2 ቆሮንቶስ 9 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)በኢየሩሳሌም ለሚገኙ ክርስቲያኖች የተደረገ መዋጮ 1 ለቅዱሳን ስለሚደረገው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግም። 2 በጎ ፈቃዳችሁን ስለማውቅ፤ በእናንተ ላይ የምመካበትን ምክንያት ለመቄዶንያ ሰዎች፥ “አካይያ ከአምና ጀምሮ ተዘጋጅቶአል፤” ብዬ ተናግሬለሁ፤ ቅንዐታችሁም ብዙዎችን አነሣሥቶአል። 3 ነገር ግን ለእነርሱ እንደተናገርኩት፥ ስለ እናንተ ያለን ትምክህት እንዲሁ በባዶ እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ወንድሞችን እልካለሁ፤ 4 ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ቢመጡና ሳትዘጋጁ ቢያገኟችሁ፥ ያን ያህል ማለታችን እንድታፍሩ ባይሆንም፥ እንዲህ በመመካታችን ግን እንድናፍር ያደርገናል። 5 እንግዲህ ዝግጁ እንድትሆኑ ወንድሞች አስቀድመው ወደ እናንተ መጥተው፥ አስቀድማችሁ ተስፋ የሰጣችሁትን የልግስና ስጦታ እንደ ግዴታ ሳይሆን በበጎ ፈቃደኝነት ቀደም ብለው እንዲያዘጋጁ፥ እነርሱን መለመን አስፈላጊ መሆኑን አስቤበታለሁ። 6 ይህን አስታውሱ፤ በጥቂት የዘራ ጥቂት ያጭዳል፤ ብዙ የዘራም ብዙ ያጭዳል። 7 እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና፥ እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበው ይስጥ፤ በኀዘን ወይም በግድ ግን አይሁን። 8 ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን አግኝታችሁ በበጎ ሥራ በቸርነት እንድትለግሱ፥ እግዚአብሔር ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። 9 ይህም፥ “በተነ፤ ለድኾችም ሰጠ፤ ጽድቁ ለዘለዓለም ይኖራል፤” ተብሎ ተጽፏል። 10 ለዘሪ ዘርን፥ ለመብላትም እንጀራን የሚሰጥ፥ እርሱ የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል፤ ያበረክትላችሁማል፤ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 11 በእኛ በኩል እግዚአብሔርን የማመስገኛ ምክንያት የሚሆነውን ልግስናችሁ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ያደርጋችኋል። 12 የዚህ አገልግሎት ረድኤት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ብዙ ምስጋና ምክንያትም ነው። 13 በዚህ አገልግሎት ስለ ተፈተናችሁ፥ በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለ ታዘዛችሁ፥ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና፥ እግዚአብሔርን ያከብራሉ፤ 14 እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ታላቅ ጸጋ የተነሣ ስለ እናንተም በሚጸልዩበት ጊዜ ይናፍቁአችኋል። 15 ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን። |