Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

2 ቆሮንቶስ 5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የሰማይ ቤታችን

1 የምንኖርበት ምድራዊ ድንኳን የሆነው ሕይወት ቢፈርስ፥ በሰማይ ዘላለማዊ የሆነ በእጅ ያልተሠራ፥ በእግዚአብሔር የታነጸ መኖሪያ እንዳለን እናውቃለን።

2 በዚህ ድንኳን ውስጥ እንቃትታለን፥ ከሰማይ የሆነ መኖሪያችንን ለመልበስ እንናፍቃለንና፤

3 ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም።

4 በእውነትም የሚሞተው በሕይወት እንዲዋጥ፥ ጨምረን ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለሆነ፥ በዚህ ድንኳን ሳለን ከብዶን እንቃትታለን።

5 ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው፤ እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን።

6 ስለዚህ ሁልጊዜ እንታመናለን፤ በሥጋ እስካለን ድረስ ከጌታ ርቀን እንደምንገኝ ብናውቅም፥

7 የምንኖረው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም።

8 አዎ፥ ታምነናል፤ ይልቁንም ከሥጋ ተለይተን በጌታ ዘንድ መኖር እንመርጣለን።

9 ስለዚህ በማደሪያችን ሆንን ወይም ተለይተን ሄድን፥ እርሱን ደስ የምናሰኝ መሆንን ነው የምንፈልገው።

10 መልካም ሆነ ወይም ክፉ፥ በሥጋችን እንደ ሠራነው ዋጋችንን ለመቀበል፥ ሁላችን በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት እንቆማለን።


የማስታረቅ አገልግሎት

11 እንግዲህ የጌታን ፍርሃት አውቀን፥ ሰዎችን ለማስረዳት እንጥራለን፤ ስለ ራሳችን ከሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ የተገለጥን ነን፤ ለእናንተም ሕሊና የተገለጥን እንደ ሆንን ተስፋ አደርጋለሁ።

12 በልብ ሳይሆን በውጫዊ ነገር ለሚመኩ፥ የምትመልሱላቸው መልስ እንዲኖራችሁ፥ በእኛ ልትመኩ ምክንያት ልንሰጣችሁ እንጂ በእናንተ ፊት መልሰን ራሳችንን ለማመስገን ፈልገን አይደለም።

13 አእምሮችንን የሳትን ብንሆን፥ የሳትነው ለእግዚአብሔር ነው፤ ጤነኞችም ብንሆን ለእናንተ ነው።

14 አንዱ ስለ ሁሉ እንደ ሞተ እርግጠኞች በመሆናችን፥ የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል፤ ይህ በመሆኑም ሁሉ ሞተዋል።

15 በሕይወትም ያሉት፥ ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ፥ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ።

16 ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሰብአዊ አመለካከት እንደምናየው አድርገን አንመለክትም፤ ክርስቶስንም በዚህ መልክ ተመልክተነው የነበርን ብንሆን እንኳን፥ ከእንግዲህ ወዲህ ግን በዚህ መልክ አይደለም የምናውቀው።

17 ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል!

18 ይህ ሁሉ የሆነው፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን፥ የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፤

19 ይህ እግዚአብሔር የሰዎችን በደል ሳይቆጥርባቸው በክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋር አስታርቋል፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኑሯል።

20 ስለዚህ እግዚአብሔር ጥሪውን የሚያቀርበው በእኛ በኩል በመሆኑ፥ እኛ ለክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ስለ ክርስቶስ ሆነን “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ” ብለን እንለምናለን።

21 እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን ስለ እኛ ኃጢአት የሌለበትን እርሱን ኃጢአት አደረገው።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች