ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ 1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የቀዳማዊ ዲሜጥሮስ መንገሥ፥ የባቂደስና የአልቂሞስ ወደ ይሁዳ መላክ 1 በመቶ ሐምሳ አንድ ዓመት ገደማ የሰለውቂስ ልጅ ዲሜጥሮስ ከሮም አምልጦ ከጥቂት ሰዎች ጋር ባሕር አጠገብ ወደምትገኝ ወደ አንዲት ከተማ ሄደ፤ እዚያ ነገሠ። 2 ወደ አባቶቹ ቤተ መንግሥት በገባ ጊዜ ሠራዊቱ አንጥዮኩስንና ሊስያስን ወደ እርሱ ለማምጣት ያዙዋቸው፤ 3 ይዘናቸዋል ብለው ቢነግሩትም፥ “ፊታቸውን አታሳዩኝ” አላቸው። 4 ሠራዊቱም ገደላቸው። ዲሜጥሮስም በንጉሣዊ ዙፋኑ ላይ ተቀመጠ። 5 በዚያን ጊዜ ከእስራኤል ሕዝብ ውስጥ ሃይማኖትና ሕግ ያልነበራቸው ሰዎች ሁሉ የሊቀ ካህንነት ሹመት ይመኝ በነበረው በአልቂሞስ ተመርተው ወደ እርሱ መጡ። 6 በንጉሡ ፊት ሕዝቡን እንዲህ ሲሉ አወገዙ፥ “ይሁዳና ወንድሞቹ ወዳጆችህን ሁሉ አጠፉ፤ እኛንም ከሀገራችን ውጭ እንድንበታተን አደረጉን፤ 7 ስለዚህ አሁን በኛ መካከልና በንጉሡ ግዛት ውስጥ ይሁዳ የጠፋቸውን ጥፋቶች ሂዶ እንዲያይ አንድ የታመነ ሰው ላክ፤ እነርሱና ረዳቶቻቸውም ሁሉ ይቀጡ”። 8 ንጉሡም ታላቅና ታማኝ የነበረውን የአፍራጦስ ማዶ ገዢና ከንጉሡ ወዳጆች አንዱ የነበረውን ባቂደስን መረጠ። 9 ከኀጢአተኛው ከአልቂሞስ ጋር ላከው፤ ለአልቂማስ የክህነት ሥልጣን ሰጠውና የእስራኤልን ልጆች እንዲቀበል ሾመው። 10 ከብዙ ሠራዊት ጋር አብረው ሄዱና ወደ ይሁዳ ምድር ደረሱ፤ ለይሁዳና ለወንድሞቹ የውሸት የሰላም ቃል የያዘ መልእክት ላኩ። 11 አይሁዳውያኑ እነርሱ የባዕድ ሠራዊት ይዘው መምጣታቸውን ባዩ ጊዜ ንግግራቸውን አላመኑም። 12 የሙሴ ሕግ መምህራን ትክክለኛ መፍትሔ ለመፈለግ ተሰብስበው ወደ አልቄሚስና ወደ ባቂደስ ሄዱ። 13 ከእስራኤላውያን መካከል የመጀመሪያዎቹ ሰላም ፈላጊዎች አሲዳውያን ነበሩ። 14 እነርሱም፥ “ከወታደሮቹ ጋር አብሮ የመጣው ከአሮን ዘር የሆነው ካህን ነው፤ በእኛ ላይ ፍርድን አጓድሎ ክፉ ነገር አያደርግብንም” ይሉ ነበር። 15 እርሱም የሰላም ንግግር አደረገላቸውና፥ “በናንተም ሆነ በወዳጆቻችሁ ላይ ምንም ክፉ ነገር አናደርግባችሁም” ሲል በመሐላ አረጋገጠላቸው። 16 እነርሱም አመኑት፤ ነገር ግን በመጽሐፉ ላይ እንደተጠቀሰው ስድሳዎቹን አስይዞ ባንድ ቀን አስገደላቸው፤ 17 ይህንም ያደረገው፥ “በኢየሩሳሌም ዙሪያ የቅዱሳንህን ሥጋ በትነዋል፥ ደማቸውንም አፍስሰዋል፤ የሚቀብራቸው ማንም አልነበረም” ተብሎ የተጻፈው ይፈጸም ዘንድ ነው። 18 “ያደረጉትን ስምምነትና መሐላ ስላፈረሱ እነዚያ ሰዎች እውነተኝነትና ትክክለኝነት የለባቸውም” ተባሉ። ፍርሃትና ጭንቀትም በነሱ ላይ ነገሠ። 19 ባቂደስ ከኢየሩሳሌም ሄዶ ሰፈሩን በቤተዜት አደረገ፤ እርሷን ትተው ከሄዱትም ሰዎች መካከል ብዙዎችን አሠረ፤ እንዲሁም ከሕዝቡ አንዳንዶቹን አስያዘ፤ እንዲገደሉም አደረገ በኋላ በታላቁ ጉርጓድ ውስጥ ጣላቸው። 20 ክፍለ ሀገሩን አልቂሞስ መልሶ ሰጠው፤ የሚያግዘው ሠራዊትም ተወለት፤ ከዚህ በኋላ ባቂደስ ወደ ንጉሡ ተመልሶ ሄደ። 21 አልቂሞስ ሊቀ ካህናት መሆኑን ለማሳመን ታገለ፤ 22 በሕዝቡ መካከል ሁከት ይነዙ የነበሩ ሰዎች ሁሉ በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ የይሁዳን ምድር ያዙ፤ በእስራኤል ላይ ትልቅ ጉዳት አመጡ። 23 ይሁዳ በእስራኤል ልጆች ላይ ከአረመኔዎች የባሰ የሚያደርጉትን የአልቂሞስንና ወገኖቹን ክፋት ባየ ጊዜ 24 በይሁዳ አገሮች ሁሉ በዙሪያቸው ተዘዋወረ፤ በከሐዲዎች ላይ ተበቀለ፤ በአገሩ ውስጥ እንዳይዘዋወሩ ከለከለ። ኒቃኖረ በይሁዳ ምድር፥ የካፋር ሳልማ ጦርነት 25 ይሁዳና ጓደኞቹ ይበል ብርቱዎች መሆናቸውን ባየ ጊዜና ሊቋቋማቸው አለመቻሉን በተገነዘበ ጊዜ አልቂሞስ ወደ ንጉሡ ተመልሶ ብዙ ክፋት ሠርተዋል ሲል ከሰሳቸው። 26 የእስራኤልን ሕዝብ በጥላቻና በጠላትነት የሚመለከተውን ከክቡራት ክፍል ሆኖ ከጦር መሪዎቹ አንዱ የነበረውን ኒቃኖርን ሕዝቡን እንዲደመስስ በማዘዝ ንጉሡ ላከው። 27 ኒቃኖር ወደ ኢየሩሳሌም ብዙ ሠራዊት ይዞ ሄደ፤ ለይሁዳና ለወንድሞቹ በውሸት የሰላም ቃል ተናገረ፤ 28 “በእኔና በእናንተ መካከል ውጊያ አይሁን፤ የሰላም ንግግር ለማድረግ በጥቂት ሰዎች ታጅቤ እመጣለሁ” አለ። 29 ወደ ይሁዳ ሄደ፤ በወዳጅነት ሰላምታ ተሰጣጡ፤ ነገር ግን ጠላቶች ይሁዳን ይዘው ለመውሰድ ተዘጋጅተው ነበር። 30 ኒቃኖር ወደ እርሱ የመጣው በአታላይነት መንፈስ መሆኑን አውቆ ይሁዳ ፈራውና የሰላም ንግግሩን ለማድረግ አልፈቀደም። 31 ኒቃኖር ተንኮሉ እንደታወቀበት ተገንዝቦ ከፋርሰላም ከይሁዳ ጋር ለመዋጋት ወጣ፤ 32 በኒቃኖር በኩል አምስት መቶ ያህል ሰዎች ሞቱ፤ የቀሩት ወደ ዳዊት ከተማ ሸሽተው ሄዱ። ቤተ መቅደሱ ላይ የተሰነዘረ ዛቻ 33 ከእነዚህ ነገሮች በኋላ ኒቃኖር ወደ ጽዮን ተራራ ወጣ፤ ካህናት በሰላም እጅ ለመንሳትና ስለ ንጉሡ የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕትን ለእርሱ ለማሳየት ከሕዝብ ሽማግሌዎች ጋር ሆነው ከቤተ መቅደስ ወጡ። 34 እርሱ ግን በማላገጥ ሳቀባቸው፥ አዋረዳቸው፥ የትዕቢት ቃል ተናገራቸው። 35 እንዲህ ሲል በቁጣ ማለ፥ “አሁን በዚህ ጊዜ ይሁዳ ከነሠራዊቱ በእጄ ካልገባ እኔ አንድ ጊዜ ሰላም አድርጌ ስመለስ በዚች ግንብ ላይ እሳት እለቅባታለሁ።” ይህን ብሎ በቁጣ ወጥቶ ሄደ። 36 ካህናቱ ተመልሰው ገቡ፤ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ ፊት ቆመው እንባቸውን እያፈሰሱ እንዲህ አሉ፥ 37 አምላክ ሆይ የጸሎትና የልመና ቤት እንድትሆን፥ ስምህ በውስጧ እንዲጠራ ይህችን ግንብ የመረጥህ አንተ ነህ፤ 38 በዚህ ሰው ላይና በሠራዊቱም ላይ አንተ ተበቀል፤ በሰይፍ ተመትተው ይውደቁ፤ ስድባቸውን አስታውስ፤ ጊዜም አትስጣቸው። የኒቃኖር ቀን በአዳሳ 39 ኒቃኖር ከኢየሩሳሌም ወጣና ሰፈሩን በቤቶሮን አደረገ፤ እዚያ የሶሪያ ጦር ሠራዊት ሊተባበረው መጣለት፤ 40 ይሁዳ ከሦስት ሺህ ሰዎች ጋር ሆኖ ሰፈሩን በአሰሳ በማድረግ በዚያን ጊዜ እንዲህ ሲል ጸለየ፥ 41 “የንጉሡ መልእክተኞች በተሳደቡ ጊዜ መልአክህ መጥቶ ከእነርሱ መካከል መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰዎችን መታ፤ 42 ዛሬም እንዲሁ እኛ ፊት ይህን የጦር ሠራዊት ቀጥቅጥ፤ እርሱ ቤተ መቅደስህን መስደቡን ሌሎችም ይወቁ፤ እንደ ክፋቱ ፍረድበት።” 43 ሠራዊቶቹ በዓሥራ ሦስት አዳር (28 መጋቢት) ውጊያውን ጀመሩ፤ የኑቃኖር ሠራዊት ተመታ፤ እርሱም ራሱ በውጊያው ላይ በመጀመሪያ ተገደለ። 44 እርሱ መውደቁን ባዩ ጊዜ የኒቃኖር ወታደሮች መሣሪያቸውን ጥለው ሸሹ። 45 አይሁዳውያኑ ከአዳሳ እስከ ጋዜር ጠረፍ ድረስ የአንድ ቀን መንገድ ተከታተሏቸው፤ የሚከታተሏቸው መሆኑንም ለማመልከት መለከት ነፉ። 46 ከይሁዳ ምድር መንደሮች ዙሪያ ሁሉ እነርሱን ለመክበብና ለመውጋት ሰዎች ይወጡ ነበር፤ ሁሉም በሰይፍ ተመትተው ወደቁ፤ አንድ እንኳ አላመለጠም። 47 ከዚህ በኋላ የተዘረፉትንና የተማረኩትን ዕቃዎች ሰበሰቡ፤ የኒቃኖርን ራሱንና (ጭንቅላቱን) በትዕቢት የዘረጋውን ቀኝ እጁን ቆረጡና ወስደው በኢየሩሳሌም ሰው እንዲያያቸው አደረጉ። 48 ሕዝቡ ደስ አለው፥ ያ ቀን ታላቅ የደስታ ቀን ተብሎ ተከበረ። 49 ይህ ቀን በየዓመቱ በዓሥራ ሦስት አዳር (28 መጋቢት) እንዲከበር ተደነገገ። 50 የይሁዳ ምድር ለጥቂት ጊዜ ዕረፍት አግኝቶ እፎይ አለ። |