2 ነገሥት 15 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያ ( 2ዜ.መ. 26፥1-23 ) 1 ዳግማዊ ኢዮርብዓም በእስራኤል በነገሠ በሀያ ሰባተኛው ዓመት የአሜስያስ ልጅ ዖዝያ በይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 2 እርሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኃምሳ ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ይኮልያ ተብላ የምትጠራ የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች። 3 እርሱም የአባቱን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፤ 4 ነገር ግን በየኰረብቶች ላይ የነበሩትን የአሕዛብን የማምለኪያ ቦታዎች አልደመሰሰም፤ ስለዚህም ሕዝቡ በየኰረብቶች ላይ መሥዋዕት ማቅረባቸውንና ዕጣን ማጠናቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር፤ 5 በኋላም እግዚአብሔር በዖዝያ ላይ የቆዳ በሽታ አሳደረበት፤ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ይህ በሽታ ስላልለቀቀው ከሥራው ሁሉ ተገልሎ በተለየ ቤት ውስጥ ለብቻው ይኖር ነበር፤ በዚህም ጊዜ መንግሥቱን ሲመራ የቆየው ልጁ ኢዮአታም ነበር። 6 ንጉሥ ዖዝያ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። 7 ዖዝያ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በቀድሞ አባቶቹ መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮአታም ነገሠ። የእስራኤል ንጉሥ ዘካርያስ 8 ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የዳግማዊ ኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በእስራኤል ነገሠ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ስድስት ወር ገዛ፤ 9 እርሱም ከእርሱ በፊት እንደነበሩት ነገሥታት ሁሉ ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ እንዲሁም እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት ተከተለ፤ 10 ሻሉም ተብሎ የሚጠራው የያቤሽ ልጅ ሤራ በማድረግ ዪብለዓም ተብላ በምትጠራው ስፍራ ንጉሥ ዘካርያስን ገድሎ በእርሱ እግር ነገሠ። 11 ንጉሥ ዘካርያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 12 በዚህም ዓይነት እግዚአብሔር ለንጉሥ ኢዩ “ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ በእስራኤል ይነግሣሉ” ሲል የተናገረው የተስፋ ቃል ተፈጸመ። የእስራኤል ንጉሥ ሻሉም 13 ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የያቤሽ ልጅ ሻሉም የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ አንድ ወር ብቻ ገዛ። 14 ምናሔም ተብሎ የሚጠራው የጋዲ ልጅ ከቲርጻ ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ ሻሉምንም ገድሎ በእርሱ እግር ነገሠ። 15 ሻሉም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ እንዲሁም እርሱ የጠነሰሰው ሤራ ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 16 ምናሔም ከቲርጻ ተነሥቶ በሚያልፍበት ጊዜ እግረ መንገዱን የቲፍሳሕን ከተማ፥ ነዋሪዎችዋንና በዙሪያዋ የነበረውን ግዛት ሁሉ ደመሰሰ፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት የከተማይቱ ነዋሪዎች ለእርሱ እጃቸውን ለመስጠት ባለመፍቀዳቸው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ነፍሰ ጡሮችን እንኳ ሳይምር ሆዳቸውን ቀደደ። የእስራኤል ንጉሥ ምናሔም 17 ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ነገሠ፤ መኖሪያውን በሰማርያ አድርጎ ዐሥር ዓመት ገዛ። 18 እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱም እግዚአብሔርን አሳዘነ። 19 የአሦር ንጉሠ ነገሥት ቲግላት ፐሌሴር እስራኤልን ወረረ፤ ምናሔም በአገሩ መንግሥት ላይ ሥልጣኑን እንዲያጸናለትና እንዲደግፈው ለመማጠን ሠላሳ አራት ሺህ ኪሎ የሚመዝን ብር እጅ መንሻ አድርጎ ለቲግላት ፐሌሴር ሰጠው። 20 ምናሔም ገንዘቡን የሰበሰበው የእስራኤል ከበርቴዎች እያንዳንዳቸው ኀምሳ ጥሬ ብር አዋጥተው እንዲሰጡ በማስገደድ ነበር። በዚህም ዓይነት ቲግላት ፐሌሴር በሰላም ወደ አገሩ ተመልሶ ሄደ። 21 ምናሔም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 22 ምናሔም ሞተ፤ ተቀበረም፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ፈቃሕያ ነገሠ። የእስራኤል ንጉሥ ፈቃሕያ 23 ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በኀምሳኛው ዓመት የምናሔም ልጅ ፈቃሕያ በእስራኤል ነገሠ፤ መኖርያውንም በሰማርያ አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ፤ 24 እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት ስለ ሠራ እግዚአብሔርን አሳዘነ። 25 ከፈቃሕያ ሠራዊት መካከል ፈቁሔ ተብሎ የሚጠራ የረማልያ ልጅ የሆነ አንድ የጦር መኰንን ከኀምሳ የገለዓድ ሰዎች ጋር ሆኖ ሤራ ጠነሰሰ፤ በሰማርያ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በሚገኘው ምሽግ ውስጥ ዘልቆ በመግባትም ፈቃሕያን ከአርጎብና ከሃርዬ ጋር ገድሎ በፈቃሕያ እግር ተተክቶ ነገሠ። 26 ፈቃሕያ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። የእስራኤል ንጉሥ ፈቁሔ 27 ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በኃምሳ ሁለተኛው ዓመት የረማልያ ልጅ ፈቁሔ በእስራኤል ነገሠ፤ መኖርያውንም በሰማርያ አድርጎ ሀያ ዓመት ገዛ። 28 እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ ንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነትን በመከተል ኃጢአት ስለ ሠራ እግዚአብሔርን አሳዘነ። 29 የአሦር ንጉሠ ነገሥት ቲግላት ፐሌሴር ዒዮን፥ አቤልቤትማዕካ፥ ያኖሐ፥ ቄዴሽና ሐጾር ተብለው የሚጠሩትን ከተሞች፥ እንዲሁም የገለዓድን፥ የገሊላንና የንፍታሌምን ግዛቶች በመውረር ሕዝቡን ወደ አሦር ማርኮ የወሰደውም ይኸው ፋቁሔ በነገሠበት ዘመን ነበር። 30 የዖዝያ ልጅ ኢዮአታም በይሁዳ በነገሠ በሀያኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በንጉሥ ፋቁሔ ላይ ሤራ ጠነሰሰ፤ እርሱንም ገድሎ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ 31 ፈቁሔ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአታም ( 2ዜ.መ. 27፥1-9 ) 32 የረማልያ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የዖዝያ ልጅ ኢዮአታም የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 33 በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሀያ አምስት ዓመት ነበር፤ መኖርያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም የሩሻ ተብላ የምትጠራ የጻዶቅ ልጅ ነበረች። 34 የአባቱንም የዖዝያን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፤ 35 ነገር ግን በየኰረብቶች ላይ የነበሩትን የአሕዛብ መሠዊያዎችን አላስወገደም፤ ሕዝቡም መሥዋዕት ማቅረባቸውንና ዕጣን ማጠናቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር፤ የቤተ መቅደሱን ሰሜናዊ ቅጽር በር ያሠራ ይኸው ኢዮአታም ነበር። 36 ኢዮአታም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 37 እግዚአብሔር በመጀመሪያ የሶርያ ንጉሥ ረጺንና፥ የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ በይሁዳ ላይ አደጋ እንዲጥሉባት የላካቸው ይኸው ኢዮአታም በይሁዳ በነገሠበት ዘመን ነበር፤ 38 ኢዮአታም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አካዝ ነገሠ። |