2 ነገሥት 16 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የይሁዳ ንጉሥ አካዝ ( 2ዜ.መ. 28፥1-27 ) 1 የረማልያ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአታም ልጅ አካዝ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 2 በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሀያ ዓመት ነበር፤ እርሱም መኖሪያውን በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ እርሱም የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም አርአያነት አልተከተለም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ አምላኩን እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኝ ሥራ ሠራ፤ 3 የእስራኤልንም ነገሥታት መጥፎ አርአያነት ተከተለ፤ የገዛ ልጁን እንኳ ሳይቀር ለጣዖቶች የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ ይህንንም የፈጸመው የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ አገር ለመግባት ወደ ፊት እየገፉ በመጡ ጊዜ እግዚአብሔር ከዚያች ምድር ነቃቅሎ ያስወገዳቸው አሕዛብ ይሠሩት የነበረውን አጸያፊ ድርጊት በመከተል ነው። 4 አካዝ በየኰረብቶች ላይ በተሠሩት የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችና በእያንዳንዱም ዛፍ ሥር መሥዋዕት በማቅረብ ዕጣን አጠነ። 5 የሶርያ ንጉሥ ረጺንና የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ በመጣል ከበቡአት፤ ነገር ግን አካዝን ድል ሊያደርጉት አልቻሉም። 6 በዚያኑ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ረጺን የኤላትን ከተማ አስመልሶ በቁጥጥሩ ሥር በማድረግ በዚያ የነበሩትን አይሁድ አስወጣ፤ ያንጊዜ በኤላት የሰፈሩት ኤዶማውያን እስከ አሁን በዚያ ይገኛሉ። 7 ከዚህም የተነሣ ንጉሥ አካዝ ወደ አሦር ንጉሠ ነገሥት ወደ ቲግላት ፐሌሴር “እኔ ለአንተ ታማኝ አገልጋይህ ነኝ፤ ስለዚህም ወደ እኔ መጥተህ አደጋ ከጣሉብኝ ከሶርያና ከእስራኤል ነገሥታት እጅ አድነኝ” የሚል ጥያቄ የያዙ መልእክተኞች ላከ። 8 ከዚህም በቀር አካዝ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ዕቃ ግምጃ ቤት ሰብስቦ ለዚሁ ለአሦር ንጉሥ ገጸ በረከት በማድረግ ላከለት። 9 የአካዝን ጥያቄ በመቀበል ቲግላት ፐሌሴር ዘምቶ ደማስቆን በቁጥጥሩ ሥር አደረገ፤ ንጉሥ ረጺንንም ገደለ፤ ሕዝቡንም ማርኮ ቂር ተብላ ወደምትጠራው ስፍራ ወሰደው። 10 ንጉሥ አካዝ ወደ ደማስቆ ሄዶ ከንጉሠ ነገሥት ቲግላት ፐሌሴር ጋር በተገናኘ ጊዜ በዚያ አንድ መሠዊያ አየ፤ ያንን መሠዊያ በተመሳሳይ ሁኔታ መሥራት የሚያስችለውን ቅርጽ አዘጋጅቶ ለካህኑ ለኡሪያ ላከለት፤ 11 ስለዚህም ኡሪያ ንጉሥ አካዝ ተመልሶ ከመምጣቱ በፊት ልክ ያንኑ የሚመስል መሠዊያ ሠራ፤ 12 አካዝም ከደማስቆ በተመለሰ ጊዜ ያ መሠዊያ በትክክል መሠራቱን ለማየትና መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ መሠዊያው ወጣ፤ 13 እንዲሁም በዚያ መሠዊያ ላይ የሚቃጠል የእንስሶች መሥዋዕትና የእህል መባ አቀረበ፤ የመባውን ወይን ጠጅና የኅብረት መሥዋዕት ደም አፈሰሰበት። 14 ከነሐስ ተሠርቶ ለእግዚአብሔር የተለየውም መሠዊያ በዚያ አዲስ መሠዊያና በቤተ መቅደሱ መካከል ነበር፤ አካዝም ያንን መሠዊያ አስነሥቶ እርሱ ባሠራው በአዲሱ መሠዊያ በስተ ሰሜን በኩል አኖረው፤ 15 ከዚህ በኋላ ኡሪያን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “ይህን የእኔን ታላቅ መሠዊያ ማለዳ ለሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት፥ በምሽት ለሚቀርበውም የእህል መባ ስለ ንጉሡና ስለ ሕዝቡ የሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል መባ የሚቀርብበትና የሕዝቡ የወይን ጠጅ መባ የሚፈስበት እንዲሆን አድርግ፤ የሚሠውትንም የእንስሶች ደም ሁሉ በእርሱ ላይ አፍስስ፤ ከነሐስ የተሠራው መሠዊያ ግን እኔ ራሴ የምፈልገውን ነገር የምጠይቅበት እንዲሆን አድርግ።” 16 ኡሪያም ንጉሡ እንዳዘዘው አደረገ። 17 ንጉሥ አካዝ በቤተ መቅደስ ውስጥ መገልገያ የነበሩትን ከነሐስ የተሠሩ መንኰራኲሮች ቆርጦ ልሙጥ የሆነውን ነገር ከጐናቸው ወሰደ። በእነርሱ ላይ የነበሩትንም የመታጠቢያ ሳሕኖች ወሰደ፤ ከነሐስ የተሠራውን የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ከታች በኩል ተሸክመውት ከነበሩት ከነሐስ ከተሠሩት ከዐሥራ ሁለት የበሬ ቅርጾች ጀርባ ላይ አንሥቶ፥ ከድንጋይ በተሠራ መሠረት ላይ አኖረው። 18 አካዝ የአሦርን ንጉሠ ነገሥት ለማስደሰት ሲል ንጉሣዊ ዙፋን የሚዘረጋበትን ሉዓላዊ ስፍራ አስወገደ፤ ከዚያ በፊት የነበረ ማንኛውም ንጉሥ ወደ ቤተ መቅደስ ይገባበት የነበረውንም ልዩ በር ዘጋ። 19 ንጉሥ አካዝ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ 20 አካዝ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ሕዝቅያስ ነገሠ። |