Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

2 ነገሥት 19 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ንጉሥ ሕዝቅያስ የነቢዩን የኢሳይያስን ምክር መጠየቁ
( ኢሳ. 37፥1-7 )

1 ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ በኀዘን ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደ፤

2 ወዲያውም የቤተ መንግሥቱ ኃላፊ የሆነውን ኤልያቄምን፥ የቤተ መንግሥቱን ጸሐፊ ሼብናንና ሽማግሌዎች ካህናትን ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ላከ፤ እነርሱም ራሳቸው ማቅ ለብሰው ነበር፤

3 ለኢሳይያስም እንዲነግሩት የላከው መልእክት ከዚህ የሚከተለው ነው፦ “ዛሬ የታላቅ መከራ ቀን ነው፤ የሚያሳፍር ቅጣትና ውርደት እየደረሰብን ነው፤ የምትወልድበት ጊዜ ደርሶ ለማማጥ አቅም እንዳነሣት ሴት ሆነናል፤

4 የአሦር ንጉሠ ነገሥት ሕያው እግዚአብሔርን እንዲሰድብለት ከፍተኛ ባለሥልጣኑን ልኮአል፤ አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ስድብ ሰምቶ ተሳዳቢውን ይቀጣ ይሆናል፤ ስለዚህ ከሕዝባችን መካከል በሕይወት ለተረፉት ሰዎች እባክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ።”

5 የንጉሥ ሕዝቅያስ መልእክተኞች ወደ ኢሳይያስ በመጡ ጊዜ፥

6 ኢሳይያስ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብላችሁ ለጌታችሁ ንገሩት አላቸው፤ ‘የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች ሲሰድቡኝ ስለ ሰማችሁት ቃል አትፍሩአቸው።

7 እነሆ፥ እኔ የሽብር ወሬ የሚያሰማ መንፈስ እልክበታለሁ፤ ስለዚህም ወደ አገሩ ተመልሶ እንዲሄድና እዚያም በገዛ ምድሩ በሰይፍ ተመትቶ እንዲሞት አደርጋለሁ።’”


አሦራውያን ሌላ የዛቻ መልእክት መላካቸው
( ኢሳ. 37፥8-20 )

8 የአሦር የጦር አዛዥ፥ የአሦር ንጉሥ ከሰፈሩ ከላኪሽ ተነሥቶ ሊብናን ሊያጠቃ እንደ ሄደ በመስማቱ እርሱም ወደዚያው ሄደ።

9 በኢትዮጵያ ንጉሥ በቲርሃቃ የሚመራ የግብጽ ሠራዊት እነርሱን ለመውጋት በመገሥገሥ ላይ መሆኑን አሦራውያን ሰሙ፤ ወዲያውኑ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ወደ ሕዝቅያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ በመልእክተኞች እጅ ላከ፦

10 “የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሆይ፥ የምትታመንበት አምላክ ‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሠ ነገሥት እጅ አትወድቅም’ ብሎ አያታልህ፤

11 የአሦር ነገሥታት አገሮችን ሁሉ እንዴት ፈጽመው እንደ ደመሰሱ ሰምተሃል፤ አንተስ የምታመልጥ ይመስልሃልን?

12 የቀድሞ አባቶቼ የጎዛንን፥ የካራንና የሬጼፍን ከተሞች አጥፍተዋል፤ በተላሳር የሚኖሩትን የዔዳንን ሕዝብ ገድለዋል፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ከአማልክታቸው አንድ እንኳ ሊያድናቸው ችሎአልን?

13 ለመሆኑ የሐማት፥ የአርፋድ፥ የሰፋርዋይም፥ የሄናዕና የዒዋ ከተሞች ነገሥታት የት አሉ?”

14 ንጉሥ ሕዝቅያስ ደብዳቤውን ከመልክተኞች ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ ቤተ መቅደስም ወስዶ ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው፤

15 እንዲህ ሲል ጸለየ፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ኪሩቤል ተብለው በሚጠሩ መላእክት ላይ የተቀመጥህ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ የዓለምንም መንግሥታት የምትመራ አንተ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን የፈጠርህ አንተ ነህ፤

16 አሁንም እግዚአብሔር ሆይ፤ የደረሰብንን ነገር ሁሉ ተመልከት፥ ሕያው አምላክን አንተን በመስደብ ሰናክሬም የተናገረውን የዛቻ ቃል ሁሉ አድምጥ፤

17 እግዚአብሔር ሆይ፥ የአሦር ነገሥታት ብዙ ሕዝቦችና ምድራቸውን መደምሰሳቸው እርግጥ ነው።

18 ከእንጨትና ከድንጋይ ተጠርበው የተሠሩ የሰው እጅ ሥራ እንጂ አማልክት ስላልነበሩ በእሳት ላይ ጥለው አጠፉአቸው።

19 እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ አንተ ብቻ አምላክ መሆንህን የዓለም መንግሥታት ሁሉ ያውቁ ዘንድ አሁን ከአሦር ንጉሥ በመታደግ አድነን።”


ኢሳይያስ ወደ ንጉሡ ያስተላለፈው መልእክት
( ኢሳ. 37፥21-38 )

20 ከዚህ በኋላ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ አሦር ንጉሠ ነገሥት ስለ ሰናክሬም ዛቻ ያቀረብከውን ጸሎት ሰምቻለሁ፤

21 ስለ እርሱ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ የጽዮን ድንግል ትንቅሃለች፤ ታፌዝብሃለች፤ አንተ እየሸሸህ ሳለህ፥ የኢየሩሳሌም ልጃገረዶች ከኋላህ ሆነው ራሳቸውን ይነቀንቁብሃል።

22 የሰደብከውና የተዳፈርከው ማንን ነው? ድምፅህንስ ከፍ ያደረግኸው በማን ላይ ነው? በትዕቢትስ ዐይንህን ያነሣኸው በማን ላይ ነው? በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ላይ ነው።

23 በመልክተኞችህ አማካይነት፥ በእግዚአብሔር ላይ ስድብህን ከምረሃል፤’ ‘በሠረገሎቼ ከፍተኛ ወደ ሆኑት ተራራዎች፤ ወደ ሊባኖስ ጫፍ ወጥቼአለሁ፤ ረጃጅሞቹን የሊባኖስ ዛፎችዋንና ምርጦች ዝግባ ቆርጬአለሁ፤ ወደ ዳርቻዋና ውብ ወደ ሆነው ጫካዋ ደርሼአለሁ፤’ ብለሃል።

24 ‘በባዕድ አገር ጉድጓድ ቆፍሬ፥ ውሃ ጠጣሁ፤ በእግሬ ኮቴዎች የግብጽን ወንዞች አድርቄአለሁ’ ብለህ ታብየሃል።

25 ሰናክሬም ሆይ! አስተውል፤ ጥንቱኑ እኔ እንደ ወሰንኩት፥ በቀድሞ ዘመን እንደ ዐቀድኩትና አሁን በሥራ ላይ ባዋልኩት መሠረት የተጠናከሩ ከተሞችን ወደ ፍርስራሽ ክምርነት እንድትለውጥ ያደረግኹህ እኔ መሆኔን አልሰማህምን?

26 የእነዚያ አገር ነዋሪዎች ኃይላቸው ተዳክሞ፥ ተስፋ በመቁረጥ እንዳያፍሩ ተደርገው በምሥራቅ ነፋስ እንደ ተመቱ፥ የመስክ አትክልቶች፥ እንደ ቀጨጩ አረንጓዴ ቡቃያዎች፥ በጣራ ላይ እንደ በቀለ ሣር ናቸው።

27 እኔ ግን መነሣትህንና መቀመጥህን፥ መውጣትህንና መግባትህን፥ እንዲሁም እኔን መቃወምህን ዐውቃለሁ።

28 በእኔ ላይ ያለው ተቃውሞህና ትዕቢትህ ወደ ጆሮዬ ደርሶአል፤ በአፍንጫህ ስናጋ፥ በአፍህ ልጓም አድርጌ፥ በመጣህበት መንገድ እመልስሃለሁ።”

29 ከዚህ በኋላ ኢሳይያስ ንጉሥ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፤ “ይህ ሁሉ እንደሚፈጸም ምልክቱ ይህ ነው፥ በአሁኑና በሚቀጥለው ዓመት ሳይዘሩት የሚበቅለውንና የገቦውን እህል ትበላላችሁ፤ በሦስተኛው ዓመት ግን የራሳችሁን እህል ዘርታችሁ ታመርታላችሁ፤ ወይንም ተክላችሁ ፍሬውን ትበላላችሁ፤

30 በይሁዳ ከጥፋት የተረፉት ሁሉ ወደ መሬት ሥር ሰድዶ እንደሚያድግና እንደሚያፈራ ተክል ይሆናሉ፤

31 ከኢየሩሳሌምና ከጽዮን ተራራ የተረፉት ወገኖች ይወጣሉ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን ከመፈጸም አይመለስም።”

32 እግዚአብሔር ስለ አሦራውያን ንጉሠ ነገሥት የተናገረውም ቃል ይህ ነው፦ “ሰናክሬም ወደዚህች ከተማ ፈጽሞ አይገባባትም፤ አንድ ፍላጻ እንኳ አይወረውርባትም፤ ጋሻ ያነገበ ወታደርም ወደ እርሷ አይቀርብም፤ በዐፈር ቁልልም አትከበብም።

33 እርሱ ወደዚህች ከተማ ሳይገባ በመጣበት መንገድ ተመልሶ ይሄዳል፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤

34 ስለ ራሴ ክብር እንዲሁም ለአገልጋዬ ለዳዊት ስለ ሰጠሁት የተስፋ ቃል ይህችን ከተማ እኔ ራሴ ተከላክዬ አድናታለሁ።”

35 በዚያው ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወደ አሦራውያን ሰፈር አልፎ አንድ መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ወታደሮችን ገደለ፤ በማግስቱ በማለዳ ሰዎች በሚነቁበት ጊዜ ሁሉም ሞተው ተገኙ።

36 ከዚህ በኋላ የአሦራውያን ንጉሠ ነገሥት ሰናክሬም ወደ ኋላው በማፈግፈግ ወደ ነነዌ ተመለሰ።

37 ከዕለታት በአንዱ ቀን ኒስሮክ በሚል ስም በሚጠራው ባዕድ አምላኩ ቤተ መቅደስ ውስጥ በስግደት ላይ እንዳለ፥ ከልጆቹ ሁለቱ በተለይ አድራሜሌክና ሣሬጼር ተብለው የሚጠሩት በሰይፍ ገደሉት፤ እነርሱም ወደ አራራት አምልጠው ሄዱ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ከልጆቹ አንዱ አስራዶ የተባለው ነገሠ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች