Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 9 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የይሁዳ መቃቢስ መሞትና የቤርሶይት ጦርነት

1 ደሜጥሮስ የኒቃኖርን ከነሠራዊቱ በጦርነት ላይ መውደቅ በሰማ ጊዜ እንደገና ባቂደስንና አልቅሞስን ከሠራዊቱ የቀኝ ክንፍ ሠራዊት ጋር ወደ ይሁዳ አገር ላከ።

2 እነርሱ ወደ ገሊላ በሚወስደው መንገድ አልፈው በአርበሊስ ምድር የምትገኘዋን መላሎትን ከበቡና ያዟት፤ እዚያ ብዙ ሰዎችን ገደሉ።

3 በመጀመሪያው ወር በመቶ ሐምሳ ሁለት ዓመተ ዓለም በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ሠፈሩ፤

4 ከዚያ ተነሥተው ከሃያ ሺህ እግረኛና ከሁለት ሺህ ፈረሰኛ ሠራዊት ጋር ወደ ቤርሳይት ሄዱ።

5 ይሁዳ ግን ምርጥ የሆኑ ሦስት ሺህ ተዋጊዎች ይዞ ሰፈሩን በኤልአሳ አደረገ።

6 የጠላት ወታደሮች ተደናግጠው ብዙዎቹ ከዱ፤ ከስምንት መቶ ሰዎች በቀር ሌላ የተገኘ የለም።

7 ውጊያው ልክ ሊጀመር በታቀደበት ሰዓት ይሁዳ የእርሱ ሠራዊት የጐደለበት መሆኑን አየ፤ ወታደሮቹን ለማሰባሰብ ጊዜ በማጣቱ ልቡ በኀዘን ተሰበረ።

8 ተስፋ ቆርጦ የቀሩትን ወታደሮች፥ “እንነሣ፤ ምናለበት ልንወጋቸው እንችል እንደሆነ እንውጣና እንግጠማቸው” አለ።

9 እነርሱ አይሆነም አሉት፤ “አሁን ለጊዜው እኛ ሕይወታችንን ከማዳን በቀር ምንም ማድረግ አንችልም፤ ከወንድሞቻችን ጋር ሆነን ተመልሰን እንዋጋለን፤ አሁን እኛ በጣም ጥቂቶች ነን” አሉት።

10 ይሁዳም፥ “እኔ ሽሽትን መርጧል አልባልም፤ ሰዓታችን ደርሶ ከሆነ ስለ ወንድሞቻችን በጀግንነት እንሙት፤ ክብራችንን አናስነውር” ሲል መለሰላቸው።

11 የጠላት ጦር ሠራዊት ከሰፈሩ ወጥቶ ውጊያ ሊገጥማቸው መጣ፤ ፈረሰኛ ጦር በሁለት ክፍል ተከፍሎ ነበር፤ ከጦር ሠራዊቱ ፊት ቀድመው ወንጫፊዎችና ቀስተኞች እንዲሁም የፈጥኖ ደራሽ ጀግኖች ሁሉ ይሄዱ ነበር።

12 ባቂዳስ በቀኝ ክንፍ በኩል ነበር፤ መለከት እየተነፋ ሠራዊቱ በሁለት ጐን ወደ ፊት ይሄድ ነበር። የይሁዳ ሰዎችም እንዲሁ መለከት ነፉ።

13 ከሠራዊቱ ድምፅ የተነሣ ምድር ተንቀጠቀጠች ውጊያውም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ቀጠለ።

14 በቂደስና ኃይለኛው ጦር በቀኝ በኩል መሆኑን ይሁዳ አየ፤ በድፍረት የተሞሉትን ሁሉ በይሁዳ ዙሪያ አሰባሰቡ፤

15 በቀኝ ክንፍ በኩል ያሉትን ገለባበጡና እስከ አዞጦን (አዘሬ) ኮረብታ ድረስ አባረሩዋቸው፤

16 የቀኝ ክንፍ ሰዎች መሸነፋቸውን ባዩ ጊዜ የግራ ክንፍ ሰዎች ወደ ይሁዳና ወደ እርሱ ሰዎች ተመልሰው ተከተሉት።

17 የከረረ ውጊያ ተደረገ፤ ከዚህም ከዚያም ብዙ ሰዎች አለቁ።

18 ይሁዳም ወደቀ፤ ሌሎቹ ሸሹ።


የይሁዳ መቃቢስ የቀብር ሥነ ሥርዓት

19 ዮናታንና ስምዖን ወንድማቸውን ይሁዳን አንሥተው በሞዲን በአባቶቹ መቃብር ቀበሩት።

20 መላው የእስራኤል ሕዝብ አለቀሱለት፤ ትልቅ ኀዘንም አደረጉለት፤

21 “እስራኤልን ያድን የነበረው ጀግና እንዴት ወደቀ?” እያሉ ብዙ ቀኖች አለቀሱ።

22 ሌሎቹ የይሁዳ ሥራዎች፥ የዋለባቸው ጦር ሜዳዎች፤ የሰበሰባቸው ምርኮዎች፤ በየወቅቱ ያገኛቸው ከፍተኛ ማዕረጎች አልተመዘገቡም። ነገር ግን እጅግ በርካታ እንደ ነበሩ የተሰወረ አልነበረም።


የአይሁድ መሪና የካህናት አለቃ ዮናታን የግሪኩ ቡድን ድል፤ ዮናታን ተቃውሞውን መራ

23 ከይሁዳ ሞት በኋላ አመፀኞቹ ከሐዲዎቹ እንደገና በእሥራኤል ምድር ሁሉ ብቅ ብቅ አሉ፤

24 በዚያን ጊዜ ትልቅ ረሃብ ስለ ነበር አገሩ ከእርሱ ጋር ተስማማ፤

25 ባቂደስ ሆን ብሎ ከዓመፀኞቹ መካከል አገሩን የሚያስተዳድሩ ሰዎች መረጠ፤

26 የይሁዳን ወዳጆች እያደኑ ይዘው ወደ ባቂደስ ይወስዷቸው ነበር፤ ያላግጡባቸው ነበር፥

27 የነቢያት መጨረሻ ጊዜ ከነበረበት ቀን አንሥቶ እንዲህ ያለ ጭቆና በእስራኤል ላይ ተደርጐ አይታወቅም ነበር።

28 በዚያን ጊዜ የይሁዳ ወዳጆች ተሰበሰቡና ዮናታንን እንዲህ አሉት፤

29 “ወንድምህ ይሁዳ ከሞተ ጀምሮ እንደ እርሱ ያለ በጠላቶቻችን ላይ በባቂደስና የሕዝባችን ጠላቶች በሆኑት ሰዎች ላይ የሚነሣ ሰው አልተገኘም።

30 ስለዚህ ውጊያችንን እንድናደርግ አንተን ዛሬ በእርሱ ቦታ አለቃችንና መሪያችን አድርገን መርጠንሃል”

31 ዮናታን ወዲያውኑ መሪነትን ተቀብሎ በወንድሙ በይሁዳ ቦታ ተተካ።


ዮናታን በተቆዓ በረሃ ውስጥ በሜዴባ ዙሪያ ያካሄደው ደም አፍሳሽ ፍልሚያ

32 ባቂደስ ይህን በሰማ ጊዜ ዮናታንን ሊገድለው ፈለገ።

33 ለዮናታንና ለወንድሙ ለስምዖን እንዲሁም ዮናታንን ለተከተሉት ሰዎች ሁሉ ይህን ዜና ስለደረሳቸው፤ ወደ ተቆዳ ሸሽተው ሄዱ፤ በአጽፋር በሚባለው የበረሃ ገነትም አጠገብ ሠፈሩ።

34 ባቂደስ በሰንበት ቀን ይህን ነገር ሰማና ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር ሆኖ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ተሻገረ።

35 ዮናታን ጓዙ ብዙ ስለ ነበረ ወዳጆቹ ናቦታውያን ጓዙን በእነርሱ ዘንድ ለማስቀመጥ እንዲፈቅዱለት ለመጠየቅ የወታደሮች አዛዥ የነበረውን ወንድሙን ወደ እነርሱ ላከው።

36 ግን ከሜዳባ ወገን የሆኑ አምራይ ልጆች መንገድ ላይ ጠብቀው ዮሐንስና ያለውንም ነገር ሁሉ ዘርፈው ምርኮአቸውን ይዘው ሄዱ።

37 ይህ ነገር ከተደረገ በኋላ የአምራይ ልጆች ትልቅ የጋብቻ በዓል የሚያደርጉ መሆናቸውን ለዮናታንና ለወንድሙ ለስምዖን ተነገራቸው፤ ሙሽራይቱን ከናዳባት (ከናባታ) በታላቅ ክብር ያመጡ ነበር። እርሷ የአንድ በከነዓን አገር የተከበረ ሰው ልጅ ነበረች።

38 እነርሱም የወንድማቸውን የዮሐንስን መገደል አስታወሱ፥ ከተራራ ላይ ወጥተው ከተራራው ጥግ በስተ ኋላ ተደበቁ።

39 ቀና ብለው በጫጫታ መካከል ብዙ ሰዎች ሲመጡ አዩ፤ ሙሽራው፤ ሚዜዎቹና ወንድሞቹ ብዙ ጓዝ ይዘው ከአጀቡ ፊት ፊት እየሄዱ፥ ከበሮ እየመቱ፥ እየዘፈኑ በጦርነት ጊዜ እንደሚሆነው የደመቀ ትርኢት እያሳዩ ሲመጡ ተመለለከቱ።

40 ከተደበቁበትም ዘለው በውጣት ጨፈጨፍዋቸው፤ ብዙዎቹ ቆስለው ወደቁ፤ የተረፉትም ወደ ተራራው ሸሹ፤ እነዮናታን የሰዎቹን ዕቃዎች ሁሉ ይዘው ሄዱ።

41 በእዚህ ዓይነት ሰርጉ ወደ ኀዘን ተለወጠ፤ ሙዚቃውም ወደ ዋይታ ተለወጠ፤

42 የወንድማቸውንም ደም እንደዚህ ተበቀሉና ወደ ዮርዳኖስ ረግረግ ስፍራዎች ተመልሰው ሄዱ።


ዮርዳኖስን ማቋረጥ

43 ባቂደስ ይህ ነገር ተነገረውና ከብዙ ሠራዊት ጋር እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ድረስ በሰንበት ቀን ሄደ።

44 በዚያን ጊዜ ዮናታን የእርሱን ሰዎች እንዲህ አላቸው፥ “እንነሣ፤ ሕይወታችንን ለማዳን እንዋጋ፤ ምክንያቱም ዛሬ እንደ ትላንትና እንደ ትላንት በስቲያ አይደለም።

45 እንደምትመለከቱት ከፊትም ከኋላም መዋጋት አለብን በአንድ በኩል በዮርዳኖስ ውሃ በሌላ በኩል ማጥና ጫካው ስለሚጠብቀን ምንም ማምለጫ ቀዳዳ አይኖረንም።

46 አሁን እንግዲህ ከጠላቶቻችሁ እጅ ለማምለጥ ወደ ሰማይ ጩሁ”።

47 ዮናታን ፍልሚያውን ጀመረ፤ ዮናታን ባቂደስን ለመምታት እጁን ሠነዘረ፤ ሶሪያዊው ግን ራሱን አላቆ ተፈተለከ፤

48 ዮናታንና ጓደኞቹ በዮርዳኖስ ውስጥ ዘልለው ገቡና እየዋኙ ወዲያ ማዶ ተሻገሩ፤ ጠላት ግን ተከትለዋቸው ለመሻገር አልቻሉም።

49 በዚያ ቀን በቂደስ ሺህ ተከታዮቹን አጣ።


ባቂደስ ምሽጎችን ገነባ አልቂይሞስ ሞት

50 ባቂደስ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። በይሁዳ ምድር ከተሞች ሠራ፤ በኢያሪኮ፥ በኤማሁስ፥ በቤቶሮን፥ በቤቴል፥ በተሞናታ፥ በፋራቶን፥ በጫፎን ምሽግ ሠራ፤ ከፍተኛ ግንቦችንና መዝጊያዎችን፥ መሸጐሪያዎችንም አደረገ።

51 እስራኤላውያን ለማስጨነቅ በእያንዳንዱ ምሽግ ወታደሮችን አቆመ።

52 የቤተሱራን፥ የጊዜርን፥ የኢየሩሳሌምን ምሽግ አጠናከረ። በእዚያ ወታደሮችና የስንቅ መጋዘንን አደረገ።

53 የአገሩን ታላላቅ ሰዎች ልጆቻውን በመያዣነት ያዘባቸውና በኢየሩሳሌም ምሽግ ውስጥ አሠራቸው።

54 በመቶ ሐምሳ ሦስት ዓመተ ዓለም፤ በሁለተኛው ወር አልቂሞስ የቤተ መቅደሱን የውስጥ ግንብ እንዲያፈርስ አዘዘ፤ ዕቅዱም የነቢያትን ሥራ ለማፍረስ ነበር። የማፍረሱንም ሥራ አስጀመረ።

55 በዚያን ጊዜ አልቂሞስ መቅሠፍት አገኘው፥ ሥራውም ተቋረጠ፤ አንደበቱ ተያዘ፤ ሽባ ሆነ፤ ከዚያ ወዲያ አንዲት ቃል እንኳን መናገርና ስለ ቤቱ አንድ ነገር እንኳ ማዘዝ አቃተው።

56 አልቂሞስ ብዙም ሳይቆይ በከፍነተኛ ስቃይ ሞተ።

57 ባቂደስ የአልቂሞስን ሞት ባየ ጊዜ ወደ ንጉሡ ተመለሰ፤ በይሁዳ አገርም ሁለት ዓመት ሰላም ሆነ።


የቤትባሲ መከበብ

58 ከሐዲዎች እንዲህ ሲሉ ተማከሩ፥ “እነሆ ዮናታንና የእርሱ ተከታዮች በሰላምና ያለ ፍርሃት ይኖራሉ፤ ስለዚህ ሄደን ባቂደስን እናመጣዋለን፤ እርሱ ሁሉንም ባንድ ሌሊት ይዞ ያስራቸዋል።”

59 ሄደውም ከእርሱ ጋር ተማከሩ።

60 ባቂደስ ብዙ ወታደሮች ይዞ ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ ዮናታንንና ጓደኞቹን እንዲይዙ በይሁዳ አገር ለሚገኙ የጦር ጓደኞቹ ሁሌ በሥውር ይጽፍላቸው ነበር። ግን ሐሳባቸው ከሸፈባቸውና ያሰቡት አልሆነላቸውም።

61 እንዲያውም ይህን ክፉ ምክር የመከሩ ሐምሳ የሚሆኑ የሀገሩ ሰዎች ተይዘው ተገደሉ።

62 ከዚህ በኋላ ዮናታንና ስምዖን ተከታዮቻቸውም ወደ በረሃ፥ ወደ ቤትባሲ ሄዱ። እዚያ የፈራረሱትን እንደገና ሠሩ ከተማዋንም አጠናከሩ።

63 ባቂደስ ይህን ሰምቶ ወታደሮቹን ሁሉ ሰበሰበ፤ በይሁዳ ምድር ላሉት ተከታዮችም አስታወቃቸው።

64 በቤትባሲ ፊት ለፊት ቦታ ያዘና ከብቦ ለብዙ ቀናት ቤትባሲን ወጋት፤ የውጊያ ተሽከርካሪዎችንም አሠራ።

65 ዮናታን ወንድሙን ስምዖንን በከተማ ትቶ ከቂት ሰዎች ጋር ሆኖ ወደ ገጠር ወጣ።

66 ኦዶሜራንና ወንድሞቹን እንዲሁም የፋሴሮንን ልጆች በሠፈራቸው እንዳሉ ወጋቸው፤ እነሱም ከእርሱ ኃይል ጋር ተደባለቁ።

67 ስምዖንና ሰዎቹ ወጡና ተሽከርካሪዎቹን አቃጠሉ።

68 ባቂደስን ወጉት እርሱ ተሸንፎ ሐሳቡ ስላልተሳከላት በታላቅ ጭንቀት ላይ ወደቀ።

69 ንዴቱንም ወደ ይሁዳ እንዲገባና በይሁዳ ወረዳ ላይ እንዲፈጽም ያነሣሡትን ከሐዲዎችን ሁሉ ሰብስቦ በመግደል እልሁን ተወጣ። ወዲየውኑ ወታደሮቹን ያዘ ወደ ሀገሩ ተመለሰ።

70 ይህን በሰማ ጊዜ ዮናታን ሰላም ለማድረግና እስረኞችን ለመለዋወጥ ወደ እርሱ መልእክተኞችን ላከ፤

71 እርሱም ነገሩን ተቀብሎ ዮናታን በጠየቀው መሠረት አደረገ፤ ከእንግዲህ ወዲህ በመላ ሕይወቱ በእርሱ ላይ ክፉ ማድረግ እንደሚይፈልግም ማለለት።

72 በይሁዳ አገር የማረካቸውንም ሰዎች መለሰለት፤ ከዚህ በኋላ ወደ ሀገሩ ተመለሶ ሄደ፤ ዳግመኛ ወደ ድንበሮቻቸው አልተመለሰም፤

73 በእስራኤል ላይ ሰይፍ ማንዣበብ አቆመ፥ በማቅማስ ዮናታን ተቀመጠ፤ እዚያ ሕዝቡን መደኘት ጀመረ፤ ዓመፀኞችንም ከእስራኤል አጠፋ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች