Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

1 ሳሙኤል 14 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ዮናታን በፍልስጥኤማውያን ላይ የጣለው አደጋ

1 አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፥ “ና በሌላ በኩል ወዳለው የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ይህን ግን ለአባቱ አልነገረውም ነበር።

2 ሳኦልም በጊብዓ ዳርቻ በሚግሮን ከአንድ የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ስድስት መቶ ያህል ሰዎችም አብረውት ነበሩ፤

3 ኤፉድ ይለብስ የነበረውም አኪያ በመካከላቸው ነበር። እርሱም በሴሎ የጌታ ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ ነበር። ሕዝቡም ዮናታን አለመኖሩን አላወቁም ነበር።

4 ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ለመሻገር በፈለገበት መተላለፊያ ግራና ቀኝ ሁለት ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ፤ የአንዱ ስም ቦጼጽ ሲሆን፥ ሌላው ሴኔ ተብሎ ይጠራል።

5 ከድንጋዮቹም አንዱ ከመተላለፊያው በስተ ሰሜን በኩል በሚክማስ ፊት ለፊት የሚገኘው ሲሆን፥ ሁለተኛውም በስተ ደቡብ በኩል በጌባዕ ፊት ለፊት ይገኝ ነበር።

6 ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፥ “ና፤ ወደነዚያ ያልተገረዙ ሰዎች ጦር ሰፈር እንሻገር፤ ምናልባትም ጌታ ይዋጋልን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት ለማዳን ጌታን የሚያግደው የለምና” አለው።

7 ወጣቱ ጋሻ ጃግሬም፥ “በልብህ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ፤ ወደ ኋላም አትበል፤ እኔም በሙሉ ልብ ካንተው ጋር ነኝ” አለው።

8 ዮናታንም እንዲህ አለው፥ “እንግዲያውስ ና፤ ወደ ሰዎቹ እንሻገርና እንታያቸው።

9 እነርሱም፥ ‘ወደ እናንተ እስክንመጣ እዚያው ጠብቁን’ ካሉን፥ ስፍራችንን ይዘን እንጠብቃቸዋለን፤ ወደ እነርሱም አንወጣም።

10 ነገር ግን፥ ‘ወደ እኛ ኑ’ ካሉን፥ ጌታ እነርሱን በእጃችን አሳልፎ የሰጠን ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ስለሆነ፥ ወደ እነርሱ እንወጣለን።”

11 ሁለቱም ለፍልስጥኤማውያን ሠራዊት በታዩ ጊዜ፥ ፍልስጥኤማውያን፥ “እነሆ፤ ዕብራውያን ከተደበቁባቸው ጉድጓዶች እየወጡ ነው” አሉ።

12 የፍልስጥኤም ጦር ሰፈር ሰዎችም፥ “ኑ ወደ እኛ ውጡ፤ የምናሳያችሁ ነገር ይኖራል” ሲሉ በዮናታንና በጋሻ ጃግሬው ላይ ጮኹባቸው። ስለዚህ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፥ “ተከትለኸኝ ውጣ፤ ጌታ በእስራኤላውያን እጅ አሳልፎ ሰጥቷቸዋልና” አለው።

13 ዮናታን በእጁና በእግሩ ወደ አፋፉ፥ ጋሻ ጃግሬውን በማስከተል ወጣ። በዮናታንም እጅ ወደቁ፤ ጋሻ ጃግሬውም ከበስተኋላው እየተከተለ ገደላቸው።

14 ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በመጀመሪያው ቀን ባደረጉት ግዳያቸው በአንድ ጥማድ የእርሻ ቦታ ላይ ሃያ ያህል ሰዎች ገደሉ።

15 በሰፈር በእርሻ ላይና በሕዝብ ሁሉ መካከል ሽብር ሆነ፤ ከተማ ጠባቂዎችና አደጋ ጣዮችም ሁሉ ተቀጠቀጡ፤ ምድሪቱም ተናወጠች፤ ሽብሩም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ነበር።


የፍልስጥኤማውያን መሸነፍ

16 በብንያም ግዛት በጊብዓ የነበሩ የሳኦል ጠባቂዎች፥ የፍልስጥኤም ሠራዊት በየአቅጣጫው መበታተኑን አዩ።

17 ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች፥ “ሠራዊቱን ቁጠሩና ማን ከዚህ እንደ ሄደ ለዩ” አላቸው። በቆጠሩም ጊዜ፥ እነሆ፥ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልነበሩም።

18 ሳኦልም አኪያን፥ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደዚህ አምጣ” አለው፤ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር ታቦት በእስራኤላውያን ዘንድ ነበር።

19 ሳኦል ለካህኑ በመናገር ላይ ሳለ፥ በፍልስጥኤማውያን ሰፈር ሁካታው እየጨመረ ሄደ። ስለዚህ ሳኦል ካህኑን፥ “እጅህን መልስ” አለው።

20 ከዚያም ሳኦልና ሰዎቹ ተሰብስበው ወደ ውጊያው ሄዱ። እዚያም ፍልስጥኤማውያን ግራ በመጋባት በታላቅ ትርምስ እርስ በርሳቸው በሰይፍ ይጋደሉ ነበር።

21 እነዚያ ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጐን ተሰልፈው የነበሩትና አብረዋቸውም ወደ ሰፈራቸው የወጡት ዕብራውያን ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደነበሩት እስራኤላውያን ገቡ።

22 በተራራማው የኤፍሬም አገር ተሸሽገው የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ ፍልስጥኤማውያኑ በሽሽት ላይ መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ፥ እነርሱም አጥብቀው በመከታተል ሊወጉአቸው አሳደዷቸው።

23 በዚያ ቀን ጌታ እስራኤልን ታደገው፤ ጦርነቱም ከቤትአዌን ዘልቆ ሄደ።


ከጦርነቱ በኋላ የተፈጸሙ ድርጊቶች

24 ሳኦል፥ “ዛሬ ጠላቶቼን ከመበቀሌ በፊት፥ እስከ ማታ ድረስ እህል የሚበላ ሰው የተረገመ ይሁን” ብሎ ሕዝቡን አስምሎ ስለ ነበር፥ በዚያች ዕለት የእስራኤል ሰዎች ተጨንቀው ዋሉ፤ ስለዚህ ከሕዝቡ አንድም እህል የቀመሰ አልነበረም።

25 ሕዝቡም ሁሉ ወደ ጫካ ሲገባ፥ ማር በመሬቱ ላይ ይታይ ነበር።

26 ሕዝቡ ወደ ጫካው በገባ ጊዜ፥ የማሩ ወለላ እየተንጠባጠበ ወደ ምድር መውረዱን አየ፤ ሆኖም መሓላውን ፈርቶ ስለ ነበር፥ እጁን ወደ አፉ የዘረጋ ማንም አልነበረም።

27 ነገር ግን ዮናታን አባቱ ሕዝቡን በመሐላ ማሰሩን አልሰማም ነበር። ስለዚህ በእጁ የያዘውን ዘንግ ጫፍ በማሩ ወለላ ውስጥ በማስገባት እጁን ወደ አፉ አደረገ፤ ዐይኑም በራ።

28 ከሕዝቡም አንድ ሰው፥ “አባትህ ሕዝቡን፥ ‘ዛሬ እህል የሚቀምስ ማናቸውም ሰው የተረገመ ይሁን!’ በማለት በጽኑ መሓላ አስጠንቅቆናል” አለው። ሰው ሁሉ ተዳክሞ ነበር።

29 ዮናታንም እንዲህ አለ፤ “አባቴ በምድሪቱ ላይ ችግር ፈጥሯል፤ ከዚህ ማር ጥቂት በቀመስሁ ጊዜ ዐይኔ እንዴት እንደ በራ ተመልከቱ!

30 ሕዝቡ ከጠላቶቻቸው እጅ ከወሰዱት ምርኮ ዛሬ በልተው ቢሆን ኖሮ ምንኛ በተሻለ ነበር፤ የተገደሉትም ፍልስጥኤማውያን ቍጥር ከዚህ በበለጠ ነበር።”

31 በዚያች ዕለት ፍልስጥኤማውያንን ከሚክማስ እስከ አያሎን ድረስ ከመቷቸው በኋላ ሕዝቡ እጅግ ዝለው ነበር።

32 በምርኮው ላይ ተረባርበው በጉን፥ በሬውንና ጥጃውን በመውሰድ በመሬት ላይ ዐርደው ሥጋውን ከነደሙ በሉት።

33 ከዚያም ለሳኦል፥ “እነሆ፤ ሕዝቡ ሥጋውን ከነደሙ በመብላት ጌታን እየበደለ ነው” ተብሎ ተነገረው። ሳኦልም፥ “ይህ የክሕደት ተግባር ነው! አንድ ትልቅ ድንጋይ አንከባላችሁ ወደዚህ አምጡልኝ” አለ።

34 ሳኦልም፥ “በሕዝቡ መካከል እየዞራችሁ፥ ‘እያንዳንዳችሁ በሬዎቻችሁንና በጎቻችሁን አምጡ፤ እዚሁ ዐርዳችሁ ብሉ፤ ነገር ግን ሥጋውን ከነደሙ በመብላት ጌታን አትበድሉ’ በሏቸው” አለ። ስለዚህ በዚያች ሌሊት እያንዳንዱ ሰው በሬውን አምጥቶ በዚያ አረደው።

35 ሳኦልም ለጌታ መሠዊያ ሠራ፤ ለጌታ መሠዊያ ሲሠራም ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነበር።

36 ከዚያም በኋላ ሳኦልም፥ “ፍልስጥኤማውያንን ተከትለን በሌሊት እንውረድና እስኪ ነጋ ድረስ እንዝረፋቸው፤ አንድም ሰው በሕይወት አናስቀርላቸው” አለ። እነርሱም “መልካም መስሎ የታየህን ሁሉ አድርግ” ብለው መለሱለት። ካህኑ ግን፥ “ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ” አለ።

37 ሳኦልም፥ “ፍልስጥኤማውያንን ተከትዬ ልውረድን? በእስራኤላውያንስ እጅ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እርሱ ግን በዚያች ቀን አልመለሰለትም።

38 ሳኦል እንዲህ አለ፦ “እናንተ የሕዝቡ አለቆች ሁሉ፥ ወደዚህ ቅረቡ፥ ዛሬ ይህ ኃጢአት በምን እንደሆነ እወቁ፥ ተመልከቱም።

39 እስራኤልን የታደገ ሕያው ጌታን! አድራጊው ልጄ ዮናታን እንኳ ቢሆን መሞት አለበት።” ነገር ግን ከሕዝቡ መካከል የመለሰለት አንድም አልነበረም።

40 ለእስራኤላውያን ሁሉ፥ “እናንተ በዚያ በኩል ቁሙ፤ እኔና ልጄ ዮናታን ደግሞ በዚህ በኩል እንቆማለን” አላቸው። ሰዎቹም፥ “መልካም መስሎ የታየህን አድርግ” አሉት።

41 ሳኦል፥ “ትክክለኛውን መልስ ስጠኝ” ሲል ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ጌታ ጸለየ፤ ዕጣው በሳኦልና በዮናታን ላይ ወደቀ፤ ሕዝቡም ነጻ ሆነ።

42 ሳኦልም፥ “በእኔና በልጄ በዮናታን መካከልም ዕጣ ጣሉ” አላቸው። ዕጣውም በዮናታን ላይ ወደቀ።

43 ከዚያም ሳኦል ዮናታንን፥ “ያደረግኸውን ነገር ንገረኝ” አለው። ዮናታንም፥ “በበትሬ ጫፍ ጥቂት ማር ቀምሻለሁ፤ እነሆኝ፥ ለመሞት ዝግጁ ነኝ” አለው።

44 ሳኦልም፥ “ዮናታን፥ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብኝ፤ እንዲህም ይጨምርብኝ፤ ዛሬ ፈጽመህ ትሞታለህ” አለ።

45 ሕዝቡ ግን ሳኦልን፥ “ለእስራኤል ይህን ታላቅ ድል ያስገኘ ዮናታን መሞት ይገባዋልን? ይህ አይሆንም! ዛሬ ይህን ያደረገው በእግዚአብሔር ርዳታ ስለ ሆነ፥ ሕያው ጌታን! ከራስ ጠጉሩ አንዲቱ እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም” አሉት። ስለዚህ ሰዎቹ ዮናታንን ታደጉት፤ እርሱም ከመሞት ዳነ።

46 ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመለሰ፤ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ስፍራቸው ተመለሱ።


የሳኦል ዘመነ መንግሥትና ቤተሰቡ

47 ሳኦል በእስራኤል ላይ ከነገሠ በኋላ፥ በዙሪያው ያሉትን ጠላቶቹን ሞዓብን፥ አሞናውያንን፥ ኤዶምን፥ የጾባን ነገሥታትና ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው። በተዋጋበት ስፍራ ሁሉ ድል አድራጊ ነበር።

48 በጀግንነት ተዋግቶ አማሌቃውያንን አሸነፈ፤ እስራኤልንም ይዘርፏቸው ከነበሩት እጅ ታደጋቸው።

49 የሳኦል ወንዶች ልጆች ዮናታን፥ ይሽዊና ማልኪሹዓ ነበሩ፤ ሴቶች ልጆቹም ትልቋ ሜሮብ፥ ትንሿ ሜልኮል ይባሉ ነበር።

50 የሳኦል ሚስት አሒኖዓም የምትባል የአሒማዓጽ ልጅ ነበረች፤ የሠራዊቱም አዛዥ አበኔር የሚባል የሳኦል አጎት የኔር ልጅ ነበረ።

51 የሳኦል አባት ቂስና የአበኔር አባት ኔር የአቢኤል ልጆች ነበሩ።

52 በሳኦል ዘመን ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ከባድ ጦርነት ነበረ፤ ሳኦልም ብርቱ ወይም ጀግና ሰው ባየ ቍጥር ወደ ራሱ ይሰበስብ ነበር።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች