Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የኤማሁስ ጦርነት

1 ጐርጊያስ አምስት ሺህ እግረኞችና አንድ ሺህ ምርጥ ፈረሰኞች ይዞ በሌሊት ሄደ፤

2 ይህን ማድረጉም በአይሁዳውያን ሠፈር በድንገት ደርሶ በእነርሱ ላይ ድንገተኛ አደጋ ለመጣል ነው። የኢየሩሳሌም ምሽግ ሰዎች የሱ መሪዎች ሆነው ያገለግሉት ነበር።

3 ይሁዳ ወሬውን አስቀድሞ በመስማቱ በኤማሁስ የነበረውን የንጉሡን ጦር ሠራዊት ለመውጋት ከጀግኖቹ ጋር ሆኖ ሄደ፤

4 በዚያን ጊዜ የጐርጊያስ ሰዎች ከሠፈር ውጪ ተበታትነው ይገኙ ነበር።

5 ጐርጊያስ ወደ ይሁዳ ሠፈር ሌሊት ደረሰ፤ እዚያ ማንንም ሳያገኝ ቀርቶ፥ “ሸሽተውን ሄደዋል” ብሎ አይሁዳውያንን በተራራዎቹ ላይ ይፈልግ ጀመር።

6 በነጋ ጊዜ ይሁዳ ከአምስት ሺህ ሰዎች ጋር በማዳው ላይ ታየ፤ ግን ሰዎቹ ያስፈልጓቸው የነበሩትን የጦር መሣሪያዎችና ሰይፎች አልያዙም ነበር።

7 ያንጊዜ ካሉበት ስፍራ ሆነው የተጠናከረውንና የመሸገውን የአረማውያንን ሠፈር ተመለከቱ፤ በሠፈሩ ዙሪያ ፈረሰኞች ነበሩ፤ ሁሉም ዓዋቂዎችና የጦር ልምምድ ያላቸው ነበሩ።

8 ይሁዳ ሰዎቹ እንዲህ አላቸው፥ “ብዛታቸውን በማየት አትፈሩ፤ በውጊያቸውም አትደንግጡ፤

9 ፈርዖን የጦር ሠራዊቱን ይዞ አባቶቻችንን ሲያሳድድ እነርሱ በቀይ ባሕር ላይ እንዴት እንደዳኑ አስታውሱ፤

10 አሁንም ወደ ሰማይ እንጩህ፤ የሚያስብልን ከሆነ ለአባቶቻችን የገባላቸውን ቃል ኪዳን ያስታውሳል፤ ያንን ሠራዊትም ዛሬ በፊታችን ይደመስሰዋል፤

11 አረማውያን ሕዝቦች ሁሉ እስራኤልን የሚታደግና የሚያድን መኖሩን ያውቃሉ።”

12 እነዚያ የባዕድ አገር ሰዎች ቀና ብለው የአይሁዳውያንን ወደ እነርሱ መምጣት አዩ፤

13 ጦርነት ለመግጠም ከሠፈራቸው ወጡ፤ የይሁዳ ሰዎች መለከት ነፉ፤

14 ጦርነትም ገጠሙ። አረማውያን ሕዝቦች ተሸነፉ፤ ወደ ሜዳውም ሸሹ።

15 ነገር ግን በስተ ኋላ የነበሩት ሁሉ በሰይፍ ተመትተው ወደቁ። እስከ ጌዜሮንና እስከ ኤዶምያስ ሜዳ ድረስ፥ እስከ አዛጦንና እስከ ያምንያ ድረስ ተከታተሏቸው፤ ጠላት ሦስት ሺህ የሚያህሉ ሰዎች በዚያ አጣ።

16 ይሁዳ ከወታደሮቹ ጋር ጠላቶቹን ከማሳደድ ተግባሩ ተመልሶ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ተናገረ፥

17 “ሌላ ጦርነት ስለሚጠብቀን አሁን ለምርኮ አትቸኩሉ፤

18 ጐርጊያስና ወታደሮቹ በተራራው ላይ በአጠገባችን ናቸው፤ ጠላቶቻችንን ተቋቋሟቸው፤ ውጓቸው፤ ከዚህ በኋላ ምርኳችሁን ያለ ስጋት መሰብሰብ ትችላላችሁ”።

19 ይህን ብሎ እንዳበቃም የጠላት ወታደሮች በተራራው ጫፍ ላይ ሆነው በመሰለል ላይ ሳሉ ታዩ።

20 የእነርሱ ወታደሮች መሸነፋቸውንና ሰፈራቸውም በመቃጠል ላይ መሆኑን ተመለከቱ፤ የሚታየውም ጭስ የሆነውን ነገር በግልጽ ያስረዳ ነበር።

21 ይህን ባዩ ጊዜ በፍርሃት ተዋጡ፤ እንዲሁም ለውጊያ የተዘጋጁትን የይሁዳን ጦር ሠራዊት በሜዳው ላይ አዩና

22 ሁሉም ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ሸሹ።

23 ከዚህ በኋላ ይሁዳ ሠፈራቸውን ለመዝረፍ ተመልሶ መጣ፤ ብዙ ወርና ብር፥ ሐሞራዊ ከፋይና ቀይ ጨርቆች እንዲሁም ብዙ ሀብቶችን ወሰደ።

24 በመልሱም ጉዞ ላይ፥ “እግዚአብሔር ደግና ፍቅሩም ዘላለማዊ ነው እያሉ የምስጋና መዝሙር በማቅረብ ተመለሱ”።

25 ያ ቀን በእስራኤል ትልቅ የነጻነት ቀን ሆነ።

26 እነዚያ ሸሽተው ያመለጡ የባዕድ አገር ሰዎች ወደ ሊስያስ መጥተው የሆነውን ነገር ሁሉ አወሩለት።፥

27 ይህ ወሬ በጣም አስደነገጠው፤ ፍርሃትም አሳደረበት፤ ምክንያቱም የእስራኤል ጉዳይ እርሱ እንዳሰበው አልተፈጸመለትም፤ ውጤቱም የንጉሡን ትእዛዝ የሚቃወም ሆኖ ተገኘ።


የመጀመሪያው የሊስያስ ዘመቻ

28 ቀጥሎም ባለው ዓመት አይሁዳውያንን ለመውጋት ሥልሳ ሺህ ምርጥ እግረኞችንና አምስት ሺህ ፈረሰኞችን ሰበሰበ።

29 ወደ ኤዶምያስ ሄደው በቤተሱር ሰፈሩ፤ ይሁዳ ሊገጥማቸው ዐሥር ሺህ ሰው ይዞ ሄደ።

30 ይህን ከባድ ሠራዊት ባየ ጊዜም እንዲህ ብሎ ጸለየ “የእስራኤል አዳኝ ሆይ አንተ የተመሰገነህ ነህ፤ በአገልጋይህ በዳዊት እጅ የኃይለኛውን ተዋጊ ሰው ኃይል ያንኮታኮትህ ነህ፤

31 እንዲሁም አሁን ይህን ሠራዊት በሕዝብህ በእስራኤል እጅ አጥፋው፤ በእግረኛ ጦራቸውና በፈረሰኛ ጦራቸው ይፈሩ፤

32 ፍርሃትን አሳድርባቸው፤ እፍረተ ቢሱን ጦራቸውን አቅልጠው፤ ድል ተነሥተው ይንቀጥቀጡ፤

33 በሚወዱህ ሰዎች ሰይፍ ላይ ጣላቸው፤ ስምህን የማያውቁ ሰዎች ሁሉ በመዝሙር ያመስግኑህ”።

34 ውግያው ተጀመረና በጨበጣ ውግያ ከሊስያስ ጦር ሠራዊት አምስት ሺህ ሰዎች ያህል ሞቱበት።

35 የሠራዊቱን ሽንፈትና የይሁዳ ሠራዊትን ድፍረት ባየ ጊዜ፥ እንዲሁም የይሁዳ ወታደሮች ለመኖር ወይም በጀግንነት ለመሞት ምን ያህል ዝግጁዎች መሆናቸውን ባየ ጊዜ ሊስያስ የባዕድ አገር ወታደሮችን ለመሰብሰብና ተጠናክሮ ወደ ይሁዳ አገር ተመልሶ ለመመጣት ወደ አንጾኪያ ሄደ።


የቤተ መቅደስ መንጻትና ዳግም መቀደስ

36 ይሁዳና ወንድሞቹ፥ “እነሆ ጠላቶቻችን ተሸንፈዋል፤ እንሂድና ቤተ መቅደሱን እናንጻ፥ እናክብረው” አሉ።

37 ሠራዊቱ ሁሉ ተሰበሰቡና ወደ ጽዮን ተራራ ላይ ወጡ።

38 ቤተ መቅደሱ ባዶ ሆኖ፥ መሠዊያው ረክሶ፥ መዝጊያዎቹ ተቃጥለው አዩ፤ በግቢው ውስጥ የበቀለው ሣርና ቅጠሉ በጫካ ውስጥ ወይም በተራራ ላይ እንደሚታየው ዓይነት ነበር፤ መጋዘኖቹም ፈራርሰዋል።

39 በኀዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ታላቅ ኀዘን አደረጉ፥ ራሳቸው ላይ አመድ ነሰነሱ።

40 በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ፥ መለከቱ በተነፋ ጊዜ ወደ ሰማይ ጮኹ።

41 ቤተ መቅደሱ ንጹሕ እስኪሆን ድረስ በከተማዋ ምሽግ ውስጥ ያሉትን ሰዎች እንዲዋጉ ይሁዳ ከእርሱ ሰዎች እንዳንዶቹን ጠርቶ አዘዛቸው፥

42 ከዚህ በኋላ ያልረከሱትንና የሙሴን ሕግ የሚያፈቅሩትን ካህናት መረጠ፤

43 እነርሱ ቤተ መቅደሱን አነጹ፤ የረከሱትን ደንጊያዎችን በቆሻሻ ቦታ ጣሏቸው።

44 የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ይሠውበት የነበረውን የረከሰውን መሠዊያ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ተጠያየቁ፤

45 አረማውያን አርክሰውት ስለ ነበረ ውርደት እንዳይሆንባቸው ፈርተው ለማፍረስ አሰቡ፤ ስለዚህ አፈረሱት፤

46 ስለ ድንጋዮቹ ነቢይ መጥቶ ምን ማድረግ እንደሚገባ እስኪናገር በደኀና ቦታ ከቤተ መቅደሱ በላይ በሚገኘው ከረብታ ላይ አስቀመጧቸው፤

47 በሙሴ ሕግ መሠረት ያልተጠረቡ ድንጋዮች አምጥተው እንደ በፊቱ ዓይነት አድርገው አዲስ መሠዊያ ሠሩ።

48 የቤተ መቅደሱን ውጭውንና ውስጡን አደሱት፤ ግቢውን ቀደሱት፤

49 አዳዲስ የተቀደሱ ዕቃዎችን ሠርተው በቤተ መቅደሱ ውስጥ መቅረዙን፥ የዕጣን ማጨሻውን፥ ጠረጴዛውን አስገቡ።

50 በመሠዊያው ላይ ዕጣን አጨሱ፤ በመቅደሱ ውስጥ ብርሃን የሚሰጡትን የመቅረዙን መብራቶች ዘረጉና አበሩ።

51 በጠረጴዛው ላይ ኀብስት አስቀመጡ፤ መጋረጃዎቹን ዘረጉ፤ ሥራዎቹንም ሁሉ ፈጸሙ።

52 ቂስለው በሚባለው በዘጠነኛው ወር በሃያ አምስት (ታኀሣሥ 14 በመቶ አርባ ስምንት ዓመት) ጎህ ሲቀድ ተነሡ፤

53 የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች በሚቀርቡበት ቦታ እነርሱ በሠሩት በዲሱ መሠዉያ ላይ በሙሴ ሕግ መሠረት መሥዋዕት አቀረቡ።

54 በዚያው አረማውያን ባረከሱበት ዓመትና ዕለት መሠዊያው በመዝሙር፥ በበገና፥ በክራር፥ በጸናጽል ተመረቀ።፥

55 ሕዝቡ ሁሉ ለመስገድ በግንባሩ ተደፋ፤ ወደ ድል ለመራቸው አምላክም ምስጋና አቀረቡ።

56 የመሠዊያውን ምረቃ በዓል ስምንት ቀን አከበሩ፤ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን፥ የአንድነትና የምስጋና መሥዋዕቶችንም በታላቅ ደስታ አቀረቡ።

57 የቤተ መቅደሱን ፊት በር በወርቅ አክሊሎችና ጋሻዎች አጌጡት መግቢያዎቹንና ቤቶቹን አደሷቸው፤ መዝጊያዎችም አደረጉላቸው።

58 በሕዝቡ መካከል ታላቅ ደስታ ሆነ፤ ከአረማውያን የመጣባቸው ውርደት ተደመሰሰ።

59 ይሁዳና ወንድሞቹ፤ የእስራኤልም ሕዝቡ በሙሉ በሃያ አምስት በቂስለው ወር ጀምሮ ስምንት ቀን ሙሉ በየዓመቱ በእነርሱ ጊዜ የመሠዊያው ምረቃ ቀኖች በታላቅ ደስታ እንዲከበሩ ወሰኑ።

60 እንደ ቀድሞው አረማውያን መጥተው እነዚህን ቦታዎች እንዳይበዘብዙ በዚያን ጊዜ ከፍተኛ መካበቢያዎችና የግንብ ምሽጐች በጽዮን ተራራ ዙሪያ ሠሩ።

61 ይሁዳም ጠባቂ ወታደሮችን አሠማራ። በኤዶምያስ በኩል ሕዝቡም ምሽግ እንዲኖረው ቤተሱርን አጠናከረ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች