1 ሳሙኤል 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 የቂርያትይዓሪም ሰዎችም መጥተው የጌታን ታቦት ይዘው ወጡ፤ ከዚያም በኮረብታው ላይ ወዳለው ወደ አሚናዳብ ቤት ወሰዱት። የጌታን ታቦት እንዲጠብቅም ልጁን አልዓዛርን ቀደሱት። ሳሙኤል የእስራኤል መሪ መሆኑ 2 ታቦቱ በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠ ረዥም ጊዜ ሆነው፤ ሃያ ዓመትም ያህል ኖረ። በዚያን ጊዜ የእስራኤል ቤት ሁሉ አዝኖ ጌታን ፈለገ። 3 ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ፥ “በፍጹም ልባችሁ ወደ ጌታ የምትመለሱ ከሆነ፥ ባዕዳን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ራሳችሁንም ለጌታ አሳልፋችሁ ስጡ፤ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ እርሱም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋችኋል።” አላቸው። 4 ስለዚህ እስራኤላውያን የበዓልንና የዐስታሮትን አማልክት አስወግደው፥ ጌታን ብቻ አመለኩ። 5 ከዚያ በኋላ ሳሙኤል፥ “እስራኤልን ሁሉ በምጽጳ ሰብስቡ፤ እኔም ስለ እናንተ ወደ ጌታ እጸልያለሁ” አለ። 6 እስራኤላውያን በምጽጳ በተሰበሰቡ ጊዜ፥ ውሃ ቀድተው በጌታ ፊት አፈሰሱ፤ በዚያች ዕለትም ጾሙ፤ በዚያም “እግዚአብሔርን በድለናል” አሉ። ሳሙኤልም በምጽጳ እስራኤልን ይፈርድ ነበር። 7 ፍልስጥኤማውያንም እስራኤል በምጽጳ መሰብሰባቸውን በሰሙ ጊዜ፥ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ሊወጓቸው ወጡ። እስራኤላውያንም ይህን ሲሰሙ ፍልስጥኤማውያንን ፈሩ። 8 ሳሙኤልንም፥ “አምላካችን ጌታ ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድነን ዘንድ ስለ እኛ ወደ እርሱ መጸለይህን አታቋርጥ” አሉት። 9 ስለዚህ ሳሙኤል አንድ የሚጠባ የበግ ግልገል ወስዶ ሙሉ ለሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ ለጌታ አቀረበው፤ ስለ እስራኤልም ወደ ጌታ ጸለየ፤ ጌታም መለሰለት። 10 ሳሙኤል የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያሳርግበት ጊዜ፥ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለመውጋት ቀረቡ። ጌታ ግን በዚያ ዕለት በፍልስጥኤማውያን ላይ ከባድ የነጐድጓድ ድምፅ አንጐዳጐደባቸው፤ እነርሱም እጅግ ተሸበሩ፤ በእስራኤላውያን ፊት ድል ተመተውም ሸሹ። 11 እስራኤላውያንም ከምጽጳ ተነሥተው ፍልስጥኤማውያንን እስከ ቤትካር በታች እያሳደዱ በየመንገዱ ገደሉአቸው። 12 ከዚህ በኋላ ሳሙኤል አንድ ድንጋይ ወስዶ በምጽጳና በሼን መካከል አቆመው፤ “ጌታ እስከ አሁን ድረስ ረድቶናል” ሲል ስሙን “አቤንኤዘር” ብሎ ጠራው። 13 በዚህ ሁኔታ ፍልስጥኤማውያን ድል ስለተመቱ የእስራኤልን ምድር ዳግመኛ አልወረሩም። ሳሙኤል በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ የጌታ እጅ በፍልስጥኤማውያን ላይ ነበረች። 14 ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል የወሰዷቸው ከዔቅሮን እስከ ጌት የነበሩ ከተሞች ለእስራኤል ተመለሱላት፤ ግዛታቸውም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ነፃ ወጣች፤ በእስራኤልና በአሞራውያንም መካከል ሰላም ወርዶ ነበር። 15 ሳሙኤል በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ፥ እስራኤልን ይዳኝ ነበር። 16 በየዓመቱ በቤቴል፥ በጌልጌላና በምጽጳ እየተዘዋወረ፥ በእነዚህ ቦታዎች ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። 17 ከዚያም በራማም ወዳለው ቤት ይመለስ ነበር፤ በዚያም ደግሞ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። በዚያም ለጌታ መሠዊያ ሠራ። |