባቱንና የእናቱን የኤልዛቤልን ያኽል መጥፎ ሰው አልነበረም፤ ባዓል ተብሎ የሚጠራውን ባዕድ አምላክ ለማምለክ አባቱ አሠርቶት የነበረውን ምስል አስወገደ፤

3 ይህም ሆኖ ከእርሱ በፊት እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራው የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን አምልኮ ተከተለ እንጂ አላስወገደውም።

4 የሞዓብ ንጉሥ ሜሻዕ በግ አርቢ ነበር፤ በየዓመቱም አንድ መቶ ሺህ ጠቦትና የአንድ መቶ ሺህ በጎች ጠጉር ለእስራኤል ንጉሥ ይገብር ነበር፤

5 ነገር ግን የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በሞተ ጊዜ የሞዓብ ንጉሥ ሜሻዕ በእስራኤል ላይ ዐመፀ።

6 በዚያን ጊዜ ንጉሥ ኢዮራም ወዲያውኑ ከሰማርያ ወጥቶ ወታደሮቹን ሁሉ በአንድነት ሰበሰበ፤

7 ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ኢዮሣፍጥም “የሞዓብ ንጉሥ በእኔ ላይ አምፆብኛል፤ በእርሱ ላይ በማደርገው ጦርነት ከእኔ ጋር ትተባበራለህን?” የሚል መልእክት ላከ። ንጉሥ ኢዮሣፍጥም “አዎ እተባበርሃለሁ፤ እኔን እንደ አንተ፥ ሠራዊቴን እንደ ሠራዊትህ፥ ፈረሶቼን እንደ ፈረሶችህ መቁጠር ትችላለህ” ሲል ከመለሰ በኋላ፥

8 ዳሩ ግን “አደጋ ለመጣል የምንጓዘው በየትኛው መንገድ ነው?” ሲል ጠየቀው። ንጉሥ ኢዮራምም “በኤዶም በረሓ የሚገኘውን ዙሪያ መንገድ ይዘን እንጓዛለን” ሲል መለሰለት።

9 ስለዚህም ንጉሥ ኢዮራምና እንዲሁም የይሁዳና የኤዶም ነገሥታት ለዘመቻ ወጡ፤ ከሰባት ቀን ጉዞም በኋላ ውሃ አለቀባቸው፤ ለሠራዊቱም ሆነ ለጭነት እንስሶች ምንም ውሃ አልነበረም።

10 ንጉሥ ኢዮራምም “እግዚአብሔር ሦስታችንንም ነገሥታት ለሞዓብ ንጉሥ አሳልፎ ሊሰጠን ነውና ወዮልን!” ሲል ጮኸ።

11 ንጉሥ ኢዮሣፍጥም “በእርሱ አማካይነት እግዚአብሔርን መጠየቅ እንድንችል በዚህ አንድም ነቢይ የለምን?” ሲል ጠየቀ። ከንጉሥ ኢዮራም ሠራዊት አዛዦች አንዱ፥ “ቀድሞ የኤልያስ ረዳት የነበረው የሣፋጥ ልጅ ኤልሳዕ እዚህ አለ” ሲል መልስ ሰጠ።

12 ንጉሥ ኢዮሣፍጥም “የእግዚአብሔር ቃል በእርሱ ዘንድ ይገኛል” አለ፤ ከዚያም በኋላ ሦስቱም ነገሥታት ወደ ኤልሳዕ ሄዱ።

13 ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ ኢዮራምን፥ “እኔ አንተን የምረዳህ ስለምንድን ነው? ሄደህ አባትህና እናትህ ይጠይቁአቸው የነበሩትን እነዚያን ነቢያት ጠይቅ!” አለው። ንጉሥ ኢዮራምም መልሶ፥ “አይደለም እኮ! ሦስታችንንም ነገሥታት ለሞዓብ ንጉሥ አሳልፎ ለመስጠት የጠራን እግዚአብሔር ነው” አለ።

14 ኤልሳዕም “እኔ በማገለግለው በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ! አንተን ለመርዳት ለመጣው ለይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ክብር ስል ነው እንጂ፥ ለአንተስ ምንም ነገር ላደርግልህ ባልተገባ ነበር፤

15 አሁንም በገና የሚደረድር ሰው አምጡልኝ” አለ። ባለ በገናውም በሚደረድርበት ጊዜ የእግዚአብሔር ኃይል በኤልሳዕ ላይ ወርዶ እንዲህ አለ፤

16 “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘በዚህ የደረቀ ሸለቆ ሁሉ የውሃ ጉድጓድ ቆፍሩ፤

17 ምንም ዝናብና ነፋስ ባታዩም፥ ይህ ሸለቆ በውሃ የተሞላ ይሆናል፤ እናንተ፥ የቀንድ ከብቶቻችሁና የጭነት እንስሶቻችሁ ሁሉ የምትጠጡት በቂ ውሃ ታገኛላችሁ።’

18 ነገር ግን ይህን ማድረግ በእግዚአብሔር ዘንድ ቀላል ነገር ነው፤ ከዚህም በላይ እርሱ በሞአባውያን ላይ ድልን ያጐናጽፋችኋል።

19 የተመሸጉና ምርጥ የሆኑ ከተሞቻቸውን ሁሉ ድል አድርጋችሁ ትይዛላችሁ፤ የፍራፍሬ ዛፎቻቸውን ሁሉ ትቆርጣላችሁ፤ ምንጮቻቸውን ትደፍናላችሁ፤ ለም የሆኑ የእርሻ ቦታዎቻቸውን በማበላሸት ድንጋይ ትከምሩባቸዋላችሁ።”

20 በማግስቱም ጠዋት መሥዋዕት የሚቀርብበት ሰዓት ሲደርስ ከኤዶም በኩል የውሃ ምንጭ ፈልቆ ምድሩን ሸፈነው።

21 ሞዓባውያንም ሦስቱ ነገሥታት አደጋ ሊጥሉባቸው መምጣታቸውን በሰሙ ጊዜ፥ ከሽማግሌ እስከ ወጣት መሣሪያ መያዝ የሚችሉ ሰዎች ሁሉ ተጠርተው በመውጣት በጠረፉ ላይ ተጠባበቁ።

22 በማግስቱም ጠዋት ከእንቅልፋቸው ነቅተው ሲመለከቱ፥ በውሃው ላይ የሚያበራው የፀሐይ ነጸብራቅ እንደ ደም መስሎ ታያቸው፤

23 ስለዚህም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በመጮኽ “ይህ ነገር ደም ነው! የሦስቱ ጠላቶቻችን ሠራዊቶች እርስ በርሳቸው በመተራረድ ተላልቀዋል! እንግዲህ ሄደን ሰፈራቸውን እንዝረፍ!” ተባባሉ።

24 ነገር ግን እነርሱ ወደ ሰፈር በደረሱ ጊዜ እስራኤላውያን ተነሥተው አደጋ በመጣል ወደ ኋላ መለሱአቸው፤ እስራኤላውያን አገሪቱን ወረው ሞዓባውያንን ጨፈጨፉአቸው።

25 ከተሞቻቸውን ደመሰሱ፤ ለም በሆነው እርሻ ውስጥ በሚያልፉበትም ጊዜ እያንዳንዱ እስራኤላዊ አንዳንድ ድንጋይ ይወረውርበት ስለ ነበር በመጨረሻ እርሻዎቹ ሁሉ በድንጋይ ተሸፈኑ፤ ምንጮቻቸውን ደፈኑ፤ የፍራፍሬ ዛፎቻቸውንም ሁሉ ቆረጡ፤ በመጨረሻም የአገሪቱ ዋና ከተማ የነበረችው ቂርሔሬስ ብቻ ቀረች፤ እርሷንም ድንጋይ የሚያወነጭፉ ጦረኞች ከበው አደጋ ጣሉባት።

26 የሞዓብ ንጉሥ ድል እንደ ተመታ ባረጋገጠ ጊዜ ሰይፍ የታጠቁ ሰባት መቶ ሰዎችን አስከትሎ የጠላት ጦር የተሰለፈበትን መስመር ጥሶ ለማምለጥና ወደ ሶርያ ንጉሥ ለመሄድ ቢሞክርም ከቶ አልተሳካለትም።

27 ስለዚህም በእርሱ ምትክ መንገሥ የሚገባውን የመጀመሪያ ልጁን በከተማይቱ ግንብ ላይ ለሞዓብ አምላክ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ እስራኤላውያንም በነገሩ ስለ ተሠቀቁ ከተማይቱን ለቀው ወደ አገራቸው ተመለሱ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች