Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

2 ቆሮንቶስ 13 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የመጨረሻ ምክርና ሰላምታ

1 ወደ እናንተ ስመጣ ይህ ሦስተኛዬ ነው። “ማንኛውም ነገር በሁለትና በሦስት ምስክር አፍ ይጸናል።”

2 ለሁለተኛ ጊዜ ከእናንተ ጋር በነበርሁ ጊዜ እንደነገርኳችሁ አሁንም ደግሞ በሩቅ ስሆን፥ እንደገና ብመጣ እንዳልራራላቸው አስቀድመው ኃጢአት ለሠሩት ለሌሎችም ሁሉ አስቀድሜ እናገራለሁ፤

3 ይህንንም የምለው ክርስቶስ በእኔ አድሮ እንደሆነ ማስረጃ በመፈለጋችሁ ነው፤ ክርስቶስ ስለ እናንተ አይደክምም፤ ነገር ግን በመካከላችሁ ኀያል ነው።

4 በድካም ተሰቅሎአል፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል በሕይወት ይኖራል። እኛ ደግሞ ከእርሱ ጋር ደካሞች ብንሆን፤ እናንተ ለማገልገል በእግዚአብሔር ኃይል ከእርሱ ጋር በሕይወት እንኖራለን።

5 በእምነት እንደምትኖሩ ለማወቅ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ካልሆናችሁ በቀር፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ አታውቁም ኖሯል?

6 እኛ ግን የማንበቃ እንዳልሆንን እንደምታውቁ ተስፋ አደርጋለሁ።

7 ክፉ ነገርንም ከቶ እንዳታደርጉ ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን፤ እኛ የበቃን ሆነን እንድንታይ አይደለም፤ ነገር ግን እኛ ምንም የማንበቃ እንኳን ብንሆን፥ እናንተ መልካሙን እንድታደርጉ ነው።

8 ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልም።

9 እኛ ስንደክም እናንተም ኀይለኞች ስትበረቱ ደስ ብሎናልና፥ ፍጹማን እንድትሆኑ ደግሞ እንጸልያለን።

10 ከእናንተ ርቄ ሳለሁ እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ ሥልጣኔን በኃይል እንዳልጠቀም ነው፤ ጌታም ይህን ሥልጣን የሰጠኝ እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለም።

11 በቀረውስ ወንድሞች ሆይ! ደኅና ሁኑ። ፍጹማን ሁኑ፤ ምክሬን ስሙ፤ በአንድ ልብ ሁኑ፤ በሰላም ኑሩ፤ የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።

12 በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

13 የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች