ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ 1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ይሁዳ በኢዱማውያንና በአሞናውያን ላይ ዘመተ 1 በአካባቢው የሚኖሩ አረማውያን ሕዝቦች መሠዊያው እንደገና መሠራቱንና ቤተ መቅደሱም ታድሶ እንደ ቀድሞው መሆኑን ሰሙ፤ 2 ስለዚህ በጣም ተቆጡና በእነርሱ መካከል የሚኖሩትን የያዕቆብ (የእስራኤል) ልጆች ለመደመሰስ ወሰኑ፤ ሕዝባችንን መግደልና ማስወጣት ጀመሩ። 3 ይሁዳ የኤሳውን ልጆች በኢዱምያስና በአቅራባቲና ወጋቸው፤ ምክንያቱም እነርሱ የእስራኤልን ሕዝብ ከበው ነበር፤ ደኀና አድርጐ መታቸውና አሸነፋቸው፤ ዕቃዎቻቸውንም ማርኮ ወሰደ። 4 ቀጥሎም የቤያንን ልጆች ክፋት አስታወሰ፤ በየመንገዱ መጥመድ በመዘርጋት ሕዝቡን በአደጋ ላይ መጣላቸውን አሰበ፤ 5 ከተማቸውን በመከበብና እንዳይፈናፈኑ በማድረግ ወጋቸው፤ አጠፋቸው፤ ምሽጐቻቸውንም በውስጦቸው ከነበሩት ሰዎች ጋር አጋያቸው። 6 ከዚህ በኋላ ወደ አሞን ልጆች አለፈ፤ እዚያም በጢሞቴዎስ ይታዘዝ የነበረ ብርቱ ሠራዊትና ብዙ ሕዝብ አገኘ። 7 ብዙ ውጊያ ካደረገ በኋላ ቀጠቀጣቸውና አሸነፋቸው፤ 8 ጋዜርንና በአካባቢዋ የነበሩትን መንደሮች ያዘ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ይሁዳ አገር ተመለሰ። ለገለዓድና ለገሊላ ዘመቻዎች የተደረገ ቅድመ ዝግጅት 9 የገለዓድ ሕዝቦች በምድራቸው የሚገኙትን እስራኤላውያንን ለማጥፋት ተባብረው ተነሡባቸው፤ እስራኤላውያን መጠጊያ ለማግኘት ወደ ድያቴማ ምሽግ ሸሹ። 10 እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ይሁዳና ወደ ወንድሞቹ ላኩ፥ “አረማውያን ሕዝቦች ሊያጠፉን ከበውናል፤ 11 እነርሱ የተጠጋንበትን ምሽግ ለመውረር በዝግጅት ላይ ናቸው፤ የሠራዊታቸው መሪ ጢሞቴዎስ ነው፤ 12 እስካሁን ድረስ ብዙ ጥፋት የደረሰብን ስለሆነ በፋጣኝ ደርሰህ ከእጃቸው አውጣን። 13 ጦቢያ አገር የነበሩ ወንድሞቻችን ሁሉ ተገድለዋል፤ ሚስቶቻቸው ተማርከው፤ ንብረቶቻቸው ተወሰዋል፤ በእነዚህ አገሮች ወደ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች አልቀዋል።” 14 ይህ መልእክት ገና በመነበብ ላይ ሳለ ሌሎች መልእክተኞች ልብሳቸውን በኀዘን ቀደው ይህንኑ የመሰለ ወሬ ይዘው ከገሊላ መጡ፤ 15 “የጰጦሌማይዳ፥ የጢሮስ የሲዶና ሰዎች በገሊላ ከሚኖሩት ከባዕድ አገር ሰዎች ጋር ሆነው እኛን ለማጥፋት ተባብረውናል”። 16 ይሁዳና ሕዝቡ ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ ስለተጨቆኑትና በውጊያ ስላሉት ወንድሞቻቸው ምን ማድረግ እንደሚገባ ለመመካከር ብዙ ሰዎችን ሰበሰቡ። 17 ይሁዳ ወንድሙን ስምዖንን፥ “ሰዎች ምረጥና በገሊላ ያሉትን ወንድሞችህን ለማውጣት ሂድ፥ እኔና ወንድሜ ዮናታን ወደ ገለዓድ እንሄዳለን” አለው። 18 የዘካሪያስን ልጅ ዮሴፍንና የሕዝቡን መሪ ዓዛርያስን ከቀረው ሠራዊት ጋር በይሁዳ አገር ተዋቸው። 19 “ሕዝቡንም አስተዳድሩ (ጠብቁ) እኛ እስክንመለስ ድረስ ከአረማውያን ውጊያ አትግጠሙ” ብሎ አዘዛቸው። 20 ለስምዖን ወደ ገሊላ የሚሄዱ ሦስት ሺህ ሰዎች ተሰጡ፤ ከይሁዳ ጋር ወደ ገሊላ የሚሄዱ ስምንት ሺህ ሰዎችም ተመረጡ። የገሊላና የገለዓድ ዘመቻ 21 ስምዖን ወደ ገሊላ ሂዶ ብዙ ውጊያ ካደረገ በኋላ አረማውያንን ጠራርጐ አጠፋቸው። 22 እስከ ጰጦሎማይዳ በር ድረስ ተከታትሎ አባረራቸው። ሦስት ሺህ ያህል አረማውያን ሞቱ፤ ዕቃዎቻችን ሁል ማረከ። 23 በገሊላና በአራባቲስ የሚኖሩትን አይሁዳውያን ከነሚስቶቻቸውና ከነልጆቻቸው፤ ከንብረታቸው ጋር በደስታ ወደ ይሁዳ አገር ወሰዳቸው። 24 ይሁዳ መቃቢስና ወንድሙ ዮናታን ዮርዳኖስን ተሻግረው ሦስት ቀን በበረሃ ተጓዙ፤ 25 በሰላም ወደ እነርሱ የመጡትን ናቦታውያንን አገኙዋቸው፤ 26 እንዲሁም ለእነርሱ ብዙዎቹ በቦዝራ፥ በአሊሜስ፥ በቃስፎር፥ በማቄድ፥ በቃርኔን በእነዚህ ታላላቅ ከተሞችና ምሽጐች ውስጥ መከባባቸውን ነገሩዋቸው፤ 27 በገለዓድ፥ በሌሎች ከተሞችም ውስጥ ተዘግተው የሚገኙ እንዳሉ፥ ጠላቶቻቸውም በሚቀጥለው ቀን ምሽጐቹን ወግተው ለመያዝና እዚያ የሚገኙትን ሁሉ ባንድ ቀን ለማጥፋት እንደወሰኑ አወሩላቸው። 28 ይሁዳና ሠራዊቱ ቶሎ ብለው ወደ ቦዝራ በረሃ አመሩ፤ ከተማዋን ያዙ፤ ወንዶቹን ሁሉ በሰይፍ ገደሉ፤ ምርኮውን ሁሉ ወሰዱ፤ ከተማዋንም አቃጠሉ። 29 በሌሊት ሄዱ፥ እስከ ምሽጉ አጠገብ ድረስ ተጓዙ። 30 በነጋ ጊዜ ቀና ብለው ሲመለከቱ ከተማዋን ለመያዝ መሰላሎችንና የጦር ተሽከርካሪያዎች የሚያዘጋጁ ቍጥር ስፍር የሌላቸው ብዙ ወታደሮችን አዩ፤ ውጊያውም ተጀምሮ ነበር። 31 ይሁዳ ውጊያው መጀመሩንና መለከቱንና የጦርነት ዋይታ ከመለከቱ ድምፅ ጋር እና ከብጥብጡ ጋር ወደ ሰማይ መድረሱን አይቶ 32 ለሠራዊቱ እንዲህ አለ፤ “ዛሬ ስለ ወንድሞቻችን ተዋጉ”። 33 ሠራዊቱን በሦስት ክፍል ከፋፍሎ ከጠላት በስተ ኋላ በኩል እንዲሄድ አደረገ፤ ያንጊዜ መለከት ተነፋ ከፍ ባለም ድምፅ ጸሎቱ ቀጠለ። 34 የጢሞቴዎስ ሠራዊት ይሁዳ መቃቢስ መሆኑን አውቆ ካጠገቡ ሸሸ፤ ይሁዳም ሙሉ ለሙሉ ደመሰሳቸው፤ በዚያን ቀን በውጊያ ላይ የሞቱት ሰዎች ስምንት ሺህ ያህል ናቸው። 35 ከዚህ በኋላ ፊቱን ወደ አሌማ መለሰና ወጋት፥ ያዛት፥ ወንዶቹን በሙሉ ገደለ፥ ምርኮውን ሰበሰበ፥ ከተማዋን አቃጠለ። 36 ከዚያም ቃስፎን፥ በቄድን፥ በሶርነና ሌሎችንም የገለዓድ ከተሞች ለመያዝ ሄደ። 37 ይህ ነገር ከሆነ በኋላ ጢሞቴዎስ ሌላ ጦር ሠራዊት ሰብስቦ ከወንዝ ወዲያ ማዶ በራፎን ፊት ለፊት ተሰለፈ። 38 ዓረቦችም ጦሩን ለማሟላት ከባድ ሠራዊት ሆነው በጢሞቴዎስ ዙሪያ ተሰብስበዋል፤ 39 ዓረቦችም ጦሩን ለማሟላት ተቀጥረዋል፤ ውጊያ ሊገጥሙህ ተዘጋጅተው ከወንዙ ወዲያ ማዶ ሰፍረዋል። ይሁዳ ውጊያ ሊገጥማቸው ወደ እነርሱ ሄደ፤ 40 ከሠራዊቱ ጋር ሆኖ ወደ ውሃው (ወንዙ) ተጠጋ፤ ጢሞቴዎስም፤ “እርሱ ቀድሞን ወዲህ የተሻገረብን እንደሆነ ልንቋቋመው አንችልም፤ ምክንያቱም ከተሻገረ ከእኛ ይበልጥ እርሱ ጥቅም ያገኝበታል። 41 ነገር ግን ከፈራና ከወንዙ ወዲያ ማዶ ከሰፈረ እኛ እንሻገረና እናሸንፈዋለን” አለ። 42 ይሁዳ በወንዙ ውሃ አጠገብ በደረሰ ጊዜ በወንዙ ዳር የሕዝቡ ጸሐፊዎችን አቁሞ፥ “ሁሉም ወደ ውጊያ ይሂድ እንጂ ማንም እዚህ እንዲሰፍር አታድርጉ” ብሎ ትእዛዝ ሰጣቸው። 43 እርሱ ቀድሞ ተሻገረና ወደ ጠላት ሄደ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተከተሉት። አረማውያንን ቀጠቀጣቸው፤ እነርሱ የጦር መሣሪያዎቻቸውን ጥለው ወደ ቃርኔን ቤተ መቅደስ ሸሽተው ሄዱ። 44 የይሁዳ አገር ሰዎች አስቀድመው ከተማዋን ያዙ፤ በኋላም ቤተ መቅደሳቸውንና እዚያ ያሉትን በእሳት አጋዩ። ቃርኔን ወደመች፤ ከዚያ በኋላ ይሁዳን መቋቋም አልተቻለም። 45 ይሁዳ በገለዓድ የተገኙትን እስራኤላውያንን ትልቁንም ትንሹንም በሙሉ ከነሚስቶቻቸው፤ ከነልጆቻቸው፤ ከነንብረቶቻቸው በአንድነት ሰበሰባቸው፤ በጣም ብዙ ሕዝብ ነበረ፤ ሁሉም ወደ ይሁዳ አገር እንዲሄዱ ተደረገ። 46 በመንገዳቸው ላይ ወደምትገኘው ታላቅና ብርቱ ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ኤፌሮን ደረሱ፤ ይህችን ከተማ በመካከሏ ማለፍ ካልሆነ በቀር ወደ ቀኝ ወይ ወደ ግራ ዞሮ ማለፍ አይቻልም ነበር። 47 የከተማይቱ ሰዎች ማለፍ ከለከሏቸው፤ በሮቹንም በቋጥኝ ድንጋዮች ጥርቅም አድርገው ዘጉ። 48 ይሁዳም፤ “በሀገራችሁ በኩል አልፈን ወደ ሀገራችን የምንሄድ ነን፤ ማንም ክፉ አያደርግባችሁም፤ የምንፈልገው በእግራችን ብቻ ማለፍ ነው።” ሲል የሰላም ቃል ወደ እነርሱ ላከ፤ እነርሱ ግን አንከፈትልህም አሉት። 49 በዚያን ጊዜ ይሁዳ ለሠራዊቱ፤ “በያለህበት እርጋ” የሚል ትእዛዝ አስተላለፈ። 50 ወታደሮቹ ቦታ ቦታቸውን ያዙ፤ ይሁዳ ያን ቀን በሙሉና ሌሊቱንም በሙሉ ከተማዋን ወጋት፤ ከተማዋ በእጃቸው ወደቀች፤ 51 ወንዶቹን በሙሉ በሰይፍ ገደላቸው፤ ከተማዋን ባድማ አደረጋት፤ ዕቃዎችን ማርኮ በተገደሉት ሰዎች ሬሳ ላይ አልፎ ሄደ። 52 ከዚያም ዮርዳኖስን በመሻገር በቤትሳን ፊት ለፊት ወዳለው ታላቁ ሜዳ ተሻገሩ፤ 53 ዮርዳኖስን የቀሩትን እያሰባሰበ፤ በመንገድ ያሉትን ሕዝብ እያበረታታ ወደ ይሁዳ ምድር እስኪደርስ ድረስ ወዲያ ወዲህ ይል ነበር። 54 በደስታ ተሞልተው የጽዮንን ተራራ ወጡ፤ አንድም ሰው ሳይሞትባቸው በሰላም ስለ ተመለሱ የሚቃጠሉ ምሥዋዕቶችን አቀረቡ። ውድቀት በያምንያ 55 ይሁዳና ዮናታን በገልዓድ አገር ወንድሙ ስምዖን በጰጦሎማይዳ ፊት ለፊት በገሊላ በሚገኙበት ጊዜ 56 የጦር ሹማምንቱ የዘካርያስ ልጅ ዮሴፍና አዛርያ የእነርሱን ጀግንነትና ያደረጓቸውንም ውጊያዎች ሰሙና 57 “እኛም ዝናን እናትርፍ፤ እንሂድና በአካባቢያችን ያሉትን አረማውያን ሕዝቦች እንውጋ” ተባባሉ። 58 ከነርሱም ጋራ ለነበረው ሠራዊት ሁሉ ትእዛዝ በመስጠት በጃኔያ ከተማዎች ላይ ሰፈሩ። 59 ጐርጊያስ ውጊያ ሊገጥማቸው ከወታደሮቹ ጋር ሆኖ ከከተማ ወጣ። 60 ዮሴፍና ዓዛርያስ ተሸነፉና እስከ ይሁዳ ምድር ዳርቻ ድረስ ተባረሩ። በዚያን ቀን ከእስራኤል ሕዝብ ሁለት ሺህ ያህል ሰዎች ሞቱ። 61 የጀግንነት ሥራ የሚሠሩ መስሏቸው ይሁዳንና ወንድሞቹን ስላልሰሙ የእስራኤል ሕዝብ ሽንፈት ደረሰበት። 62 ነገር ግን እነርሱ እስራኤልን ለማዳን ኃላፊነት የተጣለባቸው ሰዎች ዓይነት አልነበሩም። በኤዶሚያንና በፍልስጥኤም የተገኙ ድሎች 63 ጀግናው ይሁዳና ወንድሞቹ በእስራኤል ዘንድና ስማቸው ሲነገር በተሰማበት በአረማውያን ሕዝቦችም ዘንድ ታላቅ ክብር አግኝተዋል። 64 ሰው ሁሉ እነርሱን ለማመስገን በዙሪያቸው ይረባረብ ነበር። 65 ይሁዳ ከወንድሞቹ ጋር ሆኖ በደቡብ አውራጃ ከዔሳው ልጆች (ኤዱማውያን) ጋር ለመዋጋት ሄደ፤ ሔብሮንና መንደሮችዋን ያዘ፤ ምሽጐቿን አፈረሰ፥ የመካበቢያውን ረጃጅም ግንቦች በእሳት አጋየ። 66 ከዚህ በኋላ ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር መጓዝ ጀመረ፤ በማሪባ በኩል አልፎ ሄደ። 67 በዚያን ቀን ወደ ውጊያ በመሄድ ጉብዝናቸውን ለማሳየት የፈለጉ ካህናት በውጊያው ላይ ሞቱ፤ 68 ቀጥሎም ይሁዳ የፍልስጥኤማውያን አገር ወደ ሆነችው ወደ አዞጦን ተመለሰ፤ መሠዊያዎቻቸውን ገለባበጠ፤ የጣዖቶቻቸውን የተቀረጹ ምስሎች አቃጠለ፤ የከተማዎቹን የምርኮ ዕቃዎች ወሰደ፤ ወደ ይሁዳ ምድር ተመለሰ። |