ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ 1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የአይሁድ መሪ ይሁዳ መቃቢስ የይሁዳ መቃቢስ ሙሾ 1 መቃቢስ የተባለው ልጁ ይሁዳ በእርሱ ቦታ ተተካ (ተነሣ)። 2 ወንድሞቹ የአባቱ ተከታዮች ሁሉ ረዱት፤ ስለ እስራኤል በደስታ ተዋጉ። 3 የሕዝቡን ክቡርና ዝና አስፋፋ፤ ታላቅ ጀግና ሆኖ የጦር ልብስ ለበሰ፤ የጦር መሣሪያዎቹን ታጠቀ፤ ጦርነት ገጠመ። 4 በአደን ላይ እንዳለ አንበሳ ሆነ፤ በምግቡና በግዳዩም ላይ ማግሳት ጀመረ፤ 5 ክፉዎቹን እያሳደደ አባረራቸው፤ በሕዝቡ ላይ በደል የፈጸሙትን ሁሉ በእሳት አቃጠላቸው። 6 ክፉዎቹ የእርሱ ፍራት አደረባቸው፤ ክፉ አድራጊዎች ሁሉ በፍራት ተንቀጠቀጡ፤ በእርሱ እጅ ነፃነት ተገኘ። 7 የብዙዎችን ነገሥታት ሕይወት መራር አደረገባቸው፤ የእርሱ ሥራዎች ያዕቆብን (እስራኤልን) አስደሰቱ፤ መታሰቢያውም ለዘለዓለም ይመሰገናል። 8 የይሁዳን ከተሞች አረሳቸው፤ አረማውያንንም ፈጃቸው፤ መዓትን ከእስራኤል አራቀ። 9 እስከ ምድር ዳርቻ ዝናው ተሰማ፤ ጠፍተው የነበሩትን ሁሉ ሰበሰበ። የመጀመሪያዎቹ የይሁዳ ድሎች 10 አጰሎንዮስ (የንጉሡ ሹም) እስራኤልን ለመውጋት አረማውያንና ብዙ የሰማሪያ ሰዎችን ሰበሰበ። 11 ይሁዳ ጉዳዩ ተነገረውና ጦርነት ሊገጥመው ወጣ፤ ተዋጋውና ገደለው፤ ብዙዎች ሞተው ወደቁ፤ የቀሩት ሸሹ። 12 ምርኮዎቻቸው ተሰበሰቡ፤ ይሁዳ የአጰሎንዮስን ሰይፍ ወሰደ፤ በሕይወቱ ሙሉ በየጦርነቱ ላይ ተገለገለበት። 13 የሦርያ የጦር አዛዥ ሴሮን ይሁዳ የጦር ሰዎችንና ታማኞች ሰዎችን እንዳከማቸ ሰማ፤ 14 እንዲህም አለ፤ “እኔ ዝና አተርፋለሁ፤ በዚህ መንግሥትም ክብር አገኛለሁ፤ የንጉሡን ትእዛዝ ንቀው አንታዘዝም ያሉትን ይሁዳንና ሰዎቹን እወጋቸዋለሁ”። 15 ስለዚህ በተራው እርሱም ዘመተ፤ ከእርሱም ጋር ብዙ አረማውያን ወታደሮች በእስራኤል ላይ በቀላቸውን ሊወጡ አብረውት ዘመቱ። 16 ወደ ሴቶሮን አቀበት ቀረበ፤ ይሁዳም ከጥቂት ሰዎች ጋር ሆኖ ጦርነት ሊገጥመው ወጣ። 17 ሰዎቹ ጦርነት ሊገጥማቸው የሚመጣውን የጦር ሠራዊት ባዩ ጊዜ ይሁዳን፥ “እኛ በቍጥር ጥቂቶች ነን፤ ታዲያ ከኛ በጣም ከሚበዙት ሰዎች ጋር መዋጋት እንዴት እንችላለን? ዛሬ ምንም ሳንበላ ነው የዋልነው ደክሞናል” አሉት። 18 ይሁዳ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፥ “የብዙ ሰዎች በጥቂት ሰዎች እጅ መውደቅ እኮ በአምላክ ዐይን አስቸጋሪ አይደለም፤ 19 በጦርነት ድል መንሣት የሚገኘው ከሠራዊት ብዛት ሳይሆን ከእግዚአብሔር በሚመጣው ኃይል ነው። 20 እነርሱ እኛንና ሚስቶቻችንን፥ ልጆቻችንን ለመደመሰስና ለመዝረፍ ወደ እኛ የሚመጡት በትዕቢትና በክፋት ተወጥረው ነው፤ 21 እኛ ግን የምንዋጋው ስለ ሕይወታችንና ስለ ሕጋችን ብለን ነው፤ 22 እርሱ አምላካችን በፊታችን ይሰባብራቸዋል፤ እናንተ እንግዲህ አትፍሩዋቸው”። 23 ወዲያውኑ ንግግሩን እንደጨረሰ በድንገት አደጋ ጣለባቸው፤ ሴሮንና የጦር ሠራዊቱ በፊቱ ተሸነፉ፤ 24 በቤቶሮን ቁልቁለት እስከ ሜዳው ድረስ ተከታትለው ወጉዋቸው፤ ስምንት መቶ ሰዎች ያህል ሞቱ፤ የቀሩት ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ሸሹ። 25 ይሁዳና ወንድሞቹ በዙሪያቸው ያሉትን አረማውያን ሕዝቦችን ማስፈራራትና ማንቀጥቀጥ ጀመሩ። 26 የይሁዳ ዝና እስከ ንጉሡ ደረሰ፤ ሕዝብ ሁሉ ይሁዳ ስላደረገው ጦርነት ይናገር ነበር። በፋርስና በይሁዳ ወረራ የአንጥዮኩስ ዝግጅት፥ የሊስያስ ውክልና 27 እነዚህን ነገሮች በሰማ ጊዜ ንጉሠ አንጥዮኩስ በጣሙን ተቆጣ፤ የመንግሥቱን ወታደሮች በሙሉ ሰብስባ እጅግ ከባድ የጦር ሠራዊት አዘጋጀ። 28 የሀብት ግምጃ ቤቱንም ከፍቶ ለሠራዊቱ የዓመት ደሞዛቸውን አደላቸው፤ በተጨማሪም ለድንገተኛ ንቅናቄ ተዘጋጅተው እንዲጠባበቁ ተነገራቸው። 29 በዚያን ጊዜ በሣጥኖቹ ውስጥ ገንዘብ እንዳልነበረና የክፍለ ሀገሩም የግብር ገቢ በቂ እንዳልነበረ አየ፤ ይህ የገንዘብ መጉደል የመጣው ከጥንት ጀምሮ ሁልጊዜ የነበሩት ሕጐች በመፍረሳቸው በአገሩ ውስጥ መከራና ብጥብጥ በመነሣቱ ምክንያት ነው። 30 ከእርሱ በፊት ከነበሩት ነገሠታት ይበልጥ ቀድሞ በለጋስነት የሚያደርገውን ወጪና ልግስና ለማድረግ አለመቻሉን በመገንዘብ ፈራ፥ 31 ጭንቀት ያዘው፤ ስለዚህ ከክፍለሀገሮች ግብር ለማስፈከልና ብዙ ገንዘብ ለመሰብሰብ ፋርስን ለመውረር ወሰነ። 32 ከንጉሥ ጋር ዝምድና ያለውንና ክቡር ሰው የሆነውን ሊስያስን ከኤፈራጥስ እስከ ምስር ድንበሮች ድረስ ያሉትን ንጉሣዊ ጉዳዮች እንዲያከናውን ሾመና እዚያው ተወው። 33 የልጁን የአንጥዮኩስን አስተደደግና ትምህርት ንጉሡ እስኪመለስ ድረስ እንዲከታተል ኃላፊነት ተሠጠው። 34 ከሠራዊቱ እኩሌታውን ክፍልና ዝሆኖችን አስረከበው፤ ሰለውሳኔዎቹም አስፈላጊ ምክሮችን ለገሠው፤ በተለይም ስለ ይሁዳ አገርና ሰለ ኢየሩሳሌም ነዋሪዎች አስታወቀው። 35 የእስራኤልን ኃይልና በኢየሩሳሌም ጥቂት የቀሩትንም ለመደምሰስና በዚያ ቦታ ላይ ያላቸውን ትውስታቸውን ለማጥፋት ወደ እነርሱ የጦር ሠራዊቱን መላክ እንደሚገባው ነገረው፤ 36 በመላው አገራቸው ላይ የባዕድ አገር ሰዎችን ማስቀመጥና አገራቸውንም በዕጣ ማከፋፈል እንደሚገባ አስታወቀው። 37 ንጉሡ ቀሪውን የወታደሮቹን ክፍል ይዞ በመቶ አርባ ሰባት ዓመተ ዓለም የመንግሥቱ መናገሻ ከተማ ከሆነችው ክፍል ይዞ በመቶ አርባ ሰባት ዓመተ ዓለም የመንግሥቱ መናገሻ ከተማ ከሆነችው አንጾኪያ ተነሣ፤ ኤፍራጥስን ተሻግሮ በላይኛዎቹ ክፍለ ሀገሮች አድርጐ አለፈ። ኒቃኖርና ጐርጊያስ የሶሪያን ጦር ወደ ይሁዳ አዘመቱ 38 ሊስያስ ከንጉሡ ወዳጆች መካከል ብርቱዎች የሆኑትን የዶራሜን ልጅ ጰጠሎሜዎስን፥ ኒቃኖርን፥ ጐርጊያስን መረጠ፤ 39 ወደ ይሁዳም አገር እንዲሄድና በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት አገሩን እንዲያጠፉ አርባ ሺህ እግረኞችንና ሰባት ሽህ ፈረሰኞችን ከእነርሱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር ላከ። 40 እነርሱ ከጦር ሠራዊታቸው ሁሉ ጋር ሄደው ወደ አማሁስ አጠገብ ደረሱና ሠፈራቸውን በሜዳው ላይ አደረጉ፤ 41 የእዚያ አገር ነጋዴዎች ዝናቸውን ሰምተው ብዙ ወርቅና ብር፥ እግር ብረቶችም ይዘው መጡ፤ የእስራኤልን ሰዎች እንደ ባርያ ገዝተዋቸው ለመውሰድ ወደ ሰፈሩ ሄዱ። የሦርያ (የኢዶምያስ) ወታደሮችና የፍልስጥኤማውያን አገር ወታደሮችም ከእነርሱ ጋር ተባበሩ። 42 ይሁዳና ወንድሞቹ መከራቸው እየከበደ እንደሄደና በምድራቸው ላይ የጦር ሠራዊቶች እንደሰፈሩ አዩ። ሕዝቡን ጠራርጐ ማጥፋት ነው ያለውን የንጉሡንም ውሳኔ አወቁ። 43 “ሕዝባችንን ከጥፋቱ እናውጣው፤ ስለ ሕዝባችንና ስለ ቅዱስ ቦታችን እንዋጋ” ተባባሉ። 44 ለጦርነት ለመዘጋጀት በመጸለይ የእግዚአብሔርን ርኀራኄና ምሕረት ለመለመን ሕዝቡን ሰበሰቡ። 45 ኢየሩሳሌም ባዶዋን ቀርታ ነበር፤ ከልጆችዋ ማንም የሚገባና የሚወጣ አልነበረም፤ ቤተ መቅደሱ ተበዝብዞ ነበር፤ አረመኔ ገብቶበታል፥ በያዕቆብ (በእስራኤል) እልልታዎች ተወግደዋል፤ ዋሽንትና ክራር አይሰሙበትም። በምጽጳ የአይሁዳውያን መሰባሰብ 46 ተሰብስበው በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ወደሚገኘው ወደ ምጽጳ ወጡ፤ ምክንያቱም ቀድሞ እስራኤላውያን የጸሎት ቦታ ነበራቸውና። 47 በዚያን ቀን ጾሙ፥ ያደፈ ልብስ ለበሱ፥ ራሳቸው ላይ አመድ ነሰነሱ፥ ልብሳቸውን ቀደዱ፥ 48 መቼም አረማውያን ወደ ጣዕቶቻቸው ምስሎች ይጸልያሉ፤ እስራኤላውያን ግን ለማንበብ የሙሴን ሕግ መጽሐፍ ከፈቱ፤ 49 የካህናት አልባሳትን የመጀመሪያ ምርቶችን ዓሥራቶችን አመጡ፤ የስለታቸውን ቀን የፈጸሙትን ናዝራውያንንም አመጡ። 50 ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ወደ ሰማይ እንዲህ አሉ፥ “እነዚህን ሰዎች ምን እናድርጋቸው? ወዴትስ እንውሰዳቸው? 51 ቅዱስ ቦታህን በዝብዘውታል፥ አርክሰውታል፥ ካህናትህ በኀዘንና በውርደት ላይ ናቸው። 52 እነሆ አረማውያን ሕዝቦች እኛን ለማጥፋት ተስማምተውብናል፤ እነርሱ በእኛ ላይ የሚያቅዱትን ሁሉ አንተ ታውቃለህ፤ 53 አንተ ካልረዳኸን እንዴት አድርገን ልንቋቋማቸው እንችላለን?” 54 ቀጥሎም መለከት በመንፋት ታላቅ ድምፅ አሰሙ። 55 ከዚህ በኋላ ይሁዳ ሕዝቡን የሚመሩ የሺህ አለቆችን፥ የመቶ አለቆችን፥ የሃምሳ አለቆችን፥ የዐሥር አለቆችን ሾመ። 56 ቤታቸውን የሚሠሩትን ወይም ለማግባት የታጩትን በቅርብ ወይን የተከሉትን ወይም ፍርሃት ያደረባቸውን በሕጉ መሠረት ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ነገራቸው። 57 በዚያን ጊዜ የጦር ሠራዊቱ መሄድ ጀመረና በአማሁስ በስተ ደቡብ ሰፈረ። 58 ይሁዳ እንዲህ አላቸው፥ “ተዘጋጁ ጀግኖች ሁኑ፥ እኛንና መቅደሳችሁን ለማጥፋት የተሰበሰቡትን እነዚህ አረማውያን ሕዝቦች ነገ ለመውጋት ዝግጁዎች ሆናችሁ ቆዩ፤ 59 ምክንያቱም የሕዝባችንንና የቤተ መቅደሳችንን ጥፋት ከማየት እየተዋጋን መሞት ይሻለናል። 60 የእግዚአብሔር (የሰማይ) ፈቃድ ይፈጸማል”። |