Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

1 ጢሞቴዎስ 5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ስለ ምእመናን የተሰጠ ምክር

1 ሽማግሌን እንደ አባት አድርገህ ምከር እንጂ አትገሥጽ፤ እንዲሁም ጎልማሶችን እንደ ወንድሞች፥

2 አሮጊቶችን እንደ እናቶች፥ ወጣት ሴቶችን እንደ እኅቶች አድርገህ በፍጹም ንጽሕና ተመልከት።

3 በእርግጥ ረዳት የሌላቸውን መበለታትን ተንከባከብ።

4 ማንም መበለት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፥ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተሰቦቻቸው የሃይማኖታዊ ግዴታቸውን መፈጸምን ይማሩ፥ ለወላጆቻቸውና ለአያቶቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ የሚያሰኝ ነውና።

5 በእርግጥ መበለት የሆነችና ያለረዳት ለብቻዋ የተተወች፥ ተስፋዋን በእግዚአብሔር ላይ ታደርጋለች፤ ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም ጸንታ ትኖራለች፤

6 ለዚህ ዓለም ደስታ የምትኖር መበለት ግን በሕይወትዋ ሳለች እንኳ የሞተች ናት።

7 ያለ ነቀፋ እንዲሆኑ እነዚህን ነገሮች ደግሞ እዘዝ።

8 ማንም ቢሆን ግን ለገዛ ዘመዶቹ በተለይም ለቤተ ሰቡ አባላት የማያስብ ከሆነ፥ እምነትን የካደና ከማያምን ሰው ይልቅ የባሰ ነው።

9 መበለቲቱ ከስልሳ ዓመት በታች ያልሆነች፤ የአንድም ባል ሚስት የነበረች በመዝገብ ትጻፍ፤

10 እንዲሁም ልጆችን በማሳደግ፥ እንግዶችንም በመቀበል፥ የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፥ የተጨነቁትንም በመርዳት፥ በበጎም ሥራ ሁሉ በመትጋት፥ በመልካም ሥራዎችዋ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል።

11 ወጣት መበለታትን ግን በመዝገብ ላይ አታካትት፤ ሥጋዊ ምኞታቸው ከክርስቶስ ስለሚለያቸው መጋባትን ይፈልጋሉና፤

12 በዚህም በመጀመሪያ የገቡትን ቃል በማፍረሳቸው ምክንያት በራሳቸው ላይ ፍርድን ያመጣሉ፤

13 ከዚህም ጎን ለጎን ቤት ለቤት እየዞሩ ሥራ መፍታትን ይማራሉ፤ ሥራ ፈቶችም ብቻ ሳይሆኑ የማይገባቸውን እየተናገሩ ሰውን የሚያሙና በነገር ጣልቃ የሚገቡ ይሆናሉ።

14 እንግዲህ ወጣት መበለታት እንዲያገቡ፥ ልጆችንም እንዲወልዱ፥ እያንዳንዳቸውም ቤተሰቦቻቸውን እንዲያስተዳድሩ እፈቅዳለሁ፤ በዚህም ተቃዋሚ የሚሳደብበትን ምንም ዓይነት ሰበብ እንዳይሰጡት ነው፤

15 ከአሁን በፊት አንዳንዶች ሰይጣንን ለመከተል መንገድን ስተው ሄደዋልና።

16 አማኝ የሆነች ማንም ሴት መበለታት ዘመዶች ቢኖሩአት፥ እነርሱን ትርዳቸው፤ ቤተክርስትያንም በእርግጥ እርዳታ የሚያሻቸውን መበለታትን መርዳት እንድትችል ሸክም አይሁኑባት።

17 በመልካም የሚያስተዳድሩ፥ በተለይም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙ ሽማግሌዎች፥ እጥፍ ክብር ይገባቸዋል።

18 ቅዱስ መጽሐፍ፦ “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፤” ደግሞ “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል፤” ይላል።

19 በሁለት ወይም በሦስት ምስክር ካልተደገፈ በቀር በሽማግሌ ላይ ክስ አትቀበል።

20 ሌሎቹ ደግሞ እንዲፈሩ፥ ኃጢአት የሚሠሩትን በሁሉ ፊት ገሥጽ።

21 አንዱን ከሌላው በማበላለጥ ምንም ዓይነት ነገር ሳታደርግ፥ ያለ አድልዎ እነዚህን ትዛዛቶች እንድትጠብቅ በእግዚአብሔርና በጌታ በክርስቶስ ኢየሱስ በተመረጡትም መላእክት ፊት አደራ እልሃለሁ።

22 በማንም ላይ ፈጥነህ እጆችህን አትጫን፤ በሌሎችም ኃጢአት አትተባበር፤ ራስህን በንጽህና ጠብቅ።

23 ስለ ሆድህና በተደጋጋሚ ስለሚያጠቃህ በሽታ ስትል ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ፥ ከእንግዲህ ውሃ ብቻ አትጠጣ።

24 የአንዳንድ ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ በመሆኑ አስቀድሞ ፍርድን ያመለክታል፤ የሌሎች ግን የሚገለጠው ዘግየት ብሎ ነው፤

25 እንዲሁ መልካም ሥራ ደግሞ የተገለጠ ነው፤ ያልተገለጠም ከሆነ እንኳ ተሰውሮ መቅረት አይችልም።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች