2 ነገሥት 17 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የእስራኤል ንጉሥ ሆሴዕ 1 አካዝ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፤ 2 እርሱም ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ ይሁን እንጂ የእርሱ በደል ከእርሱ በፊት የነበሩት የእስራኤል ነገሥታት የፈጸሙትን ያኽል አልነበረም፤ 3 የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር ጦርነት በገጠመው ጊዜ ተሸንፎ እጁን በመስጠት በየዓመቱ ይገብርለት ጀመረ። 4 ነገር ግን ከጥቂት ዓመቶች በኋላ ንጉሥ ሆሴዕ፥ ሶእ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ግብጽ ንጉሥ መልእክተኞች በመላክ ይረዳው ዘንድ ጠየቀ፤ በየዓመቱ ለአሦር ንጉሥ ይሰጠው የነበረውንም ግብር አቆመ፤ ሰልምናሶር ይህን በሰማ ጊዜ ሆሴዕን አስይዞ ወህኒ ቤት አስገባው። የሰማርያ መውደቅ 5 ከዚህ በኋላ ሰልምናሶር አገሪቱን ወረረና ሰማርያን ለሦስት ዓመት ከበባት፤ 6 ይኸውም ሆሴዕ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ሰልምናሶር ድል አድርጎ ሰማርያን ያዘ፤ እስራኤላውያንንም ማርኮ በእስረኛነት ወደ አሦር ወሰዳቸው፤ ከእነርሱም ጥቂቶቹ በሐላሕ ከተማ፥ ጥቂቶቹ በጎዛን አውራጃ ውስጥ በሚገኘው በሐቦር ወንዝ አጠገብ፥ እንዲሁም ሌሎቹ በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ። 7 ይህም የሆነበት ምክንያት እስራኤላውያን በሠሩት ኃጢአት ከግብጽ ንጉሥ እጅ በመታደግ አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር የመራቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን በማሳዘናቸው ነበር፤ ይኸውም ለባዕዳን አማልክት ሰገዱ፤ 8 ሕዝቡ ወደ ፊት እየገፋ በመጣ ጊዜ ከፊታቸው ነቃቅሎ ያጠፋላቸውን የአሕዛብን መጥፎ ልማድ ተከተሉ፤ እንዲሁም የእስራኤል ነገሥታት ያሠራጩትን መጥፎ ልማድ ተቀባዮች ሆኑ። 9 እስራኤላውያን አምላካቸው እግዚአብሔር የሚጠላውን ነገር ሁሉ አደረጉ፤ ከዘብ ጠባቂዎች ማማ አንሥቶ እስከ ትልቅ ከተማ ድረስ በገጠር ከተሞቻቸው ሁሉ በየኰረብታዎቹ የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሠሩ፤ 10 በኰረብቶች ሁሉ ላይና በየዛፉ ጥላ ሥር የድንጋይ ዐምዶችንና አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስሎች አቆሙ፤ 11 እግዚአብሔር ከምድሪቱ ነቃቅሎ ያስወጣቸውን የአረማውያንን ሕዝብ ልማድ በመከተል በአሕዛብ መሠዊያዎች ሁሉ ላይ ዕጣን አጠኑ፤ በዚህም ክፉ ሥራቸው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሡ፤ 12 እግዚአብሔር ለጣዖት እንዳይሰግዱ ያዘዛቸውንም ሕግ ሁሉ አፈረሱ። 13 እግዚአብሔርም እስራኤልንና ይሁዳን የሚያስጠነቅቁ መልእክተኞችንና ነቢያትን በመላክ “ከክፉ መንገዳችሁ ሁሉ ተመለሱ፤ አገልጋዮቼ በሆኑት ነቢያትና ባለ ራእዮች አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻችሁና ለእናንተም በሰጠሁት ሕጎችና ትእዛዞች የተጻፈውን ሥርዓቴን ጠብቁ” ብሎ ነግሮአቸው ነበር። 14 እነርሱ ግን መታዘዝ አልፈለጉም፤ በአምላካቸው በእግዚአብሔር እንዳልታመኑ እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው እልኸኞች ሆኑ፤ 15 የሰጣቸውንም ድንጋጌ አልተቀበሉም፤ ከቀድሞ አባቶቻቸው ጋር የገባውንም ቃል ኪዳን አልጠበቁም፤ የሰጣቸውንም ማስጠንቀቂያዎች ሁሉ ቸል አሉ፤ ለከንቱ ጣዖቶች በመስገድ ራሳቸውም ከንቱዎች ሆኑ፤ የእነርሱን መጥፎ ምሳሌነት እንዳይወርሱ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትእዛዝ በመሻር በዙሪያቸው የሚኖሩ የአሕዛብን ልማድ ሁሉ ተከተሉ። 16 የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ሁሉ በመጣስ የሚሰግዱላቸውን ከወርቅ የተሠሩ ሁለት ጥጆችን አቆሙ፤ እንዲሁም አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስል ሠሩ፤ ለከዋክብት ሰገዱ፤ በዓል ተብሎ ለሚጠራውም ባዕድ አምላክ አገልጋዮች ሆኑ። 17 ለእነዚያም አሕዛብ አማልክት ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ፤ ከሙታን ጠሪዎችና ከጠንቋዮችም ምክር ጠየቁ፤ እግዚአብሔር ለሚጠላው ክፉ ነገር ሁሉ ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሡ። 18 እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ተቆጥቶ የይሁዳን መንግሥት ብቻ በመተው እስራኤላውያንን ከፊቱ አስወገደ። 19 ነገር ግን የይሁዳ ሰዎችም ቢሆኑ፥ አምላካቸው እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትእዛዞች አልጠበቁም ነበር፤ እነርሱም የእስራኤል ሕዝብ የተቀበሉትን ልማድ ተከታዮች ነበሩ። 20 እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ሁሉ ተዋቸው፤ ከፊቱም እስኪወገዱ ድረስ በዝባዦች ለሆኑት ጠላቶቻቸው አሳልፎ በመስጠት ቀጣቸው። 21 እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከይሁዳ ከለየ በኋላ እስራኤላውያን የናባጥን ልጅ ኢዮርብዓምን መርጠው አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እግዚአብሔርን እንዲተው በማድረግ አሠቃቂ ወደ ሆነ ኃጢአት መራቸው፤ 22 እስራኤላውያንም በኢዮርብዓም ኀጢአት ሁሉ ጸኑ፤ ከዚያም አልተመለሱም። 23 ጌታ በባርያዎቹ በነቢያት ሁሉ አማካይነት ባስጠነቀቃቸው መሠረት፥ ከፊቱ እስኪያስወግዳቸው ድረስ በዚያው ቀጠሉበት፤ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ከሀገሩ ተማርኮ ወደ አሦር ተወሰደ፤ አሁንም በዚያው ይገኛል። አሦራውያን በእስራኤል ምድር እንዲሰፍሩ መደረጉ 24 የአሦር ንጉሠ ነገሥት በባቢሎን፥ ኩታ፥ ዓዋ፥ ሐማትና ሰፋርዋይም ተብለው በሚጠሩት ከተሞች ይኖሩ የነበሩትን አሕዛብ አምጥቶ ተሰደው በሄዱት በእስራኤላውያን እግር በመተካት በሰማርያ ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ፤ እነርሱም እነዚህን ከተሞች ወርሰው በዚያ መኖር ጀመሩ። 25 እነርሱም በዚያ ሰፍረው መኖር እንደ ጀመሩ እግዚአብሔርን አላመለኩትም ነበር። ስለዚህም እግዚአብሔር አንበሶችን በመላክ ከእነርሱ ጥቂቶቹን ሰባብረው እንዲገድሉ አደረገ፤ 26 ለአሦርም ንጉሠ ነገሥት “በሰማርያ ከተሞች ሰፍረው እንዲኖሩ ያደረግሃቸው ሕዝቦች የዚያችን አገር አምላክ ሕግ የሚያውቁ ሆነው አልተገኙም፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሰባብሮ የሚገድሉ አንበሶችን ላከባቸው” የሚል ወሬ ደረሰው። 27 ስለዚህም ንጉሠ ነገሥቱ “ማርከን ካመጣናቸው ካህናት አንዱን ወደዚያ ላኩ፤ ወደዚያም ተመልሶ በመሄድ የዚያችን አገር አምላክ ያዘዘውን ሕግ ለሕዝቡ እንዲያስተምራቸው አድርጉ” ሲል አዘዘ። 28 ስለዚህም ከሰማርያ ተማርኮ የተወሰደ አንድ እስራኤላዊ ካህን ተመልሶ በመሄድ በቤትኤል ተቀመጠ፤ በዚያም ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንደሚገባው አስተማረው። 29 በሰማርያ የሰፈሩት ሕዝቦች ግን የየራሳቸውን ጣዖት መሥራት ቀጥለው እስራኤላውያን ባሠሩአቸው በከፍተኛ ማምለኪያ ቦታዎች አኖሩአቸው፤ እያንዳንዱ ቡድን በሚኖርበት ከተማ ሁሉ የየራሱን ጣዖት አቆመ። 30 በዚህም ዓይነት የባቢሎን ሰዎች ሱኮትበኖት በተባለው አምላክ ስም ጣዖት ሠሩ፤ እንዲሁም የኩታ ሰዎች ኔርጋል ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም፥ ጣዖት ሠሩ፤ የሐማት ሕዝብ ኢሺማ ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም፤ ጣዖት ሠሩ፤ 31 የዓዋ ሕዝብ ኒብሐዝና ታርታቅ ተብለው በሚጠሩ አማልክታቸው ስም ጣዖቶቻቸውን ሠሩ፤ የሰፋርዋይምም ሕዝብ አድራሜሌክና ዓናሜሌክ ተብለው ለሚጠሩ አማልክቶቻቸው ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። 32 እነዚሁ ሰዎች በተጨማሪ ለእውነተኛው አምላክ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ነበር። ከእያንዳንዳቸውም ቡድን በአረማውያን የማምለኪያ ስፍራዎች የሚያገለግሉና መሥዋዕት የሚያቀርቡላቸውን ካህናት መረጡ፤ 33 በዚህም ዓይነት እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመሩ፤ በሌላ በኩል ግን ቀድሞ ይኖሩባቸው በነበሩት ሕዝቦች ይፈጽሙት በነበረው ልማድ መሠረት ለባዕዳን አማልክታቸው ይሰግዱ ነበር። 34 ይህንኑ አሮጌ ልማዳቸውን እስከ አሁን ድረስ በመፈጸም ላይ ናቸው፤ እነርሱ እግዚአብሔርን አያመልኩም፤ ወይም ስሙ እስራኤል ተብሎ ለተጠራው ለያዕቆብ ልጆች እግዚአብሔር በሰጣቸው ደንቦች፥ ሥርዓቶች፥ ሕጎችና ትእዛዞች ጸንተው አልኖሩም። 35 እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዞአቸው ነበር፤ “ባዕዳን አማልክትን አታምልኩ፤ ለእነርሱም አገልጋዮች በመሆን አትስገዱላቸው፤ መሥዋዕትንም አታቅርቡላቸው፤ 36 በታላቅ ኃይልና በሥልጣን ከግብጽ ምድር ላወጣኋችሁ ለእኔ ለእግዚአብሔር ታዛዦች ሁኑ፤ መስገድና መሥዋዕት ማቅረብ የሚገባችሁ ለእኔ ብቻ ነው፤ 37 ጽፌ የሰጠኋችሁንም ድንጋጌና ሥርዓቱን፥ ሕጎችና ትእዛዞቹን ሁልጊዜ ጠብቁ፤ ባዕዳን አማልክትንም አትከተሉ፤ 38 እኔ ከእናንተ ጋር የገባሁትንም ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ባዕዳን አማልክትንም አታምልኩ፤ 39 እኔን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እኔም ከጠላቶቻችሁ እጅ በመታደግ አድናችኋለሁ።” 40 ነገር ግን እነዚያ አሕዛብ ይህን መስማት ትተው አሮጌ ልማዳቸውን ተከተሉ። 41 እነዚያ ሕዝቦች በዚሁ ዓይነት እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመሩ፤ በሌላ በኩል ግን ለጣዖቶቻቸው ይሰግዱ ነበር፤ ዘሮቻቸውም እስከ ዛሬ ድረስ ይህንኑ ዓይነት አምልኮ እንደ ቀጠሉ ናቸው። |